Sunday, June 29, 2014

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን 22ሺ 497 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስመርቀ፡፡

   እሁድ ሰኔ 22፣2006 ከተመረቁት ቤቶች መካከል 11 ሺ ያህሉ እጣ የወጣባቸው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ለነዋሪዎች ያልተላለፉ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች ናቸው። 

   በምረቃው ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮነን መንግስት በከተሞች ያለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

  የቤት ልማት ምርሃ ግብሩ ከተማዋን ደረጃ የጠበቀች ከማድረግ ባሻገር ለድህነት ቅነሳውና  ለቁጠባ መሰረት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው አስተዳደሩ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፋቸው ቤቶች መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት በሚቀጥሉት 3 ወራትም 73ሺ ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይደረጋሉ፡፡አስተዳደሩ የከተማዋን የቤት ችግር ለመቅረፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡


  ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ቁልፍ የተረከቡ እድለኞች  መንግስት የከተማዋን ህዝብ የቤት ባለቤት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያጠናከር ጠይቀዋል፡፡የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለማግኘት አጋጣሚው የቁጠባ ባህላቸውን እንዳሳደገላቸውም ለኢሬቴድ ተናግረዋል፡፡

 በቤቶቹ ግንባታ ላይ 785 የስራ ተቋራጮችና 939 ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡ ከተመረቁት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በየካ 9 ሺ 766፣ በአቃቂ ቃሊቲ 5 ሺ 310፣ በቂርቆስ 1 ሺ 536 እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ደግሞ 5 ሺ 885  ናቸው ።

No comments:

Post a Comment