Wednesday, June 4, 2014

ከታሪክ ማህደር …

   
   

    አጤ ቴዎድሮስ  / 1845 – 1860 ዓ.ም /  ለ15 አመት ያህል ኢትዮጵያን ካስተዳደሩ በኃላ  ከእንግሊዞች ጋር በተፈጠረው ግጭት እጄን ለጠላት አልሰጥም በማለት በ1860 ዓ.ም በራሳቸው ሽጉጥ ህይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ 


   አጤ ቴዎድሮስ በመቅደላ አምባ ራሳቸውን ከገደሉ በኃላ ደጃዝማች ካሳ ምርጫ /በዝብዝ ካሳ/ በትግራይ ፣ ዋግሹም ጎበዜ በላስታ ፣ ንጉስ ምኒልክ በሸዋ፣ በጎጃም ራስ ደስታ፣ በወልቃይት ጥሶ ጎበዜ ሆነው የንጉሰ ነገስትነቱን ስልጣን ለማግኘት ወታደር እያስታጠቁ ጦር እየሰበቁ በመሽቀዳደም ላይ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ዋግሹም ጎበዜ ኃይላቸውን ይበልጥ አጠናክረው በጌምድር፣ ጎጃም እና ወሎንም ካሰገበሩ በኃላ ስመ መንግስታቸው “ተክለ ጊዮርጊስ” ተብሎ በጎንደር ለ3 አመት ያህል ነገሱ፡፡

   ምንም እንኳ የጎጃም፣የወሎ እና የበጌምድር ገዥዎች አሜን ብለው ቢቀበሉም የትግሬ መሸፈት ስላሰጋቸው የወታደራቸውን ብዛት ለማሳወቅ አንድ ስልቻ ጤፍ ሞልተው ለበዝብዝ ካሳ ይልካሉ፡፡ በዝብዝ ካሳ /ካሳ ምርጫ/ የአጤ ተክለ ጊዮርጊስ አባት አንካሳ መሆናቸውን በማስታወስ “ከቱርክ ይዋጋል እንኳን ካንካሳ  ያባ ፈንቅል ልጅ ወሬሳው ካሳ” ብለው ፎክረው “ወታደርህ ቢበዛ በጥይት ነው የምቆላው” በማለት ጤፉን አስቀልተው ላኩላቸው፡፡ በዚህኑ ጊዜ የአጤ ተክለ ጊዮርጊስ ባለቤት የደጃዝማች በዝብዝ ካሳ እህት እቴጌ ድንቅነሽ እንዲህ ብለው ገጠሙ ፡-
                      
                     ተዉ እናንተ ሰዎች ወደ አድዋ አትሂዱ
                      በእሳተ ገሞራ እንዳትነዱ
                      ያባ በዝብዝ ካሳ ቆራጥ ናትና ሆዱ፡፡

   ከዚያ በኃላ አደዋ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም. ጦርነት ተጋጥመው አጤ ተክለ ጊዮርጊስ ተማረኩ፡፡ በአምባ ሰላማ ተራራ በእስራት እንዲቆዩ በተደረገበት ጊዜም እቴጌይቱ የሚከተለውን ገጠሙ ፡-
                        ተናግሬ ነበር እኔስ አስቀድሜ
                        አሁን ምን ልናገር ከሀዘን ላይ ቆሜ
                        የተሻረው ባሌ ተሿሚው ወንድሜ
                        ከእንግዲህስ ወዲህ አለምንም ዕድሜ ፡፡ 


  ደጃዝማች ካሳ ለበዓለ ንግሳቸው ሲዘጋጁ ከቆዩ በኃላ ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. “ዮሐንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው በአቡነ አትናቴዎስ እጅ በአክሱም ጽዮን ስርአተ ንግስናቸው ተፈፀመ፡፡
  
  
  ግብፆች የአባይ ወንዝ ዋናው ምንጩ ከኢትዮጵያ ስለሆነና ይህም ወንዝ ለግብፆች የህይወታቸው ምሰሶ በመሆኑ፣ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ከፈረዖኖች ዘመነ መንግስት ጀምሮ በየጊዜው እየተዋጉ መኖራቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ አጤ ዮሐንስ  የቱርኮች እና የግብፆች የተባበረ ጦርን ጉንዲት ላይ ህዳር 7 ቀን 1867 ዓ.ም. እና ጉራዕ  ላይ የካቲት 30 ቀን 1868 ዓ.ም. ድል አድርገዋቸዋል፡፡   

  አጤ ዮሐንስም ከድል በኃላ ለምርኮኞቹ ምህረት በማድረግ ከባህር ማዶ አሻግረው ሲያባርሩ “የግብፅ ሰራዊት በጫማው እና በእግሩ የሀገሬን አፈር ይዞብኝ እንዳይሄድ ጫማውን አስወልቃችሁ ፣እግሩንም አጥባችሁ ባህሩን አሻግራችሁ አባሩት” ብለው ለሰራዊታቸው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

   እዚህ ላይ ቀደምት ነገስታት እና አባቶች ለሀገራቸው እና ለአፈራቸው ያላቸውን ፍቅር በእንዲህ እና በእንዲያ አይነት ነበር የሚገልጡት፤ አሁንስ ሲባል …………….

                        

No comments:

Post a Comment