የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎችና በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ባገኙት የሽልማት ገቢ ከ1 እስከ 50 በወጣው ደረጃ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች በ23 አትሌቶች እንደተወከለች ለማወቅ ተቻለ፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በሽልማት ገቢያቸው ኃይሌ ገብረስላሴ እና ጌጤ ዋሚ ይመራሉ፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በዓለም ዙርያ በተካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶች ያገኙአቸውን በግልፅ የሚታወቁ የገንዘብ ሽልማቶች በመደመር ደረጃውን ከሳምንት በፊት በድረገፁ ይፋ ያደረገው የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ማህበር (ARRS/ Associations of Road racing statisticians ) ነው፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ደረጃ በወንዶች ምድብ የሚመራው በ52 የተለያዩ ጊዜያት 3 ሚሊዬን 548 ሺህ 398 ዶላር ያፈሰው ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሴቶች ምድብ ደግሞ በ56 የተለያዩ ጊዜያት 2 ሚሊዬን 236 ሺህ 415 ዶላር ያገኘችው የእንግሊዟ ፓውላ ራድክሊፍ ናት፡፡ በወንዶች ምድብ በደረጃው ሰንጠረዥ መግባት ከቻሉት 50 አትሌቶች 10 ኢትዮጵያውያን ሲገኙበት በድምሩ 10 ሚሊዬን 345 ሺህ 423 ዶላር በሽልማት ገቢ አድርገዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ከ50ዎቹ አትሌቶች 13 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ድምር የሽልማት ገቢያቸው 9 ሚሊዬን 575 ሺህ 957 ዶላር ነው፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር www.arrs.net በተባለው ድረገፁ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ከ3ሺ ሜትር አንስቶ ያሉትን የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና ሌሎች ውድድሮች በትኩረት በመከታተል የአትሌቶችን የውጤታማነት ደረጃ፤ ሰዓትና ድምር ስኬት ከፋፍሎ በማስላት ወርሃዊ እና ዓመታዊ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚሁ ድረገፅ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች በሰበሰቡት የሽልማት ገንዘብ ላይ ደረጃውን በማውጣት የሚያስታውቅበት አሰራርም አለው፡፡ ኤአርአርኤስ በሽልማት ገቢ ለሚሰራው ደረጃ እና ሌሎች መረጃዎችን በድረገፁ ለማስፈር የሚጠቀምበትን ዳታቤዝ ለማዘጋጀት በመላው ዓለም የሚደረጉን ከ160 ሺህ በላይ የጎዳና ላይ የሩጫ እና ሌሎች ውድድሮችን በመከታተል መረጃዎችን ከማሰባሰቡም በላይ በየውድድሩ 35 ሺህ አትሌቶች ያስመዘገቧቸውን 900 ሺህ በላይ ውጤቶች አገናዝቧል፡፡ እነዚህን መረጃዎች በማሰባሰብ እና በማቀናበር ከስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመላው ዓለም ያሉ ከ100 በላይ ባለሙያዎች የሚሰሩት ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የአትሌቲክስ በጎ ፍቃደኞችም በተለያዩ ተግባራት ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡
ኤአርአርኤስ የዓለም አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫ እና ሌሎች የአትሌቲክስ ውድደሮች ያገኟቸውን የሽልማት ገቢዎች ያሰባሰበው በግል በሚመዘገብ ውጤት በግልፅ የሚወስዷቸውን የሽልማት ድርሻዎችና በቡድን ውጤት የሚያገኙትን ገቢ በመደማመር ነው፡፡ በሽልማት ገቢው የተሰራው ደረጃ አትሌቶች በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በግላቸው ተደራድረው የሚያገኟቸውን የተሳትፎ ክፍያዎች፤ ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች፤ የቦነስ ሽልማቶች፤ የስፖንሰር ገቢዎች፤ እንደመኪና አይነት የተለያዩ ስጦታዎችን ያካተተ አይደለም፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በኤአርአርኤስ ድረገፅ በዓለም አትሌቶች የሽልማት ገቢ ደረጃ ላይ በሁለቱም ፆታዎች ከ50ዎቹ ተርታ የገቡት የኢትዮጵያ አትሌቶች ባገኟቸው የሽልማት ገቢዎች በአገር እና በዓለምአቀፍ የሚኖራቸው ደረጃ ነው፡፡
=======================
በወንዶች
$3,548,398 (52) ኃይሌ ገ/ስላሴ
- ከዓለም 1ኛ
1,559,828 (47) ቀነኒሳ በቀለ - 2ኛ
1,544,520 (18) ፀጋዬ ከበደ - 4ኛ
648,500 (10) አዲስ አበበ - 15ኛ
$573,445 (24) ሌሊሳ ዴሲሳ - 21ኛ
568,947 (38) ገብሬ ገ/ማርያም - 22ኛ
533,700 (32) ድሪባ መርጋ - 26ኛ
475,850 (31) ታደሰ ቶላ- 35ኛ
475,465 (26) ጥላሁን ረጋሣ -36ኛ
416,770 (11) ደሬሳ ኤዴ - 47ኛ
በሴቶች
$1,438,280 (44) ጌጤ ዋሚ - ከዓለም 6ኛ
1,254,395 (67) ብርሃኔ አደሬ - 9ኛ
970,893 (56) መሠረት ደፋር - 16ኛ
904,836 (43) ጥሩነሽ ዲባባ - 17ኛ
835,605 (45) ማሚቱ ደሳካ - 19ኛ
772,189 (19) አሰለፈች መርጊያ - 22ኛ
647,873 (46) ደራርቱ ቱሉ - 28ኛ
622,053 (36) ድሬ ቱኔ አሪሲ - 29ኛ
621,508 (25) ብዙነሽ በቀለ - 30ኛ
517,380 (40) መሰለች መልካሙ - 36ኛ
517,220 (18) ትርፌ በየነ - 37ኛ
515,185 (27) አፀደ ባይሳ - 40ኛ
475,920 (29) ሙሉ ሰቦቃ - 45ኛ
ማስታወሻ - በቅንፍ የተቀመጠው አኃዝ የተሸለሙበት ብዛት ነው፡፡
አንድ ዶላር በወቅታዊ የምንዛሬ ዋጋ 19.80 ብር ነው፡፡
ምንጭ ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment