Friday, June 14, 2013

ግብፅ የትምክህት አስተያየቶችን ከመስጠት መቆጠብ አለባት - ዩዌሪ ሙሶቮኒ


 የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሶቮኒ የግብፅ መንግስትና ሌሎች ቡድኖች የትምክህትና ምክንያታዊ ያልሆኑ አስተያየቶችን ከመሰንዘር አንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን ቺምፕ ሪፖርትስ ድረ ገፅ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሚገነባውን የሃይል ማመንጫ ግድብ አስመልክተው የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን አንብቤያለሁ፡፡ በዚህ ነገር የኢትዮጵያ መንግስት መደነቅ ነው የነበረበት፡፡  ይህ ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ሊተገብሩት የሚገባ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ ካደገባቸው ምክንያቶች ውስጥም አንዱ ይሄው ነው፡፡ ስለዚህ የግብፅ መንግስትም ሆነ በሃገሪቱ ያሉ ትምክህተኛ ቡድኖች የባለፉትን የግብፅ መሪዎች ስህተት መድገም የለባቸውም፡፡”
    አፍሪካ አሁን ግብፅ ጥቁር አፍሪካውያንን እንድትጎዳ የሚፈቅድ አህጉር አይደለም ብለዋል ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሶቮኒ ፡፡
“ማንም የአፍሪካ ሃገር ግብፅን መጉዳት አይፈልግም፡፡ ሆኖም ግብፅም ጥቁር አፍሪካውያንንና የአካባቢውን ሃገሮች እየበደለች መቀጠል የለባትም” ብለዋል፡፡ ግብፅ ያለፉት መሪዎቿን የተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫ መከተል የለባትም ያሉት ሙሶቮኒ ለናይል ወንዝ ስጋት የሚሆነው የግድቦች ግንባታ ሳይሆን የሃይል አቅርቦት እጥረትና በአካባቢው ያለው ኋላቀርነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 
 ትልቁ የናይል ወንዝ ስጋት ስር የሰደደው የልማት ኋላቀርነት ነው፡፡ ይህም በሃይል አቅርቦት እጥረትና በኢንዱስትሪ ያለመስፋፋት የሚገለፅ ነው፡፡ ሃይል ለማግኘትና ለዘልማዳዊ እርሻ ሲሉ አርሶ አደሮች ደኖችን ይመነጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን ያዛባል፡፡”
ዩዌሪ ሙሶቮኒ ይህን ሃሳባቸውን ለቀደሙት የግብፅ መሪዎችም ሆነ ለአሁኖቹ እንደመከሩ ተናግረዋል፡፡ አሁንም ከግብፅ በኩል የሚሰነዘሩ የትምክህት አስተያየቶች እንዲቆሙና በስሜት ላይ ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውይይት በሁለቱ ሃገራት መካከል እንዲካሄድ መክረዋል፡፡
                                                                 ምንጭ፤ ቺምፕሪፖርትስ

No comments:

Post a Comment