Friday, February 27, 2015

አይረሴ የአድዋ ጀግኖች እና የጥቁር ህዝቦች ሰማዕታትን እናስታውሳቸው……!!!!


  ኢትዮጵያ አድዋ ላይ በጦርነት ስትታመስ እነዚያን ሰልጥነናል ያሉትን የጣሊያን ወታደሮች ያንቀጠቀጡ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች ብዙ ነበሩ፡፡
          “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
          መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” እየተባለም ተዜሞላቸዋል፡፡ እነዚህ ጀግኖች አይረሴ የአድዋ ጌጥ እና የጥቁር ህዝቦች ሰማዕት ናቸው፡፡ 


   ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ አድዋ ሲዘምቱ ተናዘዙ “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፣ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን /አፅሜን/ ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ” አሉ፡፡ እንደተባለውም ሆነ በፅኑ ሲፋለሙ ስለ ሀገራቸው ነፃነት አደዋ ላይ ወደቁ፡፡ እንደቃላቸውም አስከሬናቸው ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሶ በክብር ተቀመጠ፡፡ ይህንንም በጥንታዊዋ የአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን እቃ ቤት ውስጥ ይመለከታሉ፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አፄ ምኒልክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱም ይነገራል፡፡
  

  የፊታውራሪ ገበየሁ (በአካባቢው አጠራር ጎራው ገበየሁ) በአድዋ የጦር አውድማ ህይወታቸው ሲያልፍ አፅማቸው ተለቃቅሞ በትንሽ ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ ነበር፡፡ ከ7 ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ቦታው ሲመለስ ከመስተዋት በተሰራ ሳጥን በቤተ ክርስቲያኗ እቃ ቤት ውስጥ ተቀምጧል፡፡ በሳጥኑ ላይም “የምኒልክ የጦር አበጋዝ እና የአድዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ የካቲት 23,1888 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት በቆራጥነት ሲዋጉ በዚያው በጦርነቱ ቦታ ላይ እንዳረፉና ከሰባት አመታት በኋላም አፅማቸው በትውልድ ቦታቸው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ስለ መቀመጡ” በፅሁፍ ሰፍሯል፡፡
  

  ፊታውራሪ ገበየሁ እና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ክርስትና የተነሱባት የአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በርከት ያሉ የብራና መፅሃፍት ፣ መስቀሎች እና ፅናፅኖች እንዲሁም ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶችን ይዛለች፡፡ ብዙዎቹ ከንጉስ ሳህለስላሴ እና ከልጅ ልጃቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተበረከቱ ናቸው፡፡ የአደዋው የጦር መሪ የፊታውራሪ ገበየሁ አፅም እና ከንጉስ ሳህለስላሴ እስከ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ቅርሶች በቤተ ክርስቲያኗ ጠባብ እቃ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ሰፋ ባለ መልኩ በሙዚየም ቢቀመጡ ደግሞ ለቅርሶቹ ደህንነትም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹ ይሆናልና ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡
   

  ዛሬ ዋነኛ አላማዬ የአድዋው የጦር መሪ ፊታውራሪ ገበየሁን ማስታወስ ነውና በዚሁ ላብቃ፤ በሌላ ጊዜ በአንጎለላ ስላሉ ቅርሶች እና አንዳንድ መረጃዎች መረጃ አደርሳችኋለሁ፡፡ እናንተም ያላችሁን እና የምታውቁትን አካፍሉኝ፡፡

                    ቀደምቶቻችን እናስታውስ ፣ እናክብር
                     ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት….. !!!


No comments:

Post a Comment