Friday, September 12, 2014

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅም እንዳላት ተገለጸ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትላንት ረፋድ ላይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳ ሀያቱን በፅሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳ ሀያቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ምስረታ የነበራት የላቀ ሚና አሁን እያካሄደች ያለችውን የእግር ኳሱ መሰረተ ልማት እድገት እና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙርያ መክረዋል፡፡ ዓመታዊ ስብሰባው  ከመስከረም 2/2007 እስከ መስከረም 10/2007 ይካሄዳል፡፡ 
  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅሙ እንዳላትና የትኛውንም አይነት መሰል ኃላፊነት ቢሰጣት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን /ካፍ/ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ በበኩላቸው አስፈላጊን ቅደመ ሁኔታ ካሟላች ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል። በካፍ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢሳ ሃያቱ የተመራ የልኡካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይቷል።

  በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የስፖርት ኢንዱስትሪ ለማገዝና ለማጠናከር ከኮንፌደሬሽኑ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተነጋግረዋል። ከውይይቱ በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴዎች ጀምራለች።
 
 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደገለፁት "በአጠቃላይ እኛ የአፍሪካን ዋንጫን ለማዘጋጀት በታሪካችንም በቁመናችንም እንመጥናለን በተለይ ደግሞ የአሁኑ ሁኔታችን። ምናልባት የትኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ብንጠይቅና ብናዘጋጅ ይሻላል የሚለው ዝርዝር እቅድ ስለሚያስፈልገው የእግር ኳስ ፌደሬሽናችን ከስፖርት ኮሚሽናችን ጋር ሆነው ያንን እንዲያጠሩና የተሟላው ጥያቄ ከዚህ በፊት የተጀመረ አለ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው እዚህም የተነጋገርነው። በኔ እምነት ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ አለብን መንግስትም ይሄንን በጣም ነው የሚደግፈው"ብለዋል።


  ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ስፖርት ትልቅ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ይህ ለረጅም ጊዜ ተቀዛቅዞ ቆይቷል ያሉት አቶ ደመቀ አሁን እየታየ ያለው መነቃቃት የሚያበረታታ እንደሆነ ጠቁመዋል። ኮንፌደሬሽኑ ይህንን ተነሳሽነትና መነቃቃት በሚደገፍባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም አገሪቱ በተለያዩ መድረኮች ያላትን ውክልና በማስፋት ዙሪያም ተወያይተዋል። አቶ ደመቀ እንደገለጹት "በውይይቱ ኮንፌደሬሽኑ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያለውን የስልጠና ማእከልና ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድኑን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል" 
 
     
  የካፍ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢሳ ሃያቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ፍላጎት እስካላትና ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላች ድረስ ካፍ ሃላፊነቱን ቢሰጣት ደስተኛ እንደሆኑ ነው የተናገሩት። ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በኢትዮጵያ በተለይ በታዳጊዎች እና ወጣቶች ላይ ያለውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለማሳደግ በሚረዳዱባቸው ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውንም ገልጸዋል። መንግስት ይህን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ ኮንፌደሬሽኑም በሚችለው ሁሉ ይህን ያግዛል፣ ያበረታታልም ብለዋል።
  
  ካፍ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገውን የኮንፌደሬሽኑ አመታዊ የስራ አስፈጻሚና የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ያካሂዳል። "ይህን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ የተመረጠችው እግር ኳሷን ለማሳደግ ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለች አገር በመሆኗ ነው" ሲሉ ተናግረዋል የካፍ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢሳ ሃያቱ ።
  ኢትዮጵያ በ 1979 የአፍሪካ ዋንጫን ስታዘጋጅ መጥቼ  ነበር። አሁንም ቢሆን ሃገሪቱ የማዘጋጀት ፍላጎቱ እስካላትና ቅድመ ሁኔታዎቹን እስካሟላች ደረስ በሃገሪቱ ህዝብ ውስጥ ካለው የእግር ኳስ ፍቅር ጋር ተደምሮ ድጋሚ የማዘጋጀት እድሉን ብታገኝ ካፍ ደስተኛ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም የሃገሪቱ እግር ኳስ ለማሳደግ ያደረገውን ጥረት በመገንዘብ ኮንፌዴሬሽኑም ለሃገሪቱ እግረ ኳሰ እድገት የሚጠበቀውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
  ሊቢያ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫን እንደማታዘጋጅ ከታወቀ በኋላ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ጋና የማዘጋጀት እድሉ ይሰጣቸው ዘንድ ለካፍ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ናቸው።

No comments:

Post a Comment