በአብዛኛው ኢትዮጵያውን ዘንድ የሚወደዱትና “እምዬ” በሚል ቅጽል የሚጠሩት ዐፄ ምኒልክ ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ነበሩ፡፡ “እምዬ” የሚለውን ቅጽል ሕዝቡ የሰጣቸው፤ የተራበውን ሕዝብ ግብር የሚያበሉ፤ ያለ ፍርድ ሰው የማይቀጡና ደግ ስለሆኑ ነው፡፡
ዳግማዊ
ዐፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ ዓ.ም. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የምኒልክን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር ‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ። ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፍ ።
ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ።አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱ የሸዋውን አልጋ የምኒልክ አባት ንጉስ ኃይለ መለኮት ወረሱ።ዓጼ ቴዎድሮስ በጥቅምት ወር ፲፰፻፵፰ ዓ/ም ትግራይንና ወሎን አስገብረው፣ ምኒልክ ገና የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ፤ የድፍን አማራንና የወሎን ጦር አስከትተው የሸዋውን ንጉሥ ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ሸዋ ገቡ። ሁለቱ መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ተዘጋጅተው ሲጠባበቁ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ባደረባቸው ሕመም ጥቅምት ፴ ቀን ፲፰፵፰ አረፉ። በዚህ ጊዜ የሸዋ መኳንንት ሕፃኑን ምኒልክን ከጠላት እጅ እንዳይወድቅባቸው ይዘው ሸሹ፤ ዳሩ ግን ዐጼ ቴዎድሮስ እንደሚከታተሏቸው ስላወቁ ኅዳር ፴ ቀን ፲፰፵፰ ዓ/ም የልጅ ምኒልክ ሠራዊትና የዐፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በረከት በተባለው ቦታ ላይ ገጥሞ የምኒልክ ሹማምንት አቶ በዛብህ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ ተያዙ። ልጅ ምኒልክም ለቴዎድሮስ ገቡ። ምኒልክ መቅደላ ገብተው በቁም እሥር ይቀመጡ እንጂ ከቴዎድሮስ ልጅ ከመሸሻ ጋር አብረው አደጉ። ወዲያውም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሹመው በጥር ወር ፲፰፻፶፮ ዓ.ም የዓፄቴዎድሮስን ልጅ ወይዘሮ አልጣሽን አገቡ። በዚህ ሁኔታ ፳፪ ዓመታቸው ድረስ ለአሥር ዓመታት ዐፄ ቴዎድሮስ ግቢ ኖሩ።
ዐፄ ቴዎድሮስ ምኒልክን እንደልጃቸው ያዩዋቸውና በታላቅ ጥንቃቄም ያስተምሯቸው ነበር። ምኒልክም ቴዎድሮስን እንደአባት ይወዷቸው እንደነበር ይገለጻል። ምኒልክ ከመቅደላ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፰፻፶፯ አምልጠው አንኮበር ገቡ። በአንኮበር ጥቂት ወራት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ወርደው አዲሱን ከተማቸውን ልቼን እያሠሩ ተቀመጡ። ዐፄ ምኒልክ የመጀመሪያ ቤተመንግሥታቸው ልቼ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናትና የልቼ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ያስረዳል፡፡ በተለይም ዐፄ ምኒልክ ከየካቲት ፲፰፻፷ ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ ፲፰፻፸፰ ዓ.ም በልቼ ቤተመንግሥት እንደነበሩ በተጻጻፉት ደብዳቤ አማካኝነት ታውቋል ፡፡ ምኒልክ ከልቼ ቤተመንግሥት ሳሉ ከሀገር ውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ መልእክቶችን ተለዋውጠዋል። ከየካቲት ፮ ቀን ፲፰፻፸፰ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲ ቀን፲፰፻፸፰ ዓ.ም ከዐፄ ዮሐንስ ጋር ልቼ ላይ ውጊያ አደርገዋል፡፡ በኋላም የካቲት ፲፪ ቀን ፲፰፻፸፰ ዓ.ም ውጊያ ለማቆም ፣የልቼ ሥልጣን ማካፈልንና በሌሎች ጉዳዮችም ለመረዳዳት ስምምነት አድርገዋል፡፡ ይህም የልቼ ስምምነት ተብሎ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ኤስ ሩቬንደንና ሪቻርድ ፓንክረሥት እንደዘገቡት ዳግመኛ በመጋቢት ፲፰፻፸፰ ዐፄ ዮሐንስና ዐፄ ሚኒሊክ ልቼ ላይ የማዕረግ አጠቃቀምን በተመለከተ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ታሪከ ነገስት ዘዳግማዊ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የዐጼ ምኒልክን ንግሥናና የልቼ ቤተ መንግሥትን ሥነ ሥርዓት እንዲህ ይገልጹታል ፤ “….(ምኒልክ) መስቀልን ውለው ልቼ ከተማቸው ወጡ፡፡ ከዚያም በሥርዓተ መንግሥት ዘውድ የሚደፉበት፣ አዳራሽ የሚገኙበት ጊዜ ነውና ልቼ ከተማ ከዕድሞው ግቢ ሰፊ ዳስ ተሠርቶ ግብር ለማብላት ልክ መጠን የሌለው ሁኖ ተዘጋጅቶ ነበረ፡፡ ደግሞም ከዳሱ አፋፍ ከሰገነቱ ዝቅ ያለ ሥራው ልዩ ልዩ የሆነ መንበር ተሠርቶ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የዳሱ ጌጥ ሥራው የቆመበትም ሁሉ በልዩ ልዩ ዓይነት ግምጃ የተሸፈነ ነበር፡፡ ከዚህም አስቀድመው ባዋጅ ‘በምገዛው አገር የሚኖር ካህን ከየደብሩ መስቀልና ጥና ከአልባሳቱ ጋር እየያዘ በጥቅምት ሁለት ቀን ይግባ’ ብለው አዘውት ጠቅሎ ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ በእስክንድርያ ሃይማኖት ሳይገዘት ሰንብቶ የነበረው ሲገዘት ሰነበተ፡፡
ከዚህም በኋላ በጥምቅት በ፫ ቀን ቅዳሜ ማታ ንጉሥ ከነሠራዊታቸው ከልቼ ተነሥተው ደብረ ብርሃን ወርደው አደሩ፡፡ ሲነጋ ንጉሡ ከመቅደስ ልብሰ መንግሥት ለብሰው መምህር ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ግርማ ሥላሴ ንጉሡን በወርቅ አልጋ አስቀመጧቸው፤ ዘውዱንም ደፉላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የመምህራኑ ጸሎት ይህ ነው፡፡ እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ ምኒልክ ወብዙኅ ይትሐሠይ በአድኅኖትከ፤ ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ፤ ወስእለተ ከናፍሪሁ ኢከላእካ፤ እስመ በጻሕካ በበረከት ሠናይ፤ ወአነበርከ አክሊለ ዲበ ርእሱ ዘእምዕንቍ ክቡር፤ ሐይወ ሰአለከ ወሀብኮ፤ ለነዋኅ መዋዕል ለዓለመ ዓለም እያሉ ምስጋና እየጨመሩ በየመሥመሩ ሁሉ ንሴብሕ ወንዜምር ለፅንዕከ ብለው ይህንን መዝሙር እያደረሱ የወርቅ ሰይፍ አስታጠቋቸው፡፡ ቅንት ሰይፈከ ኃያል ውስተ ሐቌከ በሥንከ ወበላሕይከ አርትዕ ተሠራሕ ወንገሥ እያሉ ይህንን መዝሙር በእንተዝ ይገንዩ ለከ አሕዛብ እግዚኦ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም እስከሚለው ድረስ ሲጨርሱ ካህናቱም ከቅድስት ቁመው በአንድ ቃል ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ አሉ፡፡ ሊቀ መኳስ አጥናፍ ሰገድ ካባ ላንቃ ለብሶ፡፡ ራስ ዳርጌ ራስ በና ራስ ወርቅ አሥረው ወጡ፡፡ ባለወርቅ መጣምር በቅሎዎቻቸው ቀረቡ፡፡ ንጉሡ ከበቅሎ ሲሆኑ ግራ ቀኝ ሰይፍ ተመዞ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለጊዜው ተሸልመው የነበሩ ቁጥር የሌላቸው ሊቃውንት ከቤተ ክርስቲያን በወጡ ጊዜ ዑደት ሲሆን እንደ ፊተኛው ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ እያሉ ዞሩ ስፍራው ጠቦ በሩቅ ካህናት ንሴብሖ ይሉ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ጕዞ ተጀመረ፡፡ ሲጓዝም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ሠራዊቱም አጊጦ ጭፍራውም በየአለቀው አምሮ ተሰልፎ ይሄድ ነበር፡፡ እንዲህም ባማረ ጕዞ ተጕዘው ልቼ ከተማቸው ገቡ፡፡ ካዳራሽ ገብተው ከዙፋን ሲቀመጡ ከአደባባዩ የነበሩ መድፎች ፳፪ ጊዜ ተተኰሱ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ከቡሎ ወርቄ ጀምሮ እስከ ሣሪያ ተሰልፎ የነበረው ከቅጥሩም ውስጥ የተሰለፈው ነፍጥ በተተኰሰ ጊዜ ከብዛቱ የተነሣ የክረምት ነጐድጓድ መሰለ፡፡ በንጉሡም ዙፋን አጠገብ በተዋረድ በልዩ ልዩ ዓይነት ሥጋጃው ወላንሣው እየተነጠፈ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ራሶችም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ተቀምጠው ግርማ መንግሥት ሆኖ አዳራሽ ተገኝተው ዋሉ፡፡ …. ይህም ነገር በተደረገ ጊዜ ያየውም የሰማውም እጅግ አደነቀ፡፡ ይህም የሆነ ፲፰፻፸፩ ዓመተ ምሕረት በዘመነ ሉቃስ በጥቅምት በአራት ቀን ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ዘውዳቸውን በደስታ በፍቅር ለእግዚአብሔርም ለሰውም አስመርቀው ለሠራዊትዎ ብዙ ቀን አዳራሽ (ልቼ) ተገኙ፡፡” ሲል፦ አክታ ኢትዮጲካ የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ደግሞ ፲፰፻፸፪ ዓ.