Friday, August 16, 2013

ሀጎስ – በአለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት


   በሩሲያዋ ሞስኮ ከተማ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያዊው ሀጎስ ገብረህይወት በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ብሪታኒያዊው ሞ ፋራህን በመከተል እና ኬኒያዊውን የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት አይዛያ ኮይችን በመቅደም ርቀቱን 13 ደቂቃ ከ27.26 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቆ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል። ልጅ እያለ ከአትሌቲክስ ይልቅ ለእግርኳስ ትልቅ ፍቅር እንደነበረው የሚነገርለት ሀጎስ ገብረህይወት ወደሩጫ ትኩረቱን ያዞረው የ15 አመት ታዳጊ ወጣት እያለ ነበር። “እግርኳስ ዛሬ ላለኝ ጽናት ትልቅ አስተዋጾ አበርክቶልኛል” የሚለው ሀጎስ በተለይ በአለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን ማግኘት የቻለው በአለፈው አመት ክረምት ወር ላይ ፓሪስ ውስጥ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ 5 ሺህ ሜትር ውድድር የአለም ወጣቶች ክብረወሰንን በሰበረ 12:47.53 ጊዜ በመሮጥ ካሸነፈ በኋላ ሲሆን፣ ይህ ሰአት በርቀቱ በታሪክ ሰባተኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ የተመዘገበ ነው።
 “ለወደፊት ይህ ልጅ የመሮጫው ትራክ ላይ ምን ድንቅ ነገር ይሰራ ይሆን?” ተብሎ ሲጠበቅ በአለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ አሜሪካ ቦስተን ውስጥ በተካሄደው የቤት ውስጥ የ3 ሺህ ሜትር ውድድር ርቀቱን 7:32.87 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ የአለም የወጣቶች ክብረወሰንን በርቀቱ ከሰበረ ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ከትራክ ውድድሮች ውጪ ባሉ ሩጫዎች ውጤታማ ለመሆን በሚል አላማ ሀጎስ ትኩረቱን ወደአገር አቋራጭ ውድድር በማድረግ የሜዳሊያ አደኑን ጀመረ።

    በአለፈው መጋቢት ወር በፖላንድ አስተናጋጅነት በተካሄደው 40ኛው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በአስደናቂ ብቃት አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ሀጎስ ገብረህይወት በረጅም ርቀት ሩጫ ቀጣዩ ድንቅ አትሌት ይሆናል በሚል ትኩረቶች ወደእርሱ እንዲዞሩ አደረገ። በተለይ የስፖርቱ ባለሞያዎች እና ተንታኞች ለሀጎስ ገብረህይወት ያላቸው አድናቆት ሊጠነክር የቻለበት ዋናው ምክንያት በፖላንዱ የአለም አቋራጩ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን 8 ኪሎ ሜትሩን ሮጦ ለመጨረስ የወሰደበትን 21 ደቂቃ ከ 04 ሰከንድ የሆነ ጊዜ የአገር አቋራጭ ውድድር ንጉስ የሆነው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ቀነኒሳ በቀለ እ.አ.አ በ2001 ዓ.ም ቤልጂዬም ውስጥ በተካሄደው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በውድድሩ የመጀመሪያው የሆነው የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያገኝ ርቀቱን ሮጦ ለመጨረስ የወሰደበትን 25 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ ጋር በማነጻጸር ነው።

      በርግጥም ሀጎስ ርቀቱን ከቀነኒሳ አንጻር ፈጥኖ በመሮጥ ከመጨረሱ በተጨማሪ ቀነኒሳ ያን ጊዜ የሮጠው ርቀት እንደ አሁኑ 8 ኪሎ ሜትር ሳይሆን 7.7 ኪሎ ሜትር በመሆኑ ነው። አንዳንዶች ቀነኒሳ የሮጠባት የቤልጄዬሟ የጠረፍ ከተማ ኦሽቴንድ በጊዜው የነበረው የመሮጫው ጎዳና ጭቃማ መሆኑ እና አሰቸጋሪ እንደነበር ቢገልጹም፣ ሀጎስ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነባት የፖላንዷ ቤድጎይሽት ከተማም ውድድሩ በተካሄደበት ወቅት የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ በእያንዳንዱ ዙር መጨረሻ ላይ የነበረው ዳገት ውድድሩን ፍጹም ፈታኝ እንዳደረገው ይመሰክራሉ።

    ሀጎስ በዘንድሮው የውድድር አመት በተለያዩ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችም – በተለይ በ5 ሺህ ሜትር – በተደጋጋሚ ውጤታማ የሆነ ሲሆን፣ ለአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወደሞስኮ ሲሄድ ብሪታኒያዊው ሞ ፋራህን ይፎካከራል በሚል ቀዳሚ ግምት የተሰጠው አትሌት ነበር። ምንም እንኳን ሀጎስ የ14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በብር ሜዳሊያ ቢያጠናቅቅም ለወደፊት ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆን እንደሚችል ቅድሚያ ግምት ከሚሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑን አስመስክሯል።
                                                                           
                                                                                              ምንጭ ፡-    ቶታል 433 /ፍሰሀ ተገኝ/

No comments:

Post a Comment