Thursday, August 22, 2013

የአሸንዳ እና የሻደይ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

 በሰሜን ኢትዮጵያ  ማለትም በትግራይ፣ ዋግና ላስታ ከሚከናወኑ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል እንደ እሽውላሌ፣ ጊጤ፣ ገና ጨዋታ፣ አሸንድዬ፣ ሙሻሙሾ እና ሆያ ሆዬ የመሳሰሉት በዐበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በነሐሴ ወር አጋማሽ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐለ ዕርገት/ፍልሰታ/ ጾም ፍች ጋራ ተያይዞ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል ማራኪና ልዩ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡

         ዛሬ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች እየተከበረ ያለው የፍልሰታ ለማርያም በዓል አንዱ ባህላዊ ገጽታው የአሸንዳ በዓል በመባል ይታወቃል፡፡ አሸንዳዬ በዓል ስያሜውን ያገኘው በነሐሴ ሳይዘራ ከሚበቅለው፤ አሸንዳ በመባል ከሚታወቀውና ቁመቱ 80-90 .ሜትር ከሚደርሰው ባለ አረንጓዴ ቀለም ተክል ነው፡፡ ልጆቹ አገልድመው ወይም አሸርጠው ያሸበሽቡበታል፡፡
   
  በአሸንዳ በዓል ዋዜማ እጅግ ደማቅ ባለአበባ የሻማ ቀሚስ የለበሱ፣ መቀነት የታጠቁ፣ ኮንጎ ጫማ ያጠለቁ፣ ፀጉራቸውን ቀጭን ሹሩባ (ጋምአሮ) የተሠሩና ሁለት ከበሮ የያዙ ከሃያ እስከ ሠላሳ የሚደርሱ የመንደር ልጃገረዶች ከየቤታቸው ተጠራርተው ይሰባሰባሉ፤ ከሁለት እስከ አራት የሚደርሱ እረኞችን አስከትለው ለአሸንዳ ቆረጣ የሚያደርጉትን ጉዞ ይጀምራሉ፡፡

አስገባኝ በረኛ
አስገባኝ ከልካይ 
እመቤቴን ላይ 
ጌታው አሉ ወይ አሉ ወይ 
አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ 
አሉ እንጂ ተዘንብሏል ጠጅካሉ በኋላ የአሸንድዬን ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡ 
        

የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች ከቤተሰብ ጀምሮ በሃይማኖት አባቶች  ጭምር ተቀባይነት ያለው ነፃነት የሚቀዳጁበት ነው፡፡ በሀገር ባህል ልብስ አምረው፣ በጌጣጌጥ ደምቀው፣ ቤት ለቤት የሚዘፍኑበት፣ የዕድሜ እኩዮቻቸው ከሆኑ ወጣት ወንዶች ጋር ስጦታ በመለዋወጥ የአፍላ ፍቅር አምሮታቸውን ለመወጣት የሚያስችል አጋጣሚ የሚያገኙበት የነፃነት ተምሳሌት ነው፡፡ አሸንዳ የተፈጥሮ በረከት በሚትረፈረፍበት፣ መጪው ዘመን የጥጋብ መሆኑ በሚበሰርበት የመስከረም ወር መዳረሻ አካባቢ የሚከበር በመሆኑ የብሩህ ተስፋ ተምሳሌት ነው፡፡ 

   
በቀድሞዋ ሮሃ በኋላ ላሊበላ የሚከበረው  ይህ በዓሉ÷ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በዋግ ሻደይ፣ በራያ ቆቦ    ስለል በይ በመባል ተቀራራቢነት ባላቸው ስያሜዎች ይጠራል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት ልጃገረዶች ከወገባቸው ላይ ሣር መሰል ቅጠል በማሰር ከቤት ቤት በመዘዋወር የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት የሚጫወቱት ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡
                                                                                                                          *        *       *
አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
እሽርግፍ እንደወለባ
አደይ አበባ አደይ አበባ
ነሽ ውባ ውባ

*        *       *
አደይቱ፣ መስከረሚቱ
መውደድ እንደሌሊቱ
  
*        *       *
አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ
ፍስስ በይ በቀሚሴ

