Wednesday, September 17, 2014

ኮንሶ / የታታሪነት ተምሳሌት /


የእርከን ጥበብ እንዲህ እንደዛሬው ሳይዘምን፣ በዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎች ስለ አፈር እና ውሃ ያላቸው እውቀት ሳይልቅ የዚህ ጥበብ ሰርቶ ማሳያ ማዕከል ነበር፡፡ በግብርና የሚተዳደረው የኮንሶ ህዝብ የግብርና ስራ ስልቱ ጥበብን የተሞላ መሆኑ እና የሚጠቀምባቸው ሀገር በቀል እውቀቶች 500 ዓመታትን የተሻገሩ መሆናቸው የኮንሶ መልክዓምድርን በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስችሎታል፡፡ ይህ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ ባህላዊ ምልክዓምድር 23,000 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው ፡፡ 

  ባህላዊ መልክዓምድሩ በውስጡ የተለያዩ በባህላዊ ዘዴ የተሰሩ እርከኖች፣ በካብ ታጠሩ መንደሮች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ዋካ እተባሉ የሚጠሩ የእንጨት እና የድንጋይ ሀውልቶች እንዲሁም ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ኩሬዎች / ሀርታዎችን/ አካቶ ይዟል፡፡ የኮንሶ የድንጋ እርከኖች በዓይነታቸውም ሆነ ባስቆጠሯቸው ዘመናት ከፍተኛ እሴትን የያዙ ሲሆን የማህበረሰቡ የህይወት መሰረትም ሆነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡

  ሁለንተናዊ እሴቶቹ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘው የኮንሶ ህዝብ ተፈጥሮን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ይታወቃል፡፡ በዚህም ከተፈጥሮ ጋር ባደረገው የረጅም አመታት ትግል መልክዓምድሩንም ሆነ ማህበረሰቡን የሚጠብቅበት እና የሚያስተዳድርበት ባህላዊና ትውፊታዊ ስርዓት ለመዘርጋት ችሏል፡፡


  የኮንሶ የመሬት አቀማመጥ ተዳፋት እና ተራራማ ሲሆን በከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ለምነቱን ያጣና በአካባቢውም ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ የሰው ልጆች ኑሮ መስርተው ይኖሩበታል ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡ ይሁንና ታታሪው የኮንሶ ህዝብ ይህንን ወጣ ገባ የበዛበትን እና በአፈር መሸርሸር ምክንያት የተጎዳውን ምልክዓምድር በተፈጥሮ በተቸረውና ባካበተው ጥበብ አካባቢውን ለኑሮ ምቹ እንዲሆን በማድረግ እየኖረበት ይገኛል፡፡  


  ኮንሶዎች ከድንጋይ ካብ በተገነቡ መንደሮች /ፓሌታዎች/ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ መንደሮች ለሁሉም ነገር ስትራቴጂካዊ በሆነ አመቺ ስፍራ ላይ የተገነቡ ናቸው፡፡ መንደሮቹ እስከ 6 ዙር በተገነቡ የደረቅ ካብ /ማለትም በሲሚንቶ እና በጭቃ/ ባልተሰሩ ግንቦች የታጠሩ ናቸው፡፡ የኮንሶዎች ቤት በእንጨት፣ በሳር እና በጭቃ ይሰራል፡፡ 

