Thursday, February 28, 2013

እጅግ የተከበሩ ሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ(1925 - 2004)

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 .. ምሽት ታላቁንና ዓለም አቀፋዊ ክብር ዝና ያገኙትን የሥነ ጥበብ ሰው እጅግ የተከበሩ ሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ያጡበት ዕለት ነው፡፡ ለስድስት አስርት አመታት ያህል በሥነ ጥበቡ ዘርፍ አውራ ሆነው የዘለቁት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በአፀደ ሥጋ ቢለዩም ሕያው የሚያደርጓቸውን ሥራዎቻቸውን ለትውልድ አውርሰዋል፡፡ከሰማንያ ዓመት በፊት በጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አንኮበር ከተማ ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 1925 .. ከእናታቸው ከእመት ፈለቀች የማታ ወርቅና ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ የተወለዱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማሩ በኋላ በወጣትነታቸው 1940 .. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አምርተዋል፡፡
     የማዕድን ምሕንድስናን ለመማር ቢያስቡም ስሜታቸውና ዝንባሌያቸው ወደ ሥነ ጥበቡ በማድላቱ ለንደን ውስጥ በሚገኙት የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ማዕከላዊ ትምህርት ቤትና በለንደን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ገብተው ኪነ-ቅብ፣ ኪነ- ቅርጽና  ኪነ-ሕንፃ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ 1947 .. እንደተመለሱም 22 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ለብቻቸው ያዘጋጁት ዓውደ ርዕይ ከፋሺስቱ ጦርነት ወዲህ የመጀመሪያው የሥዕል ትርዒት ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል፡፡ ከጥንታዊው የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ጋር ያስተሳሰራቸውን ልምድ ያገኙትም በተለይ በፈረንሳይ ፓሪስና በቫቲካን ጣሊያን አብያተ-መጻሕፍት የሚገኙትን የግእዝ ሥዕላዊ የብራና ጽሑፎችን በመረመሩበት ጊዜ ነው፡፡ 
    ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሰው  በቀድሞው ብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት ወመዘክር የሥዕል ስቱዲዮ በመክፈት ሥነ ጥበባዊ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቀዳሚው ታላቅ ሥራቸው አራዳ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙት ናቸው፡፡ በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ በቀለም ቅብ ሥዕሎችና ባለቀለም ከሆኑ ጠጠሮች፣ ክርክም መስተዋቶችና ከመሳሰሉት ተዋሕዶ በሞዛይክ በሸገነ ኪነት አሳምረው እንደጨረሱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ጽፈውታል፡፡ በሐረር ጦር አካዴሚ የሠሯቸው የኢትዮጵያ አራት የጦር ጀግኖች የኢዛና፣ ካሌብ፣ ምኒልክና ራስ መኰንን የሚታዩባቸው የመስተዋትና የመስኮት ሥዕሎች ናቸው፡፡
ይኸንን በሚሠሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር ከአምስት ዓመት በፊት እንዲህ አውግተው ነበር፡፡ በሐረር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና የተጫወቱ የቅርብና የጥንት ነገሥታት እንዲሠሩ ተፈልጎ አንድ ጣሊያናዊ ሠዓሊ አፄ ምኒልክና ራስ መኰንን፣ ከጥንቶቹ ጀግኖች ለአካዴሚ ተማሪዎች ምሳሌ እንዲሆን ናፖሊዮንና ታላቁ እስክንድርን ለመሣል ያቀርባል፡፡

አንተ ተምረህ የለ እንዴ ለምን አትሠራውም ብለው ጃንሆይ ይጠይቁኛል፡፡ የሥራ ሚኒስትሩን አዘው ሔጄ ጥናቱን አየሁ፡፡ የምኒልክና የራስ መኰንን ይገኛል፡፡ ታላቁ እስክንድርንና ናፖሊዮንን ግን ምን አመጣቸው? እኛ ከክርስትና በፊትና በኋላ የተነሱ ብዙ ጀግኖች አሉን፡፡ እነሱን መሥራት አለብን፡፡ ይኸ ‹‹ሰልፍድ ዊል ኮሎኒያሊዝም›› ስለሚሆን ኤዛናና ካሌብ እንዲሠሩ ለጃንሆይ ሐሳብ አቀረብሁ፡፡ ሁለቱም መሠረቶች ናቸው፡፡ ካሌብ የመርከብ ኃይላችን በነበረ ጊዜ እስከ ፋርስ ድረስ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ እንድሠራም ተደረገ፤ብለዋል፡፡ ሜትር አርቲስቱን በኪነ ቅርጽ (ቅርጻ ቅርጽ) ሙያቸው አግዝፎ የሚያሳያቸው በሐረር ከተማ እምብርት ቆሞ የሚታየው ራስ መኰንን በፈረስ ላይ ሆነው የሚያሳየው ሐውልት ነው፡፡ 

