አዲሱ የአዋሽ ድልድይ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ቀልጣፋና
የተሰላጠ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። ከጃፓን መንግሥት በተገኘ 240 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተገነባው የአዋሽ ወንዝ ድልድይ
ተጠናቆ የካቲት 21 ቀን 2007 ተመርቋል። ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ድልድዩ አገሪቱ ከጅቡቲና ከሶማሊያ ጋር ፈጣንና የተቀላጠፈ
የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖራት የሚያደርግ ነው።
የኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የወጪ ንግድ በዚህ መንገድ እንደሚስተናገድ
የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የድልደዩ መገንባት ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስቀር ነው ብለዋል። አዲሱ ድልድይ ከቀድሞው ድልድይ ጋር ሲነፃጸር በመሸከም አቅሙና በአንደ ጊዜ ሁለት
ተሽከርካሪዎችን በማሳለፍ የተሻለ እንደሆነም ጠቁመዋል። ድልድዩ በቀን ከ22 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
የቀድሞው ድልድይ በ1964 ዓ.ም የተገነባ ሲሆን በአንድ ጊዜ 36 ቶን ክብደት የመሸከም
አቅምና በአንድ ጊዜ ከአንድ ተሽከርካሪ በላይ የማሳለፍ አቅም አልነበረውም። አዲሱ ድልድይ ግን በአንድ ጊዜ ከ40 ቶን በላይ ክብደት የመጫን አቅም ሲኖረው በአንድ
ጊዜ ሁለት ተሽከርካሪዎችን የማሳለፍ አቅምም እንዳለው የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment