Friday, March 28, 2014

የምኒልክ መስኮት


     ይህ ቦታ ከደ/ብርሃን ከተማ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በሚወስደው የአስፖልት መንገድ 4ዐ ኪ.ሜትር ያክል እነደተጓዙ አንዲት ጥድና ጅብ ዋሻ የሚባሉ አካባቢዎች እንደደረሱ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ከፍታ ተራራ በመውጣት የሚያገኙት ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን ቦታ "የምኒልክ መስኮት" አንዴም "ገማሳ ገደል" በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ ቦታ በጣም ከፍተኛ ተራራ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከአመት አመት ልምላሜ የማያጣውና በአረንጓዴ ሸማ እንደተሸፈነ ጌጥ ተፈጥሮ ውበት ያለበሰችው አስደናቂ ሥፍራ ነው፡፡

       ከተፈጥሮአዊ ውበቱ ጋር ተዳምሮ በአካባቢው ያለው እንደ ጭስ ጧት ከማታ የሚግተለተለው ጉምና ነፋሻማ አየር ሁልጊዜ የማይሰለችና አስደሣች ስፍራ ያደገርዋል፡፡ በዚህ ስፍራ ነው እንግዲህ ሆን ተብሎ የታቀደና በተዋጣለት መሀንዲስ ተከርክመው የተሰሩ የሚመስሉት ግራና ቀኝ እንደምስል ቀጥ ብለው የሚገኙትን ተራሮች ከነ ግርማ ሞገሣቸው የሚያገኙት፡፡

  በዚህ ቀዳዳ ወደ ምስራቅ ቁልቁል አሻግረው ሲመለከቱ ያላሰቡትንና ያልጠበቁትን ክስተት ይመለከታሉ፡፡ የይፋት ቆላማ መንደሮች፣ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው ትልቁ ስምጥ ሸለቆ ፣ የአፋር ክልል በርሃማ ቦታዎችና የአዋሽ ወንዝ በሰልፍ ተኝተው በአግራሞት ለመመልከት ያስችልዎታል፡፡ይህ የሚሆነው ታዲያ ከገደሉ በር እንደ እጣን ጭስ እየተጥመለመለ የሚወጣው ነጭ ጉም እና የአካባቢውን ቀዝቃዛ አየር እየሳቡ ነው ፡፡

  አፄ ምኒልክ በንግስና ዘመናቸው ወደ አያታቸው ንጉስ ሣህለ
 ስላሴ የትውልድ ቦታ ወደ ሆነችው ሰላድንጋይ ከተማ ለተለያዩ ጉዳዩች ሲሄዱና ሲመለሱ በዚህ ስፍራ በመገኘት ትልቁ የስምጥ ሸለቆ የሚያልፍባቸውን አካባቢዎችና የአዋሽን ወንዝ በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ከመደነቃቸው የተነሣ በተደጋጋሚ በቦታው እየተገኙ ይመለከቱ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎችም የዚህን ስፍራ መጠሪያ ስም የምኒልክ መስኮት የሚል ስያሜ ሰጥተውት እስከ አሁን ድረስ በዚሁ ስያሜ እየተጠራ ይገኛል፡፡



        ሥፍራው የወፍ ዋሻን ደን ከፊል ገጽታ ከስሩ የያዘ ሁልጊዜ ለምለም የማይለየው በመሆኑ በርካታ ዝንጀሮዎች፣ ሺኮኮዎችና ገደሉን እንደመጠለያ አድርገው የሚኖሩ በርካታ የአእዋፍ ዝርያዎች የሚገኙበት መሆኑ ደግሞ የቱሪስት መስህብነቱን ይበልጥ ማራኪና አስደናቂ ያደርገዋል፡፡

No comments:

Post a Comment