አሞስ እና መሀመድ አማን ለአሸናፊነት ሲፎካከሩ (ፎቶ – IAAF DL) |
አሜሪካ ዩጂን ውስጥ በሚገኘው የኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ የአትሌቲክስ
ስታዲዬም ቅዳሜ ምሽት (May 31, 2014) በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የአለም ሻምፒዮኑ መሀመድ አማን
በ800 ሜትር ሁለተኛ ደረጃን አግኝቶ ሲያጠናቅቅ፣ በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር ኢትዮጵያዊያኖቹ ሶፊያ
አሰፋ እና ህይወት አያሌው የበላይነታቸውን አስመስክረዋል።
በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የወንዶች 800 ሜትር ውድድር አለም ኢትዮጵያዊው መሀመድ አማን እና የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱና ከአንድ አመት በኋላ ከጉዳቱ አገግሞ እንደገና ወደውድድር የተመለሰው ኬኒያዊው ዴቪድ ሩዲሻን ፉክክር ለማየት ሲጓጓ ባልተጠበቀ ሁኔታ ቦትስዋናዊው ወጣት አትሌት ናይጅል አሞስ አንደኛ በመውጣት አሸንፏል። ናይጅል አሞስ ከመሀመድ አማን ጋር የውድድሩ ማብቃያ 10 ሜትሮች ውስጥ ባደረገው ፉክክር የበላይነቱን ወስዶ ርቀቱን የአመቱ ፈጣን ሰአት ሆኖ በተመዘገበ 1 ደቂቃ ከ43.63 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሲያሸንፍ፣ መሀመድ አማን በ 1፡43.99 ሁለተኛ፣ ሌላው ለረጅም ጊዜ በጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቆ የቆየው ሱዳናዊው አቡበከር ካኪ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ እና በርቀቱ የአለም የክብረወሰን ባለቤት ኬኒያዊው ዴቪድ ሩዲሻ 800 ሜትሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትሮች እስከሚቀሩት ድረስ የአሸናፊነት ፉክክሩ ውስጥ አብሮ ቢቆይም በተለይ የመጨረሻዎቹ 50 ሜትሮች ላይ ፍጥነቱን መጨመር ባለመቻሉ ሰባተኛ ደረጃን አግኝቶ ለማጠናቀቅ ተገዷል። በ800 ሜትሩ የዳይመንድ ሊግ ፉክክር ቦትስዋናዊው ናይጅል አሞስ እና ኬኒያዊው ሮበርት ቢዎት እኩል አራት ነጥቦችን በመያዝ ሲመሩ፣ ኢትዮጵያዊው መሀመድ አማን በ2 ነጥቦች ቀጣዩን ደረጃ ይዞ ይከተላል።
ባለድሏ ሶፊያ አሰፋ (ፎቶ – IAAF DL) |
በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል በርቀቱ የኦሎምፒክ እና የአለም
ሻምፒዮና የነሀስ ሜዳሊያዎች ባለቤት የሆነችው ሶፊያ አሰፋ በዩጂኑ የዳይመንድ ሊግ ውድድር የዘንድሮው የውድድር
አመት ፈጣን ሰአት ሆኖ በተመዘገበ 9 ደቂቃ ከ11.39 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ አንደኛ ደረጃን አግኝታ
ስታሸንፍ፣ ህይወት አያሌው 9 ደቂቃ ከ12.89 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቃለች። አሜሪካዊቷ
ኤማ ኮብሩን ሶስተኛ ሆናለች። በዚህ ርቀት እየተካሄደ ባለው የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን የመሆን
ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ሶፊያ አሰፋ እስካሁን ከተካሄዱት ውድድሮች 6 ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ
ስትመራ፣ አሜሪካዊቷ ኤማ ኮቡርን በ5 ነጥቦች ሁለተኛ፣ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ህይወት አያሌው በሶስት ነጥቦች ሶስተኛ
ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።
በዩጂኑ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከፍተኛ ፉክክር እንደሚታይባቸው
ተገምተው ከነበሩት ውድድሮች መካክለ አንዱ በሆነው የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊው የኔው አላምረው
ርቀቱን 13፡02.91 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ፣ ኬኒያዊው ካሌብ ኢንዱኩ የአመቱ ፈጣን ሰአት ሆኖ
በተመዘገበ 13 ደቂቃ ከ01.71 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በአሸናፊነት አጠናቋል። አንጋፋው ኬኒያዊ ኤድዊን ሶይ ሶስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣
ኢትዮጵያዊው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሀጎስ ገብረህይወት ለአሸናፊነት ከተገመቱት አትሌቶች
መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
በ5 ሺህ ሜትር እየተካሄደ ባለው የዳይመንድ ሊግ ፉክክር የኔው
አላምረው እስካሁን ከተካሄዱት ውድድሮች ስድስት ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን ይዞ ሲመራ፣ ኬኒያዊው ካሌብ
ኢንዱኩ በአራት ነጥቦች ሁለተኛ፣ ሌላው ኬኒያዊ ቶማስ ሎንጎሲዋ በሁለት ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ይከተላሉ።በቀድሞው አሜሪካዊ የአትሌቲክስ ስፖርቶች አሰልጣኝ ቢል ባወርማን
ስም በተሰየመው እና በየአመቱ ከዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ጋር ዩጂን ውስጥ በሚካሄደው የባወርማን ማይል ውድድር
የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው በ1500 ሜትር የአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት አማን ዎቴ
ሶስተኛ ደረጃን አግኝቶ ውድድሩን ጨርሷል።
አማን ዎቴ የማይል ውድድሩን የኢትዮጵያ ክብረወሰን ሆኖ
በተመዘገበ 3 ደቂቃ ከ48.60 ሰከንድ በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ሲያገኝ፣ ውድድሩን ጅቡቲያዊውአያንለህ ሱሌማን
ኬኒያዊው ሲላስ ኪፕላጋትን አስከትሎ በመግባት አንደኛ በመሆን አሸንፏል። አትሌቶች በእያንዳንዱ የዳይመንድ ሊግ ተሳትፈው በሚያመጣቸው
ውጤቶች መሰረት ነጥቦች የሚሰጣቸው ሲሆን በፍጻሜው እስከሚያደርጓቸው ውድድሮች ድረስ አንደኛ ለሚወጣ አትሌት አራት
ነጥብ፣ ሁለተኛ የሚወጣ ሁለት ነጥብ፣ ሶስተኛ የሚወጣ አንድ ነጥብ ይሰጠዋል።
የፍጻሜ ውድድሮቻቸው ዙሪክ ወይም ብራሰልስ ላይ በሚካሄዱት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች ደግሞ አንደኛ የወጣ 8 ነጥብ፣ ሁለተኛው አራት ነጥብ፣ ሶስተኛው ሁለት ነጥብ ይሰጣቸዋል። በ32ቱም የዳይመንድ ሊግ የውድድር አይነቶች በአጠቃላይ ድምር
በነጥብ የበላይ ሆነው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ዋንጫ ከመሸለማቸው በተጨማሪ
የ40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ።
በሌላ ዜና በቻይና በተደረገ የማራቶን ውድድር ኬንያዊያን አትሌቶች አንደና እና ሁለተኛ ሲወጡ ኢትዮጵያዊው ሳህለ ወርቅ ሶስተኛ ታሪኩ ጅፋር አምስተኛ ገዛኸኝ ግርማ ወጥተዋል፡፡ በሴቶች ኬንያዊት አትሌት አንደኛ ስትወጣ ሁለተኛ ኢትዮጵያዊቷ አጸዱ ባይሳ ሁለተኛ መስከረም አሰፋ ሶስተኛ ወጥታለች፡፡
ምንጭ፡- ቶታል 433
No comments:
Post a Comment