ብራዚል በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ በሀገሯና በደጋፊዋ ፊት የምንግዜም
የከፋውን ሽንፍት ትናንት ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በጀርመን 7 ለ1 አስተናገደች፡፡ብራዚል እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጥር
በ1950 ባዘጋጀችው 4ኛው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በማራካኛ ስታዲዮም በኡራጓይ ከደረሰባትን ሽንፈት የከፋው አሳዛኝ ታሪክ በቤሎ
ሆርዞንቴ ስታዲዮም ተጽፏል፡፡
ጀርመን በ6 ደቂቃ ውስጥ 4 ጎሎችን በብራዚል መረብ አሳርፈዋል፡፡ ክሮስ እና ሹርሊ
ሁለት ሁለት እንዲሁም ሙለር፣ ክሎስ እና ከዲራ አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል፡፡የብራዚሉ አሰልጣኝ ስኮላሪ “በህይወቴ አስከፊው ሽንፍት ነው፤ ለዚህ ሽንፈት ሀላፊነቱን አኔ እወስዳለሁ” ብለዋል፡፡
የጀርመኑ አቻቸው ዋኪም ሎ በበኩላቸው “ቡድኔ ምርጥ ነበር፤
ብራዚሎች ግን ጨዋታውን በጫና ውስጥ ሆነው በመጫወታቸው ለዚህ የከፋ ውጤት ተዳርገዋል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ለአርጀንቲና ሊዎኔል ሚሲ፣ ለፖርቱጋል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ለብራዚል ኔማር እንዳላቸው ሁሉ ጀርመኖች ምርጥ ቡድን አላቸው”የእንግሊዙ አምበል ሰቴቨን ጀራርድ
አስተያይት ነው፡፡
የእግር ኳስ ተንታኙ አለን ሀንሰን “ላለፉት 50 ዓመታት ኳስ
ተመልክቻለሁ፤ የ1970ው የብራዚል ቡድን ምርጡ ሲሆን የአሁኑ ደግሞ ደካማው ነው” ብሏል፡፡የ5 ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ብራዚሎች
ያለ ኮከባቸው ኔይማር እና ያለ ቡድኑ አምበል ቲያጎ ጀርመንን መግጠም ከባድ እንደነበር ቢገመትም የተመዘገበው ውጤት ግን
የዘላለም በሽታቸው መሆኑ አይቀርም፡፡
የጀርመኑ ሚሎስላቭ ክሎስ በዓለም ዋንጫው ታሪክ 16ኛ ጎሉን በምሽቱ ጨዋታ በማስቆጠር የምንግዜም ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ለብቻው ተቆናጧል፡፡የብራዚል ደጋፊዎች በሀገራቸው የሆነውን ባለማመን በሀዘን ስሜት ተውጥው አምሽትዋል፡፡ የጀርመን ደጋፊዎች ደግሞ በተቃራኒው ደስታቸውን አጣጥመዋል።
No comments:
Post a Comment