Saturday, September 13, 2014

እንቁጣጣሽ /አዲስ ዓመት/


  በንፋሱ ማየል እና ማነስ፣ መቀዝቀዝ እና መሞቅ፣ በተለያዩ አበቦች እና ቅጠሎች ማበብና መርገፍ፣ በዳመናው መጥቆር እና መንጣት፣ እንደየቦታው ሁኔታ ተፈጥሮአዊ  በሆኑ ልዩ ልዩ ክስተቶች ጊዜ እንዳለፈ፣ ወቅት እንደተለወጠ፣ ዘመን እንደተቀየረ ማወቅ ይቻላል፡፡ በእነዚህ ወቅትና ሁኔታዎች ያሉ አውዳመቶችም በተለያየ ቦታ የተለያየ መልክ ይኑራቸው እንጂ የብዛም ይነስም ይከበራሉ፡፡  


    የተፈጥሮ ድምር አባል የሆነው የሰው ልጅም ከሁሉ ተለይቶ በተካነው የማሰብ እና የመፍጠር ችሎታው  ቀናትን፣ ወራትን እና ዘመናትን ከፈፀማቸው ድርጊቶች እና ካጋጠሙት ሁኔታዎች ጋር ትዝ እንዲሉት ያደርጋል፡፡

  በየዓመቱ የተወለደበትን ቀን እንደ ቤቱ አቅም እና ፍቃድ አክብሮ እና አስቦ የሚውል ሰው ጥቂት አይደለም፡፡ የጋብቻ ቀኑን፣ ስራ ጀመረበትን እለት፣ ምንም የሆነበትን ይሁን ያደረገበትን ቀን በተለያየ መንገድ ለማስታወስ ይሞክራል፡፡ በተለይ በሃገራችን ወግና ልምድ አውዳመቶች በመጡ ቁጥር ለየት ያለ ከበሬታ ይደረግላቸዋል፡፡ የሚደረግላቸው የአከባበር አይነትም ሆነ ድምቀት እንደ አውዳመቶቹ የተለያየ ነው፡፡ ለገና እነደ ፋሲካ ፣ ለፋሲካ እንደ እንቁጣጣሽ፣ ለእንቁጣጣሽ እንደ አረፋ፣ ለአረፋ ደግሞ እንደ መወሊድ ላይደገስ እና ላይደምቅ ይችላል፡፡ በተለያየ ምክንያት ማለት ነው፡፡

    አንዱ ቤት የአረፋ በዓል ሲደምቅ ሌላው ቤት የመወሊድ በዓል ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ለአንዱ ቤተሰብ ገና ትልቅ በዓል ሲሆን ለሌላው ደግሞ የደመራ በዓል የተለየ ይሆናል፡፡ እረ በዓል ማለት ፋሲካ ነው የሚልም አይጠፋም፡፡ የምን ፋሲካ ጥምቀት ነው እነጂ ዓመት በዓል “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚባልበትም ቤት አለ፡፡በሌላ በኩል በሀገራችን ተፈጥሮ እንኳን ራሷ ለመስከረም ወር የምታደላለት በዓል ማለት “እንቁጣጣሽ” ነው የሚሉም አይታጡም፡፡


   እንቁጣጣሽ /አዲስ ዓመት/ ለእኛ የተለየ ነው የሚሉት እነዚህ አካላት ሃሳባቸውን በስነ ቃል ያጠናክራሉ፡፡
                ውብ መስከረም ለምለም
                ውብ መስከረም ለምለም
                ከወራቶች ሁሉ ውብ እንዳንቺ የለም፡፡ እያሉ አዲስ ዓመትን /እንቁጣጣሽን/ ከወርሃ መስከረም ጋር አያይዘው ያወድሳሉ፡፡

   በሁለት ወር ክረምት ቆሻሻው ተጠራርጎ፣ የደረቀው፣ የወረዛው እና የረገፈው ቅጠል ለምልሞ እና አቆጥቁጦ፣ ውብ አበባዎችም በየመስኩ ደምቀው ይታያሉ፡፡ የመስከረም ወር ለምለም የሚታይበት እና ምድር በአበባ የምትሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ለእንቁጣጣሽ የሚዘጋጁ ዘፈኖች ልምላሜን በሚያጎሉ ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡

   ዘመን አልፎ ዘመን ሲለወጥ ፣ ዳመናው ተሸኝቶ ሰማዩ ሲገለጥ ምድር በአበቦች ልምላሜ ትንቆጠቆጣለች፡፡ በመስከረም የሚታዩት ወፎች እንኳን መስከረም ጠባ እንዲሉ የተላኩ ይመስላሉ፡፡ ፀሀይም ገና ብቅ ከማለቷ የአዲስ አመት ፀሀይ እንደሆነች ፈገግተዋ ያሳብቅባታል፡፡ እኛም ታዲያ እንደየሁኔታው በአዲስ መንፈስ ቤታችንን እና ግቢያችንን አፀዳድተን፣ ቤት ያፈራውን አዘጋጅተን ፣ ለበዓሉ የሚገባውን የየበኩላችንን አቅርበን ነው እንቁጣጣሽን የምንቀበለው፡፡


   በህፃናት ዘፈንና ጭፈራ መስከረምን እንኳን ደህና መጣህ ብለን፣ ከዘመድ ተጠያይቀን፣ በልጆች አበባ ስጦታ እንኳን አደረሰህ/ሽ ተባብለን በተቻለን መጠን እንደየአቅማችን በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ለማክበር እንጥራለን፡፡ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ብያለሁ፡፡ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ምርቃት እኔም የአመት ሰው ይበለን ብዬ ተሰናበትኩ፡፡

             .….…ከብረው ይቆዩን ከብረው ፣ ላመት ወንድ ልጅ ወልደው
               በመጋረጃ ውለው ፣ ሃምሳ ጥገቶች አስረው
               ከብረው ይቆዩን ከብረው ፣ ከብረው ይቆዩን ከብረው!!!

No comments:

Post a Comment