Saturday, July 19, 2014

ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ስራዎች እና የህይወት ተሞክሮ...

 እ.ኤ.አ መጋቢት 5፣ 1935 እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የተወለዱት ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ፡፡ አባታቸው የሙዚቃ ሊቅ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ የአባታቸው የጊታር እና የቫዮሊን ተማሪ ነበሩ፡፡ አሜሪካ የተዋወቁት እነዚህ ጥንዶች በ1923 የንጉሱ የዘውድ በዓልን ለማክበር እና ኢትዮጵያን ለመርዳት ከመጣው የካሪቢያን ቡድን ጋር አብረው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ በዚሁም ትዳር መስርተው ዮሴፍ ኃይለስላሴ ፎርድ እና አብይ ፎርድን ወልደው ኑሮአቸውን በኢትዮጵያ ቀጠሉ፡፡

  
    ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እናታቸው ባሰሩት ቤተ-ኡራኤል በኃላ ላይ ልዕልት ዘነበወርቅ በተባለው የአፀደ ህፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፤2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሊሴይ ገ/ማሪያም ከተማሩ በኃላ ስኮላርሽፕ አግኝተው ወደ አሜሪካ ሚሲሲፒ አቀኑ፡፡ በዚያም በፓኔ ውድስ ጁኒየር ኮሌጅ በኢለመንታሪ ኢዱኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በማስከተልም ከኮሎምቢያ  ዩኒቨርሰቲ ስኩል ኦፍ ጀኔራል ስተዲስ በፊልም ጥናቶች /Directing track and scholarship or criticisim track/ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወይም ማስተሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ የሙሉ ፕሮፌሰርንትን ማዕረግ እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ለ33 አመታት ያህል ሰርተዋል፡፡በቆይታቸውም በዩኒቨርሰቲው በኮምኒኬሽን ዲፓርትመንት የሬዲዮ፣ቴሌቪዥን እና ፊልም ትምህርት እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥም እንደ እነ ሀይሌ ገሪማ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲያስተምሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

   ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ የቀድሞው የአ.አ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምኒኬሽን የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን፤ የዩኒቨርስቲው ፐሬዚዳንት ፅ/ቤት ከፍተኛ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡በተጨማሪም በዩኒቨርስቲው የስነ ጥበባት እና ፊልም ት/ቤት ልዩ አማካሪ እና በዩኒቨርስቲው የፊልም ጥናት ክፍል ለመጀመር የተደራጀው ግብረ ሀይል አማካሪ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በአሜሪካ አየር ሀይል ኤሮ አክቲቪቲ በፓይለትነት አገልግለዋል ከዚህም ባሻገር የኢትዮ- አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ 

   ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ አማርኛ፣እንግሊዘኛ፣ፈረንሳይኛ እና ጣሊያንኛን በደንብ አቀላጥፈው ሲናገሩ አረብኛ እና ራሺያንኛ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ይሞካክራሉ፡፡ ጊታር ፣ሳክስፎን እና ፒያኖ የሚጫወቱት ፕሮፌሰሩ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን ይወዳሉ፡፡ አሁን ላይ የራሳቸውን የህይወት ታሪክ ለመፃፍ እየሞከሩ ሲሆን ከ26 የሚበልጡ ዶክመንታሪ ፊልሞችንም ሰርተዋል፡፡

Professor Abiy Ford with Tesfaye  Abebe
     በፕሮፌሰር አብይ ፎርድ እናት የተሰራው እና የተለያዩ ስሞች የተሰጡት ት/ቤት ከካዛንችስ - አቧሪ በሚወስደው መንገድ መለስ ፋውንዴሽን ፊልፊት ይገኛል፡፡ ይህ ት/ቤት ቤተ-ኡራኤል - ልዕልት ዘነበ ወርቅ - የካቲት 6 - ሚስስ ፎርድ መታሰቢያ የአፀደ ህፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የሚሉ ስያሜዎችን አግኝቷል፡፡አሁን ግን የሚስስ ፎርድ መታሰቢያ ሆኖ የትምህርት አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡

   ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ሰዓት በርካታ የውጪ ሀገር ዜጎች ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ የፕሮፌሰሩ ቤተሰቦች ግን ከኢትዮጵያ የሚለየን የለም መቃብራችንም በዚችው በምንወዳት ሀገር ይሆናል ብለው ወሰኑ ይህንንም አደርጉት፡፡ የፕሮፌሰር አብይ አባት እዚሁ ሞተው እዚሁ ተቀበሩ፣እናታቸው ልጆቻቸውን ለመጠየቅ አሜሪካ ሄድው ህይወታቸው እዚያ ቢያልፍም መቃብራቸው ግን ኢትዮጵያ ሆነ፡፡ወንድማቸውም በተመሳሳይ አሜሪካ ሞተ ኢትዮጵያ ተቀበረ፡፡ እንዲህ ያለውን የሀገር ፍቅር ፣ የሀገር መውደድ ከወዴት ያገኙታል….. እንዴትስ ይገልፁታል………!!!

No comments:

Post a Comment