ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በአውሮፓ መድረኮች የበላይነታቸውን አሳዩ
ቼክ ሪፐብሊክ ኦስትራቫ ውስጥ (ሰኔ 27 ቀን 2013 ) በተካሄደው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር የርቀቱ ንግስት ጥሩነሽ ዲባባ 30 ደቂቃ ከ26.67 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ በርቀቱ በራሷ ተይዞ ቆይቶ የነበረው የስፍራውን ክብረወሰን አሻሽላ አሸንፋለች።
ጥሩነሽ 10 ሺህ ሜትርን መሮጥ ከጀመረችበት ከስምንት አመት በፊት ጀምሮ አንድም ጊዜ ያልተሸነፈች ሲሆን ይህ የኦስትራቫ ድሏ 10ኛው ተከታታይ ድሏ ነው። በዚህ ውድድር ሌላዋ ኢትዮጵያዊት በላይነሽ ኦልጂራ ለራሷ የውድድር አመቱ ምርጥ ሆኖ በተመዘገበ ሰአት 30:31.44 በመጨረስ ኬኒያዊቷ ግላዴስ ቼሬኖን ተከትላ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቃለች።
ሌላው የኦስትራቫ የመሮጫ ትራክን ያደመቀ ኢትዮጵያዊ አትሌት የ800 ሜትር ኮከቡ መሀመድ አማን ሲሆን ርቀቱ ሊጠናቀቅ 60 ሜትሮች ያህል ሲቀሩት ባሳየው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት 1:43.78 በሆነ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። በርቀቱ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን የሆነው መሀመድ አማን ራሱን የፊታችን ነሀሴ ወር በሞስኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በግሩም ሁኔታ እያዘጋጀ ነው። ሞስኮ ላይ የመሀመድ አማን ቁጥር አንድ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው ኬኒያዊው የርቀቱ ንጉስ ዴቪድ ሩዲሻ በአሁኑ ጊዜ ጉዳት ላይ ነው።
እንደገና በታደሰው የኦስታራቫው ሜስቲስኪ ስታዲዬም የተገኘው ተመልካች እ.አ.አ በ2004 በዚሁ ስታዲዬም በ10 ሺህ ሜትር የአለም ክብረወሰንን የሰበረው ታላቁ ቀነኒሳ በቀለ አስደናቂ ብቃቱን በ5 ሺህ ሜትርም ያሳያል በሚል ጠብቆ የነበረ ቢሆንም አስደናቂ ብቃቱን ለማሳየት የቻለው ሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣቱ ሙክታር ኢድሪስ ነበር።
በርቀቱ የአለም ወጣቶች ሻምፒዮን ሙክታር በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ርቀቱን በ13፡03.69 በማጠናቀቅ የራሱን ምርጥ ሰአት አስመዝግቦ አሸንፏል። ለአሸናፊነት ተጠብቆ የነበረው እና በርቀቱ የኦሎምፒክ እና የአለም ሻምፒዮን እንዲሁም የክብረወሰኑ ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ በኦስትራቫው ውድድር ርቀቱ ሊጠናቀቅ 400 ሜትሮች ያህል እስኪቀሩት ድረስ ከመሪዎቹ ጋር አብሮ የነበረ ቢሆንም ድሮ ይታወቅበት የነበረው ፍጥነት የመቀየር እና የአጨራረስ ብቃቱ አብሮት ባለመኖሩ 5 ሺህ ሜትሩን በ13፡07.88 አጠናቆ አራተኛ ደረጃን አግኝቶ ጨርሷል። ኬኒያዊያኖቹ አጉስቲን ቾጊ እና ላዊ ላላንግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተው አጠናቀዋል።
በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያዊቷ ህይወት አያሌው ለራሷ ፈጣን የውድድር አመቱ ሰአት ሆኖ በተመዘገበላት 9:19.87 ጊዜ በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች። የውድድሩ አሸናፊ ኬኒያዊቷ ሚልካ ቼሞስ ነች።
ስዊድን ሶሌንቱና ውስጥ በተካሄዱት የአትሌቲክስ ውድድሮች (ሰኔ 27 ቀን 2013) በአብዛኛው በ5 ሺህ ሜትር የምትታወቀው ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ የረጅም ርቀት ሯጭ መሰረት ደፋር በ10 ሺህ ሜትር ተወዳድራ ርቀቱን በ30፡08.06 በማጠናቀቅ ጥሩነሽ ዲባባ ኦስትራቫ ላይ ጥቂት ሰአታት ቀደም ብላ አስመዝግባው የነበረውን የአመቱን ፈጣን ሰአት በማሻሻል አስደናቂ ድል ተጎናጽፋለች።
በርቀቱ የተካፈሉት ኢትዮጵያዊያኖቹ አፈረ ጎድፋይ (31፡08.23) እና ጎተይቶም ገብረስላሴ (31:51.42) የራሳቸውን ምርጥ ሰአት በማስመዝገብ መሰረትን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተው አጠናቀዋል።
ልክ እንደመሰረት ሁሉ ስዊድን ሶሌንቱና ውስጥ የነገሰው ኢትዮጵያዊው ደጀን ገብረመስቀል ሲሆን፣ በለንደን ኦሎምፒክ በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ደጀን በ10 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ ርቀቱን በ26:51.02 በማጠናቀቅ የአመቱን ፈጣን ሰአት በማስመዝገብ አስደናቂ ድል አግኝቷል። ከደጀን ጋር በ10 ሺህ ሜትሩ የተፎካከሩት ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን አበራ ኩማ በ26:52.85 የራሱን ፈጣን ሰአት እና የማነ መርጋ በ26:57.33 የራሱን የውድድር አመቱ ፈጣን ሰአት በማሻሻል እንደ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎችን አግኝተው አጠናቀዋል።
Source :- Total 433