ም ፋዘር ማሲያ የተባለው ጣልያናዊ በዐፄ ሚኒልክ ልቼ ተጠርቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው የጣሊያን ጆኦግራፊ ማኅበር ወደኢትዮጵያ መግባት ስለፈለገ ፋዘር ማሲያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታስቦ ነው፡፡ ካርዲናል ማሲና እንደዘገበውም ፲፰፻፸፪ዓ.ም ልቼ በተደረገው የሶስት ቀን ድግስ ንጉሥ ምኒልክ ተገኝተው ነበር፡፡ ለዚህም ድግስ አዲስ የመመገቢያ አዳራሽ ተሰርቶ ነበር፡፡
በ፲፰፻፸፮
ዓ.ም የ፷፭
ዓመት አዛውንቱ ማርኬዝ ኦራሊዬ አንቲኖሪ ከጂዮቫኒ፤ ቻሪኒና ሎሬንዝ ላንዳኒ እንዲሁም ከጣሊያን ወታደሮቻቸው ጋር በመሆን በአንኮበር በኩል በጥቅምት ፯ ቀን ልቼ ደርሰው ነበር፡፡ በዚያም ከዐፄ ሚኒልክ ጋር ተገናኝተው ወደ አዳራሽ አስገቧቸው ግብዣም ተደረገላቸው ፡፡ በ፲፰፻፸፯ ዐፄ ሚኒልክ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአውሮፓውያን ወታደራዊ ዘዴ እንዲሰለጥኑ በማሰብ አልጀሪያ የነበረ የፈረንሳይ ጦር አባል ሎያዥ ፓይተር የተባለን ሰው ልቼ መጥቶ እንዲያሰለጥን አድርገዋል፡፡ በ፲፰፻፸፯ መጨረሻ አንቲኖሪና ቻሪኒ በሴባስቲያኖ ማርቲና አንቶኒዬ ቺቺ አማካኝነት ቺሪና ቺቺ ኢትዮጵያን ለማሰሰ መጥተው ግንቦት ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፯ ከልቼ ተነሡ ፡፡
የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን
የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የዐፄ ምኒልክ ልቼ ቤተ መንግሥት ይባል ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተበሎ ተሰይሞ በቤተ ክርስቲያን ስም ነው የሚታወቀው፡፡ ስያሜውን የሰጡት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ናቸው፡፡ ቀድሞ በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሠረቱ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ:: ኋላ በግራኝ አህመድ ከፈረሱት ከአብያተ ክርስቲያናት መካከል የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ይገኝ ነበር:: ይህንንም ስለሚያውቁ ይሆናል አቡነ ኤፍሬም በደብረ ብርሃን (ልቼ) ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሠራ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት::
በድርሳነ ዑራኤል ዘሐምሌ ሁለተኛ ምእራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አሳብ እንዲህ ይላል “…ከዚህ በኋላ
ሃይማኖቱ የቀና ዘርዐ
ያዕቆብ ነገሠ እሱም
መጀመሪያ በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ደብረ
ብርሃን ላይ ታላቅ
ቤተ ክርስቲያን ሠራ
ሁለተኛም ቅድስት በሆነች
በእናቱ በድንግል ማርያም
ስም ሦስተኛም የመላእክት አለቃ
በሆነ በቅዱስ ዑራኤል
ስም …”
በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ለቀብርም ሆነ፤ ለአገልግሎት ርቆ ለመሄድ ተገዶ ነበር:: በዚህም የተነሣ ይህ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከል ግድ ስላስፈለገ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም መጥተው፤ ቦታውን ባርከው፣ ስሙንም የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ብለው መሰየማቸውን መሪጌታ ክፍለ ክርስቶስ ያስረዳሉ::
ዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸው እንደነበረ ከመጻሕፍትና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም መጽሐፍ ያገኘነው:: እዚህ ቦታ ላይ የምናያቸው ተጨባጭ ነገሮች በወቅቱ ዐፄ ምኒልክ ለችሎት በሚያስቀርቡ ጊዜ ሕዝቡ ለፍርድ ሲመጣ ድንጋዮችን ይዞ በመምጣት በመከማቸታቸው ኋላም ለአጥር አገልግሎት ውሏል፡፡ ይህም ዙሪያውን በሦስት ረድፍ የድንጋይ ካብ (እንደ አጥር ሆኖ ስፋቱ ሁለት ሜትር ቁመቱ ሶስት ሜትር) የተከበበ ነው:: ይህ የካብ ድንጋይ አረጀ እንጂ ድሮ እንደተሠራ ነው:: ቢፈርስም እንኳን ታሪኩ እንዳይጠፋ እንደዚሁ ነው የተካበው:: ዐፄ ምኒልክ እዚህ ቦታ ላይ በንግሥናቸውና ለኢትዮጵያ ቅን ተጠሪ ሆነው በነበሩበት ሰዓት የማይጠፋ አትክልት፣ የማይጠፋ ሀብት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀምጠውለት ከሄዱት አንዱ ባሕር ዛፍ ነው:: ቦታው ረግረጋማ ስለነበር ከአውስትራሊያ የባሕር ዛፍ አምጥተው ስለነበር ዛሬ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው:: ልጆች በነበርንበት ሰዓት ት/ቤት ስንሄድ ቦታውን እንዲሁ እናየዋለን እንጂ ገባ ብለን በአካባቢው መጥተን የምናየው ነገር አልነበረም::
እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ግን ተሰብስበን ይህንን ለመሥራት ወይም ደግሞ የሚሠሩትን አካል እንደ እናንተ ያሉትን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሆኑትን ለመጥራት ተነሣሥተናል:: በወቅቱ ግን እሳቸው የሠሩትም ያደረጉትም በችሎት የተቀመጡበትም እኛን ሊያነሳሳ እና የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ እንዲፈተትበት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲውል እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይህን ያስቻለው የንጉሡ ቅንነት ነው ብዬ ነው እኔ የማስበው:: ይህ ታሪክ ደግሞ የዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡
ክምር ድንጋይ የሚመስለው በሙሉ ቤት ነው ፡፡ ሁሉም የድንጋይ ቤት ነው:: ቤተ መንግሥት ሰለሆነ በብዙ ዓይነት ነው ቤቱ፡፡ ቤቶቹ ባሉበት ፈርሰው ክምር ድንጋይ ቢሆኑም አጥሩ እንደ ኢያሪኮ ግንብ ሶስት ዙር ባለበት ቢገኝም ድንጋዩም ሆነ መሬቱ የሀገር ሀብትና ንብረት ስለሆነ ማንም ግለሰብ መውሰድና ማጥፋት ሳይችል ታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር እስከፈቀደ ድረስ መቀመጥ አለበት:: ቤተመንግሥት ሰለሆነ ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዋናው ቤተ መንግሥታቸውና የችሎት አዳራሽ አለ፡፡ የንጉሣዊያን ቤተሰብ መኖሪያ ነው ተብሎ የሚገመት አለ፡፡ የግብር አዳራሽ አለ፡፡ የወታደር ሰፈር አለ፡፡ የግብር ቤት አለ፡፡ ሠራተኞች ሰፈር አለ፡፡ የእንግዶች ማረፊያ አለ፡፡ የመኳንንቱ ቤት ወዘተ. ፍራሹና ግንቡ ይታያል፡፡ የችሎት ቦታቸው የነበረው ቦታ ለቤተ ክርስቲያኑ እንደ መቃኞ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ፈረስ መፈተኛቸው የነበረው ሜዳ አሁንም ማንም ሳያርሰው ይገኛል፡፡
የውኃ ምንጫቸው
ክረምት ከበጋ አትደርቅም አለች፡፡ የገበያ ቦታቸው የተንጣለለው ሜዳ አሁንም አለ፡፡ በማለት መሪጌታ ገልጸውልን፤ ማሳሰቢያቸውን እንዲህ በማለት አስከተሉ “ታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር ፋቃዱ ሆኗል፡፡ ድንጋዩን ማንም ሳይጠብቀው አግኝተነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እየተሠራ ነው፡፡ እንግዲህ ተባብረን ታሪኩን እንጠብቅ ቤተ ክርሰቲያኑን እንሥራ፡፡”
ቀድሞ የንጉሥ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የነበረው ቦታ ዛሬ የክርስቶስ መመስገኛ ሥፍራ ሆኗል፡፡ ታሪካዊነቱ እንዳለ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ወደፊት ተመራማሪዎች፣ ጎብኚዎች፣ የሃይማኖቱ ተከተዮች ልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም እንደፍላጎቱ ማስተናገድ እንዲቻል፡የሁላችንም ትኩረት ተሰጥቶት ቦታውን ማቃናት፣መጠበቅ፣ መገንባት ወዘተ. ይኖርብናል፡፡
|
No comments:
Post a Comment