  *        *       * 
  ቅድመ ዝግጅቱ የሚጀመረውም የፍልሰታ ጾም ሲገባ ጀምሮ ነው፡፡ ነጫጭ ልብሱን ለብሶ ከማስቀደሱና ከመቁረቡ በተጨማሪ በዚሁ ሰሞን ለአሸንድዬ በዓል አከባበር የሚኾኑ ባህላዊ አልባሳት ማለት ትፍትፍና ጥልፍ ቀሚስ፣ መቀነት፣ ልዩ ልዩ ጌጣ ጌጥ ለምሳሌ፡- ያንገት መስቀል፣ የጆሮ ጉትቻ፣ የእጅ ድኮት፣ የእግር አልቦ፣ ድሪ ካሎስ (ማተብ) አምባር፣ ጉርሽጥ (እንሶስላማሰባሰብና ማዘጋጀት፣ ልብስ ማጠብ፣ ፀጉር መሠራት. . .ወዘተ ከቅድመ ዝግጅቱ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
    በዓሉ ሲደርስ አለቃ ይመርጣሉ፤ አለቃዋ በመልካም ባሕርይዋ የተመሰገነች፣ የመምራትና የማስተባበር ችሎታ ያላት፣ በአካልና በዕድሜ ላቅ ያለች፣ የታወቀችና ልምድንም ያካበተች መኾን ይኖርባታል፡፡ ገንዘብ ያዥም ይመርጣሉ፤ የታመነች፣ ገንዘቡን በጥንቃቄ ይዛ ለተፈለገው የምታውል መኾን ይጠበቅባታል፡፡ ከዚያም በጥዑም ዜማ በሠናይ ቃና ይጫወታሉ፡፡ የጨዋታቸው ስንኞች ፍቅርን፣ ጀግንነትን፣ የሥራ ክቡርነትን፣ ሞያን፣ ውበትን. . .ወዘተ የሚያወድሱበት፣ በተለያየ ጣዕመ ዝማሬ የሚያሸበሽቡበት ነው፡፡ ባለቤቱ ሞቅ ያለ ስጦታ እንዲያበረክትላቸው ሲገፋፉትም፡-
ጌታው ስም ይሻል፤ ስም ይሻል
አንድ ብር እንኳ ጠፍቶ ያመሻል
  በሬ ከጋጡ ሞቶ ያመሻል
በማለት ጥሩ ስጦታ እንዲሰጣቸው ያደርጋሉ፡፡
          ሆያ ሆዬ የወጣት ወንዶች እንደኾነ ሁሉ አሸንዳዬ ደግሞ የወጣት ሴቶች ብቻ ነው፡፡ ሴቶቹም ኾኑ ወንዶቹ በበዓል ሰሞን ያገኙትን ገንዘብ በአንዳንድ ከተሞች ዛሬ ዛሬ እንደሚታየው ተከፋፍለው ለግል ጥቅማቸው አያውሉትም፤ ሴቶቹ ገበያ ወጥተው አስፈላጊውን ነገር በመግዛት የሚበላና የሚጠጣ ያዘጋጁበታል፡፡ ወንዶች ድሮ እስከ ሰንጋ አሁን ሙክት ይገዙበታል፡፡ ተባብረው ይደግሱበታል፡፡ ዳስ ጥለውና ድንኳን ተክለው በጋራ ኾነው የሰጣቸውን ሁሉ ይጠሩና ያበሉበታል፤ ያጠጡበታል፡፡ ላልመጣም ተሸክመው ይወስዱለታል፡፡ ይህ ሁሉ ኾኖ ድግሱ ሲያልቅ በመጨረሻ ለመጪው ዓመት በሰላምና በጤና እንዲያደርሳቸው ተመራርቀው፡-
                   ከርሞ እንገናኝ ባመት
             እናንተም ሳትሞቱ እኛም ሳንሞት ………..   ተባብለው ይለያያሉ፤ በዓሉም እንደተናፈቀ በዚሁ ይጠናቀቃል፡፡

No comments:

Post a Comment