ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በ96
ዓመታቸው መጋቢት 9፣2012ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት
ተለዩ። ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ(Hamlin
Fistula Ethiopia) የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በማቋቋም ከ60 አመታት በላይ የፌስቱላ ህክምናን በመስጠት ይታወቃሉ። የማህጸን ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን ከ65 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊ በፌስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ከስነልቦናዊ እና አካላዊ ቁስለት ለማዳን ችለዋል።ዶክተር ካትሪን ሀምሊን
በትውልድ አውስትራሊያዊ ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ባደረጉት ውለታ (የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ችግርን በመቅረፋቸው) የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት እና ከአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል።
አዋላጆችን ለማሰልጠን ከሀገራቸው አውስትራሊያ የመጡት ዶ/ር ካትሪን
ሀምሊን እዚሁ ኢትዮጵያ በመቅረት ለመጀመሪያ ጊዜ የፊስቱላ ህክምና ብቻ የሚሰጥባቸው ተቋማትን በመመስረት ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡
በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ በመላ ሀገሪቱ ወደ 6 የሚጠጉ የፊስቱላ ህክምና አገልግሎት መስጫዎችን አቋቁመዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፣በባህር ዳር እና በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች እና ክልኒኮች ጋር የተጣመሩ ከአምስት መቶ ሀምሳ በላይ የሕክምና ባለሙያዎችን ያፈራው የዶ/ር ሪግራንድ እና ዶ/ር ካትሪን የፊስቱላ መታሰቢያ ተቋም በሚያደርጋቸው ምግባረ ሰናይ ተግባራት በአውስትራሊያ እና በተለያዩ አለማት ከፍተኛ እውቅና ለማግኘት ችሏል።
“የሴቶቹ ሕይወት ሲለወጥና ሲታደስ አያለሁ፡፡ ሁሌም ሃሳቤ ከነሱ ጋር ነው፤ ህመማቸው ህመሜ ነው፡፡ ይሄ ደሞ የምችለውን እንድሰራና እንዳደርግ ይገፋፋኛል፡፡ እስከዛሬ እዚህ የኖርኩትና አሁንም እዚህ የምኖረው በዚህ ምክንያት ነው” ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን
60 አመት መሉ ያለመታከት በፊስቱላ ችግር የሚሰቃዩትን አከሙ::አብረው ጥልፍ አየጠለፉ፣ የእጅ ሙያ እያስተማሩ የስጋ ብቻ ሳይሆን በደረሰባቸው መገለል እና መሸማቀቅ የመንፈስ ስብራት የደረሰባቸውን እህቶች በሩህሩነት እና ጥልቅ ፍቅር በተሞላ እንክብካቤ አዲስ ህይወት ሰጡ፡፡ የኔ ጥረት ብቻ አይበቃም ብለው ተጣጥረው አዋላጆችን የሚያሰለጥን ኮሌጅ ከፍተው ብዙዎችን ባለሙያ አደረጉ፡፡ ተቆጥሮ የማያልቅ ደግነት፣ የሙያ ፍቅር እና ርህራሄ የታደሉት ሀምሊን ለኢትዮጵያ ብዙ ደክመዋል፡፡ እድሜ
ያልገደባቸው ዶ/ር ካትሪን የእርጅና ድካም ሳያሸንፋቸው ሲሰሩ ነበር፡፡
“በእኔ አድሜ ፊስቱላ ላይጠፋ ይችላል ፣ በእናንተ እድሜ ግን ይቻላል“ ሲሉም በአንድ ወቅት ዶ/ር ሀምሊን ለወጣቶች ተናግረው ነበር፡፡ በተጨማሪም
ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን “ ሰው ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ስለሌላውም እየተጨነቀ እንዲኖር በሚያስችል
መልኩ የተቃኘውን ኢትዮጵያዊ አኗኗር ” ያደንቁም ነበር፡፡
በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ በህመማቸው ወይ በሌላ ምክንያት ከተገፉ፣ከተገለሉ እናም በዚህ ምክንያት ተስፋቸው ከጨለመ ወገኖች ጋር ከመቆም የላቀ ሰብአዊነት የለም፡፡ መልካም ተግባር ሁሌም ከመቃብር በላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ እና የሴት ልጆቿ የክፉ ቀን ባለውለታዎች የሆኑት ዶ/ር ካትሪን እና ሟቹ ባለቤታቸው ዶ/ር ሪግራንድ በተግባር አስመስክረዋል። ለሦስት አመታት የሥራ ኮንትራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከስድሳ አመታት በላይ ጉልበታቸውን ፣እውቀታቸውን ፣ ገንዘባቸውን እና ህይወታቸውን ጭምር ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ በገጸ በረከት ያበረከቱት ዶ/ር ካትሪን እና ባለቤታቸው አንድ ወንድ ልጅ ያፈሩ ሲሆን የአራት ልጆችም አያቶች ለመሆን በቅተዋል።
ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን የሰጡ ታላቅ እናት …..!!!
ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን የሰጡ ታላቅ እናት …..!!!
No comments:
Post a Comment