Tuesday, September 23, 2014

አንጋፋው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ፡፡

 
   በ68 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ በዛሬው ዕለት መስከረም 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቤተሰቦች፣ የጥበብ ወዳጆች፣ አድናቂዎቹ በተገኙበት የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
  በ1939 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደው አርቲስት ኃይማኖት ዓለሙ ዘመናዊ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት አጠናቆ የከፍተኛ ትምህርቱን በአሜሪካ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪውን በመከታተል በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቋል። ሁለተኛ ዲግሪውንም በክብር እዚያው ይዟል። በጎርጎሮሳውያኑ 1988 በተካሄደ የሼክስፒር ድርሰቶች አተዋወን ላይ በመወዳደር “የኢራ አልድሪጅ” ሽልማትን አግኝቷል። በ1989 በሎስ አንጀለስ የአል ካሚኖ ዩኒቨርሲቲ የፋኩልቲ አባል በመሆን የሼክስፒርን ተውኔቶች አስተምሯል፣ አዘጋጅቷልም።
   በሀገር ወስጥ ደግሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን /በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን/ “ፊት ለፊት” የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን ሲያልግል በውጭ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች አገልግሏል። የ3 ልጆች አባት የነበረው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ፣ ባደረበት ሕመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ68 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር፡፡
                                          ምንጭ ፡- ኢብኮ/EBC/

No comments:

Post a Comment