   ኮንሶዎች እንደቆጥ አድርገው የሚሰሩትን ጎጆ ፓፍታ ብለው ይጠሩታል፡፡ ወጣቶች በዚህ ፓፍታ ውስጥ ይውላሉ፣ ያድራሉ፡፡ የፓፍታው የታችኛው ክፍል ሙሉ በሙሉ ክፍት ሆኖ የተሰራ ሲሆን ማንኛውም በአካባቢው የሚደርሱ አደጋዎችን /ችግሮችን/ ወጣቶቹ በፍጥነት ከቆጣቸው ላይ ወርደው ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ አንድ ፓሌታ /አምባ መንደር/ በውስጡ ከሁሉም የኮንሶ ጎሳዎች የተቀላቀሉ ከ400 በላይ የሚሆኑ የአባወራዎች ግቢ ያሉት ሲሆን ራስ ገዝም ነው፡፡ ማንኛውም ባህላዊ የአስተዳደር ጉዳይ በቤተሰብ፣ በጎሳ፣ በካንታ/ጎረቤት/ እና በፓሌታ እንዲሁም በቀበሌው የበላይ አስተዳደር ይፈታሉ፡፡ ባህላዊ አስተዳደር እና የውሳኔ አሰጣጥ ዘይቤያቸው በአብዛኛው በእውነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ውሳኔዎቻቸው ተፈፃሚነት እና ተቀባነት አላቸው፡፡


ሞራዎች /የመሰብሰቢያ አደባባዮች/


  በእያንዳንዱ ባህላዊ ከተማ /አምባ መንደራት/ ውስጥ በርካታ ሞራዎች /የመሰብሰቢያ አደባባዮች/ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሞራዎች የአካባቢው ማህበረሰብ ባህላዊ እና ማህበራዊ ትስስሩን የሚያንፀባርቅቸው ማዕከላት ናቸው፡፡ በአምባ መንደራቱ በርከት ያሉ ሞራዎች ያሉ ሲሆን አንዱ ከሌላው ጋር ለሰዎች እና ለከብቶች ተብለው በተዘጋጁ ጠባብ መንገድ ተያይዘዋል፡፡ መንገዶች ውስብስብ ያሉና ለመለየት አስቸጋሪ በመሆናቸው ያልታወቀ ሰው /ሌባ/ ቢገባ በቀላሉ ይያዛል፡፡
    
  እነዚህ ሞራዎች የክብር፣ የማህላ፣ የመዝናኛ እና የህዝባዊ ስብሰባ ማከናወኛ በመባል ይከፈላሉ፡፡ ሞራ ዳውራ /የክብር ሞራ/ የሚባለው አንድ አምባ መንደር ሲመሰረት አብሮ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ሞራው ትልቅ አክብሮት የሚቸረው ሲሆን የጀብድ ስራዎችን ለሰሩ ጀግኖች መዘከሪያ ትክል ድንጋዮች /እንጨቶች/ ይቆሙበታል፡፡ የመዝናኛ ሞራዎችን ደግሞ ከህፃነት እስከ አረጋዊያን ያሉ ሰዎች ገበጣ እና ሌሎች ባህላዊ ጨዋታዎችን ያደርጉባቸዋል፡፡

  ባህላዊ የዳኝነት እና የእርቅ ስነ ስርዓትን ለማከናወን፣ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ እንዲሁም አዳዲስ አዋጆችን እና ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ሞራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከኅብረተሰቡ ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈፀሙ የውግዘት እና የማህላ ስነ ስርዓቶች ይከናወኑባቸዋል፡፡

  በኮንሶዎች ዘንድ በየ18 ዓመቱ የትውልድ ለውጥ እና የስልጣን ሽግግር ይደረጋል፡፡ የስልጣን ርክክብ ማከናወኛ፣ የትውልድ መቁጠሪያ እንጨቶች /ኦላይታዎች/ እና የጀግኖች መዘከሪያ ትክል ድንጋዮችም በየሞራዎቹ ላይ ይተከላሉ፡፡

  
  በብሄረሰቡ ባህል ለጎሳ መሪዎች እና በህይወት ዘመናቸው የጀግንነት ስራ ለሰሩ ሰዎች መታሰቢያነት ከእንጨት እና ከድንጋይ ተጠርበው የሚቆሙት ሀውልቶች ዋካ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ዋካዎች ሲሰሩ የተለያዩ መረጃዎች እንዲሰጡ እና ስለ ሰውዬው ማንነት እንዲገልፁ ተደርገው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment