Friday, July 11, 2014

የላሊበላን አብያተ-ክርስትያናት በዓለም ላይ እንዲታወቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ልዕልት ሂሩት ደስታ አረፉ


እንደዛሬው ወደ ቅዱስ ላሊበላ ገዳማት እንደልብ መሄድና መጎብኘት በማይቻልበት ወቅት የሥፍራውን ታላቅነትና ተአምረኝነት ተገንዝበው አያሌ ተግባራትን የፈፀሙ ናቸው። ወደ ከተማዋ የሚያስገባው መንገድ በሥርዓት እንዲሰራ፣ የእንግዶች ማረፊያ እንዲታነጽ፣ አብያተ-ክርስትያናቱ እንዲታደሱ ያደረጉና በኋላም የፕላኔታችን ድንቅዬ ብሎም ብርቅዬ ኪነ-ህንፃዎች መሆናቸውን ለማመላከት ከውጭ ሀገራት አጥኚዎችን እየጋበዙ ሲያስተዋውቁ የነበሩት ልዕልት ሂሩት ደስታ 84 ዓመታቸው አረፉ።

የህይወት ታሪካቸው እንደሚያወሳው ልዕልት ሂሩት ደስታ የልዕልት ተናኘወርቅ እና የጀግናው የክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው ሦስተኛ ልጅና የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና የግርማዊት እቴጌ መነን የልጅ ልጅ ናቸው። ልዕልትነታቸው በጣም ተወዳጅ አስተማሪ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶች አስከባሪና ዓለም እንዲያውቃቸው ታታሪ፣ ተሟጋች፣ ሩህሩህ፣ ለጋስ እንዲሁም በውጪው ዓለም አገራቸውን በታላቅነት የወከሉ አኩሪ ኢትዮጵያዊት እንደነበሩ ይነገራል። ልዕልት ሂሩት ደስታ አባታቸው ክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው የከፋ ክፍለ ሀገርን በሚያስተዳድሩበት ወቅት በሚያዝያ 12 ቀን 1922 . በጅማ ከተማ ተወለዱ። ፋሽስት ኢጣሊያ 1928 . ሀገራችንን በመውረሩ ከእናታቸውና ከንጉሣውያን ቤተሰብ ጋር በመጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሀገር በህፃን ዕድሜያቸው ተሰደዱ። ወላጅ አባታቸው ጀግናው ራስ ደስታም የኢጣሊያን ጦር ለመመከት የደቡብ ኢትዮጵያን ጦር በመምራት ሲዋጉ ቡታጅራ ላይ ተሰው።

ከህይወት ታሪካቸው መረዳት እንደሚቻለው ልዕልት ሂሩት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር አዳሪ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በታወቁት የፈረንሳይ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ ኒውዮርክ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። ልዕልት ሂሩት ትጉህ ተማሪ ነበሩ። እንዲሁም የስፖርት አፍቃሪ በመሆናቸው በጃንሆይ ሜዳ የፈረስ ግልቢያ ውድድር ተሳታፊ ነበሩ። ልዕልት ሂሩት አያታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ኢራን፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ አልጀሪያና በርማን በጎበኙበት ወቅት የክብር ተከታይ ሆነው ሄደዋል። እንዲሁም 1955 . ግርማዊ ጃንሆይ ታሪካዊ የአሜሪካ ጉብኝት ወቅት ልዕልትነታቸውን ተከትለው የሄዱ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ኬነዲ ለግርማዊነታቸው አቀባበል ባደረጉት ንግግር ላይ ጃንሆይ ልዕልቲቷን የልጅ ልጃቸውን ይዘው በመምጣታቸው ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

Princess Hirut Desta and Emperor Haile Selassie being welcomed at Washington D.C.s Union Station by President and Mrs. Kennedy.

ልዕልት ሂሩት የግርማዊ ጃንሆይንና የግርማዊተ እቴጌን አርአያ በመከተል የዘመናዊ ትምህርት በተለይም ለወጣት ሴቶች ልጆች ትምህርት የማግኘት ዕድል በሀገራችን መስፋፋት እንዳለበት ያምኑ ነበር። ስለዚህም ልዕልትነታቸው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በግርማዊት እቴጌ አበረታችነት በስመ ጥሩ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በአስተማሪነትና በኋላም በዳይሬክተርነት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል። የእቴጌ መነን /ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ልዕልት ሂሩት ከተማሪዎች ይሁን ከትምህርት ቤቱ ሰራተኞች ጋር የነበራቸውን መግባባትና ሰው የማክበር ፀባያቸውን እስከ ዛሬ ድረስ ይናገራሉ። ለትምህርት ቤቱ መሻሻል ያደረጉት ለምሳሌ ያህል ለተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ወላጅ ለሌላቸውና የአቅም እጦት ለነበራቸው ነፃ ዩኒፎርምና ትምህርት፣ ተማሪዎች በግብረ ገብነት መታነጽ፣ ወጣት ሴቶች በዘመናዊ አስተሳሰብ እንዲታነፁ በተለይም አብሮ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በስፖርት በቴክኒክና በሥዕል ሥራዎች እንዲሰተፉ ያደርጉ የነበሩትን ማበረታታት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በከፍተኛ ትዝታ ከማስታወሳቸውም በላይ የልዕልቲቷ አርአያነት ወጣት ሴቶች ኢትዮጵያውያን በጊዜው ከነበረው የኋላቀር አስተሳሰብ ተላቀው እራሳቸውን ለከፍተኛ የዕውቀት ደረጃ ማድረስ እንዲችሉ የመንፈስ ጽናትንና በራስ መተማመንን እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ።

