አዞ ሲበላ
ያለቅሳል ይባላል የሚበላ ከሆነ ለምን ያለቅሳል ፤ እውንስ አዞ ያለቅሳልን ? አዞ ቆዳው በጣም ጥቅጥቅ ነው፡፡ ስለዚህ በላብ መልክ
በቆዳው የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ በጥርሶቹ ደግሞ ቁርጥ እያደረገ ዋጥ ያደርጋል እንጂ አያኝክም ፣ አያላምጥም፡፡ ስለዚህ በቆረጠው
ልኬት ወደ ውስጥ እንዲገባ ነው የሚያደርገው እና አንዳንድ ከፍ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጉሮሮው ይጨናነቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ላቡ በአይኑ
ዱብ ዱብ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ላብ እንጂ እምባ አይደለም፡፡ አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም ስትል የአርባ ምንጭ አዞ ማደለቢያ
የጉብኝት ባለሙያ ወ/ሪት ህይወት አሰፋ አጫወተችኝ፡፡
አስጎብኛችን ጨዋታ አዋቂ ናት ፡፡ እያዋዛች ቁም ነገር ማስኮምኮሟን ቀጥላለች…… በአለማችን ላይ 25 አይነት የአዞ ዝርያ አይነቶች አሉ፡፡ በአፍሪካ 4 ዓይነቱ ሲገኙ በኢትዮጵያ ደግሞ “የናይል አዞ” የተባለው ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ የናይል አዞ ካሉት ሁሉ ተፈላጊ ፣ ተመራጭ ፣ ተወዳጅ ሲሆን ግን ኃይለኛ ቢሆንም ካልነኩት አይነካም፤ ከነኩት ግን አይለቅም ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው ባህሪው ስትል አከለችልኝ፡፡ አዞዎች ከእንቁላል ሲፈለፈሉ መናከስ ይጀምራሉ፤ ምክንያቱም ከጥርስ ጋር ስለሚፈጠሩ፡፡ ተንቀሳቃሽ ምላስ የላቸውም፡፡ ጥርሳቸው ግን ከ62 - 66 ይደርሳል፡፡ አዞ አያኝክም ፣ አያላምጥም ፣ አያጣጥምም ስለዚህ ቁርጥም እያደረገ ዋጥ ያደርጋል ማለት ነው፡፡
የጉብኝት ባለሙያዋ ወ/ሪት ህይወት አንዳጫወተችኝ በማዕከሉ ያሉ አዞዎች ከ3 - 6 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርድ የሚፈለጉበት /ቆዳቸው የሚፍለግበት/ ጊዜ ነው፡፡ ሲታረዱም የራሳቸው የሆነ መያዣ ዘዴ እና መምቻ ጥይት አለ፡፡ በዚህም ኢላማ የሚችል ሰው አናታቸው ላይ ይመታቸውና በማጅራታቸው/በጀርባቸው/ በኩል ይታረዳሉ፡፡
እኔም የዛሬ ጡመራዬን እዚህ ላይ ገታ ላድርግ፤ በሌላ ጊዜ ሌሎች መረጃዎች ይዤላችሁ ከች እላለሁ ፡፡ በተረፈ ግን እናንተ ጨምሩበት ፤ የምታውቁትንም መረጃ አካፍሉኝ…..
No comments:
Post a Comment