Thursday, January 23, 2014

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ የተሰማራውን /አሚሶምን/ በይፋ ተቀላቀለ

   በባይደዋ በተካሄደ ስነ ሥርዓት በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃደ ከብሩንዲያዊው የአሚሶም ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሲላፍ የአሚሶምን አርማ ተረክበዋል፡፡ 

 በሶማሊያ የአሚሶም ተልዕኮ ከሚሸፍናቸው አራት ቀጠናዎች ሁለቱ ቀጠናዎች የሚያካትቷቸው ማለትም የጌዶን፣ የቤይና የቦኮር ክልሎችን እንዲሁም የማዕከላዊ ሶማሊያን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በኃላፊነት እንደሚረከብ ተገልጿል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ አሚሶምና የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የባይደዋ አካባቢ አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በርክክብ ስነ ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ፣ኢትዮጵያ የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም እንደራሷ ሰላም በመቁጠር በሁሉም መስክ የሀገሪቱን መልሶ ማቋቋም ጥረት ትደግፋለች ብለዋል፡፡

  የአሚሶም ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሲላፍ ሰላምና መረጋጋት ለራቃቸው ሕዝቦች መፍትሔ ለማምጣት የካበተ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አሚሶምን መቀላቀል ለሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

   
  
በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረመድህን ፈቃደ በበኩላቸው አሸባሪዎችን በመዋጋት ትልቅ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠርና የሀገራቸውን ሕግና ባህል በማክበር ለሶማሊያውያን ብሎም ለአካባቢው ሰላም የተጣለብትን ኃላፊነት በከፍተኛ ወታደራዊ ስነ ምግባር እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡

     የባይደዋና አካባቢው አስተዳዳሪና ተወካይም የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ ኃይል በማመስገን የሶማሊያን ሕዝብ የዘመናት የፀጥታ ችግር ለማስወገድ የኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን መምጣት የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት ፈቃድ ወደ ሶማሊያ  የገባው የአፍሪካ  ህብረት ሀይል ተልእኮውን  የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ ነበር። የኬኒያ፣  ብሩንዲና  ኡጋንዳ  ወታደሮችም  የተልእኮው አካል  መሆናቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment