Thursday, June 19, 2014

ባለሥልጣኑ ለሁለት የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሰጠ

    የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ ለሚሰራጩ ሁለት የግል ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሰጠ።ባለሥልጣኑ ፈቃዱን የሰጠው ዓባይ ኤፍ.ኤም 102 ነጥብ 9 እና ብስራት ኤፍ.ኤም 101 ነጥብ 1 ለተባሉ ሁለት የሬዲዮ ጣቢያዎች ነው። የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ገብሩ በፈቃድ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ኤፍ.ኤም ሬዲዮዎቹ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ማጎልበት  ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል።

   ለኅብረተሰቡ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ በማድረስ እንዲሁም በልማት ጉዳዮች ላይ በመስራት የአገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባልም ብለዋል። በተያዘው ዓመት በሀዋሳና በባህር ዳር አንዳንድ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ደግሞ አራት የግል ኤፍ.ኤም የሬዲዮ ጣቢዎች ፍቃድ ከጠየቁት መሀል፣የሚጠበቅባቸውን ብቃት ይዘው ባለ መቅረባቸው ለሁለቱ ብቻ ፈቃዱ መሰጠቱን ገልጸዋል። ፈቃዱን የወሰዱት ሁለቱም የኤፍ.ኤም ጣቢያዎች በቅርቡ የሙከራ ሥርጭት እንደሚጀምሩም አቶ ልዑል አመልክተዋል።


   የብስራት ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ባለ አክሲዮን አቶ መሰለ መንግሥቱ በበኩላቸው ብስራት ሬዲዮ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማስተላለፍ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የዓባይ ኤፍ.ኤም ባለ አክሲዮን አቶ ሀጎስ ኃይሉ ጣቢያው የአገሪቱን ሕገ-መንግስት እንዲሁም የብሮድካስት ሕጉን አክብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል

No comments:

Post a Comment