Saturday, May 17, 2014

ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ነገ በማንቸስተር ከተማ በሚካሄደው የታላቁ ማንቸስተር 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ይሳተፋሉ::

 
     ነገ የፓሪስ እና የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች እርስ በእርስ የሚገናኙበት የታላቁ ማንቸስተር የሩጫ ውድድር ቀነኒሳ በቀለ እና ዊልሰን ኪፕሳንግን እርስ በእርስ ያገናኛቸዋል፣ የአለም የ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ሪከርድ ባለቤቱ ቀነኒሳ በቀለ በብሪታኒያ ምድር የመጀመሪያውን የ10ሺህ ውድድር ለማድረግ ትላንት ማለዳ ማንቸስተር ገብቶአል፡፡

       የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ ከበርሊን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁዋላ በደረሱበት ተደጋጋሚ ጉዳቶች ከውድድር ጭምር ርቆ የነበረ ሲሆን በመስከረም ከእንግሊዛዊው የወቅቱ የአለም የ5 እና 10 ሺህ ሜትር አሸናፊ ሞ ፋራ እንዲሁም ሀይሌ ገብረስላሴ ጋር በቡፓ ግሬት ኖርዝ ረን ድል አድርጎአል፡፡

   
      ከወር በፊትም በፓሪስ ማራቶን በ2፡05፡04 በአስገራሚ ሁኔታ አሸናፊ በመሆን ዳግም ወደ ድል ተመልሶአል፣ ቀነኒሳ የአለም የማራቶን ሪከርድ መስበር እና በስሙ ብሎም በሀገሩ ኢትዮጵያ ማስመዝገብ እንደሚፈልግም ተናግሮአል፣ ነገም የአለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ከሆነው ኪፕሳንግ ጋር ይፋጠጣል፡፡ የለንደን ማራቶን አሸነፊው ኪፕሳንግ እና ቀነኒሳ በቀለ እርስ በእርስ ሲገናኙ የመጀመሪያቸው ነው ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ በ2፡03፡23 የአለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ሲሆን በለንደንም በ2፡04፡29 ባለፈው ወር አሸነፊ ነበር፡፡ 


      በትራክ የአለም ሻምፒዮናዎች በርካታ ወርቅ ሜዳሊዎችን ማሸነፍ የቻሉት ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ነገ በማንቸስተር አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢገመትም ከባድ ፈክክር ግን ይጠብቃቸዋል፣ በለንደን ማራቶን ሶስተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸነፊዋ የአምስት ጊዜ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለድሏ ጥሩነሽ ከአውሮፓዊ ተወዳዳሪዎች ጋር ትፋጠጣለች፡፡ በለንደን ማራቶን ኤደን ኪፕላጋት እና ፍሎረንት ኪፕላጋትን ተከትላ በ2፡20፡35 የማራቶንን ውድድር የፈጸመችው ጥሩነሽ ሙሉ በሙሉ ግን እራሷን ወደ ማራቶን አላዛወረችም፡፡
                                                                        መልካም እድል!!

No comments:

Post a Comment