ልዕልት ሂሩት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶች በዓለም ደረጃ እንዲታወቁ በነበራቸው ምኞት ዛሬ በዓለም ዙሪያ አስደናቂ የህንፃ ሥራ ተብለው የሚቆጠሩት የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ታሪካዊነት በዓለም መንግሥታት የታሪክ ማህደር ውስጥ እንዲመዘገቡ ያደረጉ ታላቅ የሀገር ተቆርቋሪ ነበሩ። ልዕልቲቷ ይህንን ውጤት ያስገኙት ከሃምሳ ዓመታት በፊት እንደ ዛሬው መንገድና የእንግዳ ማረፊያ በሌለበት ዘመን በቦታው ተገኝተው በአንድ ደሳሳ ጎጆ ሰፍረው ለአንድ ዓመት ሙሉ የከተማውን ሰው በማስተባበርና እራሳቸው አንደኛዋ ተሳታፊ በመሆን ቤተክርስቲያናቱ ይዞታቸው ለታሪክ አስደናቂ ዓይን ማረፊያ እንዲሆን፣ እንዲሁም ላሊበላ ውሃ፣ መብራትና መንገድ እንዲገባለት አድርገዋል። ላሊበላን በወቅቱ የጐበኘ ናትናኤል ኬኒ የተባለ የናሽናል ጂኦግራፊ ጋዜጠኛ ስለ ልዕልት ሂሩት ሲጽፍ መልከ መልካሟ ዴሞክራሲያዊት ልዕልትይልና አብያተ-ክርስትያናቱ በሚታደሱበት ጊዜ ያደረጉትን ለመግለጽ፤ ከሠራተኛው እጅ መሣሪያውን ተቀብለው ራሳቸው እንዴት እንደሚሰራ ለማሳየት ወደኋላ የማይሉብሎ መዝግቦታል።

ልዕልትነታቸው 1957 . የተመሠረተው የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት የእድሳትና የታሪክ ጥበቃ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ባገለገሉበት ዘመን ከቤተ-ክህነት ከከተማው ሕዝብና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ለዓለም የአርኪዎሎጂስት ማኅበር በማመልከት እነኝህ ዛሬ ከስምንቱ አስደናቂ የዓለም ሥራዎች አንዱለመባል የበቁት ከአንድ ድንጋይ አካል የታነፁ አብያተ-ክርስቲያናት የታደሱበትን የገንዘብ እርዳታ አስገኝተዋል። ለላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ማደሻ የረዳው ዓለም አቀፍ ድርጅት ልዕልት ሂሩት በላሊበላ ፕሮጀክት የነበራቸውን ታላቅ ሚና በሚገባ መዝግቦታል። ልዕልት ሂሩት የላሊበላ ታሪካዊነት ለሀገር መመኪያና የዓለም ቱሪስቶች መሳቢያ ቅርስ መሆኑን በወቅቱ በማመናቸው ጎብኚዎች የሚያርፉበትን ሆቴል በአገር ባህል በማሰራት ሰባት ወይራዎችሲሉ ሰይመው ንብረትነቱን ለላሊበላ ድርጅት አስረከቡ። ከሆቴሉ የሚገኘው ትርፍ ለአካባቢው ልማት እንዲውል አድርገዋል።


ልዕልት ሂሩት ደስታ በኢትዮጵያ ወግና ማዕረግ መሠረት በልዕልት ተናኘወርቅና በራስ አንዳርጋቸው መሳይ ፈቃድ 1960 . ከክቡር ሜጀር ጄነራል ነጋ ተገኝ ጋር የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ፈጽመዋል። ልዕልትነታቸውም ባለቤታቸው በሐረር የሦስተኛ ክፍለ ጦር ኃላፊና በጎንደር የቤጌምድርና ሰሜን ክፍለ ሀገር አስተዳደር ተሹመው ሲሄዱ ከባለቤታቸው ጐን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ አገልግሎት ፈጽመዋል። 1967 . በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው አምባገነን ደርግ ልዕልት ሂሩትን ከእናታቸው ከልዕልት ተናኘወርቅና ከእህቶቻቸው ከልዕልት አይዳ ደስታ፣ ልዕልት ሰብለ ደስታና ልዕልት ሶፊያ ደስታ እንዲሁም በሀገር ከነበሩት መላው የንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር 14 ዓመታት ሙሉ ዓለም በቃኝ እስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ እንዲማቅቁ አድርጓቸዋል። ልዕልትነታቸው በዚያ አሰቃቂ ሁኔታ በእስር ላይ ሳሉ እጅግ የሚወዷቸው አያታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ወንድማቸው ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታና ሌሎች የቅርብ ቤተሰቦቻቸው በጨካኙ ደርግ በግፍ ተገድለውባቸዋል።

     ልዕልትነታቸው 1981 . ከእስር ከተፈቱ ጀምሮ ላለፉት 21 ዓመታት በእንግሊዝ አገርና በሀገር ቤት እየተመላለሱ ለወደጅና ለቤተሰብ አለኝታ በመሆንና ፍቅራቸውን በመለገስ አምላካቸውን እያመሰገኑ ዘመኑን አሳልፈው 84 ዓመታቸው በለንደን ከተማ (እንግሊዝ አገር) በሚወዷቸው እህቶቻቸው፣ በቤተዘመድና በወዳጅ ተከበው ሰኔ 18 ቀን 2006 . ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ሲል የህይወት ታሪካቸው ይናገራል።

                                                 በጥበቡ በለጠ ተፃፈ

No comments:

Post a Comment