Friday, May 16, 2014

በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉና በ2005 ዓ.ም የተጀመሩ የ40 /60 ቁጠባ ቤቶች መዋቅራዊ ግንባታ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይጠናቀቃሉ ተባለ።


        የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የቤቶቹ ግንባታ እስከ 58 በመቶ ደርሷል ብሏል።የኢንተርፕራይዙ ስራ አስኪያጅ አቶ ክንዴ ብዙነህ ፤ በሰንጋ ተራና በክራውን በ2005 ዓ.ም የተጀመሩ የ40 / 60 የቤቶች ግንባታ ከ58 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን ገልጸው ፥ በ2006 ዓ.ም የተጀመሩ የቤቶች ግንባታም እስከ 20 በመቶ ተጠናቀዋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 13 ሺህ 881 ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በዚህም በሰንጋ ተራ 410 ቤቶች ፣ በክራውን ሳይት 880 ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ፥ አፈፃፀማቸውም 58 በመቶ እና 46 በመቶ ላይ ይገኛል።

      በ2005 ዓ.ም በሰንጋ ተራ ሳይት የተጀመሩ 1292 ቤቶች ፣ በክራውን ደግሞ 5126 ቤቶች ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛልም ነው የተባለው።ለቤቶቹ ግንባታ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ፥ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ዜጎች የ29.6 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ገልፀዋል።
ኢንተርፕራይዙ በ2007 ዓ.ም 15 ሺህ ቤቶችን በመገናኛ ፣ በኢምፔሪያል ፣ሲ ኤም ሲ፣ በቦሌ ቡልቡላና በሌሎችም አካባቢዎች ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።ስራ አስኪያጁ በመግለጫቸው የመሰረተ ልማት ችግር ፣ የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የተቋራጮች የአቅም ውስንነት በክፍተትነት አንስተዋል።ለ40 /60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች 164 ሺህ 79 ሰዎች ተመዝግበው 2.5 ቢሊዮን ብር ቆጥበዋል።
                                                                                                 ምንጭ፡-    ኤፍ.ቢ.ሲ

No comments:

Post a Comment