Friday, September 19, 2014

ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ከዚህ አለም በሞት ተለየ::


   ተዋናይ፣የፊልም ዳይሬክተር፣መምህር፣ የዳንስ ጥበብ ባለሙያ ፣የማስታወቂያ ባለሙያና አማካሪ ነበር ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ፡፡ በተለያዩ የመድረክ ስራዎች በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ሀገር መድረኮች ላይ በብቃት በመጫወት ይታወቃል፡፡ በተለይም በተማሪነት ዘመኑ የዊሊያም ሼክስፒርን ስራዎች ይጫወት ነበር፡፡

   
  የቴአትር ስራዎችን ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው በብቃት መጫወት የጀመረው፤ ከአማርኛ ተውኔቶች በተጨማሪም በወቅቱ በእንግሊዘኛ በሚዘጋጁ የተውኔት ስራዎች ውስጥም በብቃት ተውኗል፡፡ በአሜሪካ እና በተለያዩ ሀገራትም በትወና ችሎታው የተለያዩ ልማቶችን አግኝቷል፡፡

   በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ እጅግ በርካታ ቴአትሮችን ሠርቷል ከእነዚህም መካከልምጴጥሮስ ያቺን ሰዓትኦቴሎእናት አለም ጠኑእናቴዎድሮስይጠቀሳሉ። የሲሳይ ንጉሱን ልቦለድ /ግርዶሽ/ ወደ ፊልም በመቀየር አዘጋጅቷል፤ ተውኗል፡፡ የሸክስፒርን ስራዎች በተለይም በጫንያለው ወልደጊዮርጊስና ቴዎድሮስ ተሰማ የተተረጎመውን ተጫወቷል፡፡ 

   በፀጋዬ ገብረ መድህን ስራዎች በዘመኑ እጅግ ድንቅ ብቃት ያሳየባቸውንየእናት ዓለም ጠኑእናሀሁ በስድስት ወርቴአትሮች ላይ የተለያዩ ገፀባህሪያትን ወክሎ በብሔራዊ ቴአትር ተውኗል፡፡ ሀምሌትን አዘጋጀቷል፡፡ ከፍቃዱ ተክለማሪያም በፊትቴዎድሮስንሆኖ ተወኗል፡፡

   በቀድሞው ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩንቨርስቲ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን በትወና /አክቲንግ/ በአሜሪካን አገር /ሚኒሶታ/ Minnesota University ሁለተኛ ዲግሪውን ተምሯል፡፡ትምህርቱንም በከፍተኛ ማእረግ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ በቀድሞው ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን/ የአሁን ኢቢሲ/ “ፊት ለፊትበተሰኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ይታወቃል፡፡


   አዲስ አበባ የተወለደውና ሆለታ ያደገው ሀይማኖት እስከቅርብ ቀን ድረስ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ(በተጋባዥመምህርነት) እንዲሁም በራክማኖቭ /ቤት ሲያስተምር ነበር።ሙዚቃ ይወዳል ይላሉ የቅርብ ጓደኞቹ፡፡ጊታርም በድንቅ ብቃት ይጫወት እንደነበር ይመሰክሩለታል፡፡

 
   በሲዲ ያልተለቀቁ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች እንዳሉትም ተጠቁሟል፡፡ ከምንም በላይ ግጥም በማራኪ አቀራረብ በማንበብ ይወደድ የነበረው አነጋፋው አርቲስት ሀይማኖት ዓለሙ በመድረክ መምራትም ተወዳጅ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማስታወቂያው ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራም ነበር፡፡በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን አዳዲስ ድራማዎችን በባለሙያዎች በተዋቀረ ካውንስል ለማስገምገም ከተመረጡ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ 

   ለሁለገብ ባለሙያው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች እና አድናቂዎች መፅናናትን ተመኘሁ፡፡

No comments:

Post a Comment