Tuesday, May 20, 2014

የአደዋ እና ማይጨው ዘማች ታቦት - ግንባሮ ማርያም


 የግንባሮ ማርያም ቤተክርስቲያን በሰ/ሸዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ በባቄሎ ቀበሌ አስተዳደር የምትገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ 144 ከደብረ ብርሃን ደግሞ 14 ያህል ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ ከባቄሎ ት/ቤት በስተጀርባ ባለው ጥርጊያ መንገድ በመኪና 6 ደቂቃ ከተጓዙ በኋላ ቤተክርስቲያኗን  ያገኟታል፡፡ የግንባሮ ቅድስት ማርያም ቤተ- ክርሰቲያን በአፄ ናኦድ ዘመነ መንግስት (1495 – 1508) በአርከ ስሉስ አማካኝነት እንደተቆረቆረችም ይነግራል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ባህልን አጥባቂ እንደመሆናቸው በየዓመቱ ለገና በዓል በግንባሮ ሜዳ በገበሬው መካከል እየተገኙ ባህላዊውን የእሩር ጨዋታ ሲመለከቱ በመዋል ለአሸናፊው ቡድን እንደ ዘመኑ ልምድ ጋሻ ወይም ጦር ይሸልሙ ነበር፡፡ ከአመታት አንድ ቀን የአንደኛው ቡድን አባል አክርሮ የለጋት እሩር ሜዳ ለሜዳ ተንከባላ ከእግራቸው ስር ብታርፍ ፡-
                “ ወይ እሩር ወይ እሩር ወይ እሩር ደፋር
                  የንጉሱን ጫማ ትስመው ጀመር፡፡”  ተብሎም ተገጠሞ ነበር ይባላል፡፡ ግንባሮ ጎልማሶች በእሩር ልጊያ እና በፈረስ ግልቢያ የሚያሳዩት ቅልጥፍና እጅጉን ያስደስታቸው እንደነበር አባቶች ይመሰክራሉ ፡፡ ወደ ዋናው ታሪክ እንመለስ እና ስለ ግንባሮ ማሪያም የጀመርንውን መረጃ እንቀጥል……. 

ጣሊያን ባህር ማዶ አሻግሮ ወሰን ተዳፍሮ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የግፍ ወረራ መያዙን የሰሙት ዓፄ ምኒልክ “ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት” ብለው በ1888 ዓ.ም አዋጅ አስነግረው ወደ ጦርነቱ ዘመቱ ፡፡በወቅቱ ከዘመቱ ታቦታት መካከል ግንባሮ ማርያም እና አራዳ ጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ ፡፡ አቡነ ማቲዎስ እና ታቦተ ማርያምን የያዙት ካህናት ከፊት ንጉሱ ደግሞ ከኋላ ነበሩና ታቦተ - ማርያም የታለች ብለው ንጉሱ ሲጠይቁ ይቻት ከግንባርዎት/ ከፊትዎት/ ይሏቸዋል፡፡ እናም ይህ ሁነት ለአካባቢው እና ታቦቷ ላለችበት ቤተክርስቲያን መጠሪያ ሆኗል፡፡

 በአደዋ ጦርነት ወቅት አብራ ለዘመተችው የግንባሮ ማርያም ዓፄ ምኒልክ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የአቡነ - ሰላማ /ከሳቴ ብርሃን/ እና ሌሎች ዘውዶችን ለመታሰቢያ እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡ታቦቷ ከአደዋ ጦርነት ባሻገር በ1928ቱ (ዓ.ም) የማይጨው ጦርነት ዘምታለች፡፡ እንዲያውም የአካባቢው አባቶች እንደሚናገሩት ታቦቷ ከዚህም በተጨማሪ 14 ያህል ጦርነቶች ዘምታ በድል ተመልሳለች፡፡ ስለ ቤተክርስቲያኗ ታሪክ እኔ በትንሹ አወጋኋችሁ በቦታው ተገኝታችሁ ብታዩ ደግሞ በርካታ ቅርሶችን ትጎበኛላችሁ፣ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ለሆናችሁም ብዙ ነገር እንደምታገኙ አልጠራጠርም፡፡

                   መልካም መልካሙን ተመኘሁ ! ሰላም እና ጤና አይለየን!!!

No comments:

Post a Comment