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ መግቢያ ላይ ‹‹አፍሪካ ያኔ፣ አፍሪካ አሁን እና አፍሪካ ወደፊት›› የሚለው የመስታወት ላይ ሥራቸው ዓለም አቀፋዊም አድናቆት ብቻ ሳይሆን ከፍ ላለው ‹‹ወርልድ ሜዳል ኦፍ ፍሪደም›› የተሰኘውና ከአስርት ዓመታት ወዲህ የተመሠረተውን ሽልማት ተጎናጽፈዋል፡፡ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ በሥነ ጥበብ ሥራቸው ውስጥ ስለ ሰው ልጅ የመንፈስ ነፃነት፣ የሰው ልጅ የሌላ ዓይነት መጥፎ ሐሳብ ባርያ አለመሆንን፣ የሰው ልጅ ወደ ሰላምና ወደ አንድነት የሚመራ በአንድ ሥራ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሥራ ውስጥ ይታያል ብለዋል፡፡ 
 በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ ክፍል ውስጥ ጐብኝውን ከፊት ለፊት የሚቀበለው ዓለም አቀፋዊ ዝናን ያተረፈው የመስኮቶች መስታወት ቅብ ሥዕል ነው፡፡ የጥበቡ ሐያስያን እንደጻፉት፣ 150 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የተንጣለለው ሥዕል በሦስት ሰሌዳዎች ያለፈውን የአፍሪካ አሳዛኝ ታሪክ፣ የወቅቱን ትግልና ለወደፊቱም አፍሪካ ለአንድነት ያላትን ፍላጎትና ጉጉት ያሳያል፡፡ ከሌሎች ሥዕሎቻቸው መካከልየመስቀል አበባ” (1952)እናት ኢትዮጵያ” (1956)ሰሜን ተራራ ሥርቀተ ፀሐይ” (1961)የኢትዮጵያ ድል” (1970) ይጠቀሳሉ፡፡      

    
      አፈወርቅ 32 ዓመታቸው የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) የሥነ ጥበብ ሽልማትን 1957 .. አግኝተዋል፡፡ በወቅቱ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኪነ ጥበብ ሽልማት›› የሚል መጠርያ ያለውን ሽልማት ከንጉሠ ነገሥቱ በተበረከተላቸው ጊዜ የአቶ አፈወርቅ ተክሌ ልዩ ልዩ ሥራዎች በአራት ክፍለ ዓለሞች በመሰራጨታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቱ አርቲስት ስም ለመታወቅ በቅቷል፡፡ አቶ አፈወርቅ ተክሌ ከፍ ያለ ችሎታና ዲስፒሊን ያላቸው አርቲስት ከመሆናቸውም በይበልጥ፣ ባበረከቷቸው የሥዕል ብዙ ሥራዎች ክፍለ ዓለማቸውን አጉልተው ስለገለጹና በኢትዮጵያ በዘመናዊ የአርት ቴክኒክ መሥራት ከጀመሩት ከቀዳሚዎቹ አንዱ ስለሆኑ የቀኃሥ ሽልማት በኪነ ጥበብ ሰባት ሺሕ ብር ከወርቅ ኒሻንና ዲፕሎም ጋር እንደተሰጣቸው ተበስሯል፡፡  ለሽልማት ድርጅቱ መጠንሰስ አንዱ ባለታሪክና ወትዋች እርሳቸው መሆናቸውንም መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ 
    “በአገራችን አምስት ማዕረግ ያላቸው ሰባት ኒሻኖች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁሉም የጦር ሜዳና የሃይማኖት ናቸው፡፡ በሥነ ጥበብ የለንም፡፡ በአገራችን ሥነ ጥበብ ረዥም ታሪክ ያለው ስለሆነ በግርማዊነትዎ ዘመነ መንግሥት እንደ ፀሐይ የሚያበራ ሽልማት መሰጠት አለበት፡፡ እንደ ኖቤል ያለ ለአርቲስቶች ሽልማት መስጠት አለብዎት፡፡ እኔ ዲዛይኑን ለመሥራት ዝግጁ ነኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የኒሻን ዓይነቶች አንዱ መሆን አለበት፤ስላሏቸው ለመቋቋም ችሏል፡፡  የሥነ ጠቢቡ ትሩፋት እንግሊዝ ውስጥም ይገኛል፡፡ ርእስ ጠበብት ለመሆናቸው ሜትር አርቲስት፣ የዓለም ሎሬት የሚለውን ከእጅግ የተከበሩ ጋር ያስቀጸለላቸው የስኬታቸው ጫፍ መድረስ ነው፡፡ ከትውፊት የጠለፉት ሌላም መጠርያ አላቸው ‹‹አባ መብረቅ›› ‹‹አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ (Alpha Son of Thunder)፡፡ የራሳቸው የሆነ ዓርማም አላቸው፤ በአውቶሞቢላቸውም ሆነ በቪላቸው ላይ ተለጥፎ ይታያል፡፡
 
አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ የሚለው መጠርያ መነሻ አለው፡፡ እንደርሳቸው አገላለጽ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ጠባቂመልአክያሉት ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድን ነው፡፡ አባቴ አዳኝ ነበሩ፡፡ በአገራችን ባለው ልማድ አዳኝ የፈረስ ስም ይሰጠዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ለእሳቸው የፈረስ ስም ይሰጣል፡፡ እንደሳቸው ሁሉ ለእኔም ወልደ ነጎድጓድ፣ አባ መብረቅ የፈረስ ስም ነው፡፡ ይህንን አቀናጅቼ በአርማዬ ላይ ሻምላው መብረቁን ሲያቋርጥ የሚያሳይ አለው፡፡ ሻምላ የእኔ ተወዳጅ ስፖርትና እንግሊዝ ሳለሁ ሁለት ሽልማት ያገኘሁበት ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ የዓለም ሎሬት ስባል የወይራ ጉንጉን ከራስጌ ላይ አደረግሁ?” በማለት መግለጻቸው ይወሳል፡፡  
    ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለመጪው ትውልድ የሚሆን ተለጣጣቂ (ተከታታይ) ሥዕሎችና ቅርጾችንም ነድፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) መባቻ ላይም ይፋ አድርገውታል፡፡  እነርሱም ከሚሌኒየሙ ጋር የተያያዘ አዲስ አበባ በትልቅ አደባባይ ላይ የሚያርፍ የሐውልትና መስታወት ሥራ፣ ሁለተኛው የአክሱም ሐውልት ወደ ኢትዮጵያ መመለስን የሚያመላክት በዓድዋ ተራሮችና በአክሱም መካከል የሚሠራ ሐውልት ዲዛይንና ሦስተኛው የአፍሪካን ባህላዊ ትስስርና አንድነትን የሚያሳይ ከአኅጉሪቱ በአንዱ አገር የሚተከል ናቸው፡፡ 
ኢትዮጵያንና አፍሪካን የሚወክሉ አዳዲስ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለወርልድ ፎረም ፌዴሬሽን በዋሽንግተን ዲሲ 2001 . ሰኔ መጨረሻ ላይም አቅርበውት 21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታላቅ አርቲስት በመባል ከተመረጡት መካከል የምርጦች ምርጥ ‹‹ ግሬተስት ማን›› ክብርን አግኝተውበታል፡፡ ሜትር አርቲስቱ የሥነ ሕንፃ ትምህርታቸው ትሩፋት የሆነው ስቱዲዮና መኖርያቸውን ያካተተው ‹‹ቪላ አልፋ›› ይጠቀሳል፡፡ የአክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደርና ሐረርን ሥነ ሕንፃ የያዘውን ቪላ አልፋ ዲዛይኑን የሠሩትም እሳቸው ናቸው፡፡ ‹‹የእኔ ሕልም ብዙ ሥራ ሠርቼ ሳልፍ ለአገሬ የመጀመሪያው ኮንቴምፖራሪ [የዘመኑ] አርቲስት ስቱዲዮ የሠራ ነው ተብዬ ጉዞዬን ስጨርስ ተማሪ ቤት አድርጌ ለመፍጠር ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ 
    የባህል ሚኒስቴር የሥነ ጥበባት ከፍተኛ አማካሪ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የቦርድ ሥራ አስፈጻሚ (1976-84) የነበሩት አንደበተ ርቱዕ አፈወርቅ  ቪላ አልፋን በገነቡበት ጊዜ ከቤተ መንግሥት ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸው ነገር ነበር፡፡ ቦታውን ሳሠራ የጃንሆይ መረጃዎችኧረ ይህ ልጅ ጎንደርን የመሰለ ሕንፃ እየሠራ ነው፤ ምን አስቦ ነው ይሏቸዋል፡፡ ጃንሆይም ቤተ መንግሥት ጧት እጅ ልነሳ ስሄድምንድን ነው የጎንደር ነገር የምትሠራው?’ አሉኝ፡፡ ገባኝና እኔ በሕይወቴ የምመኘው የአርቲስቶች ልዑል ለመሆን እንጂ ለመንገሥ ፍላጎት የለኝም አልኳቸው፤ያሉትም አይረሳም፡፡ ለስድስት አሠርት አቅራቢያ ያህል በሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ገናና የነበሩት ሎሬት አፈወርቅ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት 1956 .. በሥነ ጥበብ የተሸለሙትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀዳጅተዋል፡፡  
                                         ምንጭ ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment