Friday, June 14, 2013

በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መሀመድ አማን እና የኔው አላምረው አሸነፉ


     አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2005   በተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ኢትዮጵያውያኖቹ መሀመድ አማን እና የኔው አላምረው አሸነፉ። የአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ አሸናፊው መሀመድ አማን በ800 ሜትር ፥ እንዲሁም የኔው አላምረው በ1500 ሜትር አሸናፊ ሆነዋል።
    መሃመድ አማን ርቀቱን በ1 ደቂቃ ከ43.61 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት በርቀቱ የአመቱን ፈጣን ሰአት በማስመዝገብ ሲያሸንፍ ፥ ፈረንሳዊው ፒዬ-አምብሮስ እና ደቡብ አፍሪካዊው አንድሬ ኦሊቨር ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል  ሰባት ውድድሮች በሚካሄዱበት የ800 ሜትር ውድድር ዳይመንድ ሊጉን ጉዳት ላይ ያለው የኦሎምፒክ እና የአለም ሻምፒዮኑ ኬኒያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በስምንት ነጥብ ሲመራ ፣ መሀመድ አማን በስድስት ነጥብ ይከተላል።
         በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር የተካፈለው ሌላው ኢትዮጵያዊ የኔው አላምረው ርቀቱን 12 ደቂቃ ከ54.95 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ የአመቱን ፈጣን ሰአት አስመዝግቦ አሸንፏል። የአሸናፊነት ግምቱን ያገኘው ሀጎስ ገብረህይወት በ12፡55.73 ሁለተኛ ሲሆን ፥ ኬኒያዊው አይሳያ ኮይች ሶስተኛ ደረጃን አግኝተው አጠናቀዋል። ዳይመንድ ሊጉን ሀጎስ ገብረህይወት በ10 ነጥብ ሲመራ ፣ የኔው አላምረው በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይከተላል።
     በሴቶች 1500 ሜትር በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ እና ዜግነቷን ከኢትዮጵያ ወደ ስዊድን የቀየረችው አበባ አረጋዊ ፉክክር በአበባ አረጋዊ የበላይነት ተጠናቋል። አበባ ርቀቱን 4፡00.23 በሆነ ጊዜ ስታጠናቅቅ ፥ ገንዘቤ በ4፡01.62 ሁለተኛ ፣ አሜሪካዊቷ ጄኒ ሲምሰን ሶስተኛ ሆነዋል። በርቀቱ ዳይመንድ ሊጉን አበባ አረጋዊ በ12 ነጥብ ስትመራ፣ ገንዘቤ ዲባባ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ትከተላለች።
     በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሶፊያ አሰፋ ከወደቀችበት ተነስታ ርቀቱን 9፡21.24 በሆነ ጊዜ በሶስተኛነት ስታጠናቅቅ ፥ ውድድሩን ኬኒያዊቷ ሚልካ ቼሞስ የሀገሯን ልጅ ሊዲያ ቼፕኩሪን አስከትላ በመግባት በአሸናፊነት አጠናቃለች። በርቀቱ ዳይመንድ ሊጉን ሊዲያ ቼፕኩሪ በ10 ነጥብ ስትመራ፣ ሶፊያ አሰፋ እና ሚልካ ቼሞስ በእኩል አራት ነጥብ ይከተላሉ።ቀጣዩ የዳይመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር የፊታችን ሀሙስ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ይካሄዳል።

No comments:

Post a Comment