ግብርናና
የምግብ ዋስትና በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ፤ የአህጉሪቱ መሪዎች በቀጣይ የግብርናውን ዘርፍ ስር
ነቀል በሆነ መልኩ በመቀየር የአፍሪካን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በቀጣይ መግባባት ላይ
ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ከሰላምና ጸጥታ ጋር ተያይዞም መረጋጋት የራቃቸውን ሃገራት ወደ ሰላም መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሪዎቹ ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያሰቀምጡም ነው የሚሆነው ።
የአየር ንበረት ለውጥ ፤ የመሰረተ ልማት ትሰስር እና ንግድም ጉባኤተኞቹ ከሚነጋገሩባቸው ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ። በጉባኤው
ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ኒኮሳዛ ዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ሀገራት በግብርና ላይ
የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት በማሳደግ የ7 በመቶ ዓመታዊ ዘላቂ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው
መስራት እንደሚኖርባቸው ነው ያሳሰቡት።
በግብርናው መስክ ባለው ስራ ላይ በስፋት የተሰማሩ የአፍሪካ ሴቶች በቂ የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ እና ሀብት እንዲያፈሩ የሚደረገውን ጥረት ህብረቱ እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል። አፍሪካ ለእድገቷ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ያላትን የንግድና የትብብር ስራዎችን በላቀ ደረጃ ማስኬድም ይጠበቅባታል ብለዋል ሊቀመንበሯ።
ከሰላምና
መረጋጋት ጋር በተያያዘም በተወሰኑ የአህጉሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች ትልቅ ዋጋ
እንደሚያስከፍሉ የታወቀ ነው ያሉት ዶክተር ኒኮሳዛ ፥ ስለሆነም ለሰላምና መረጋጋት የሚሰጠውን ዋጋ በዚያው ልክ
በመጨመር ዲሞክራሲያዊ እና ሀላፊነትን የሚሸከም አስተዳደርን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት ።
አፍሪካ
የ2063 አጀንዳን ማሳካት እንድትችል ህብረቱ ሁሉም አፍሪካዊ እና ትውልደ አፍሪካዊ ሁሉ የሚጠበቅብትን ሁሉ
በማድረግ ለዕቅዱ መሳካት ርብርብ እንዲያደርግም ዶክተር ኒኮሳዛ ድላሚኒ ዙማ ጥሪ አቅርበዋል። የህብረቱ
የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ፥ በአሁኑ ወቅት ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት
ከአጠቃላይ ባጀታቸው 10 በመቶ ያህሉን በግብርናው ዘርፍ ላይ መመደባቸው "ግብርናና የምግብ ዋስትና” በሚል መርህ
በአፍሪካ ለሚደረገው የለውጥ እና የዕድገት ጉዞ አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰላምና
መረጋጋትን በአህጉሪቱ ለማረጋገጥም ህብረቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ እየተወጣ ይገኛል ፤ በተለይም ባለፈው አንድ
ዓመት ውስጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን አለመረጋጋት በሰላም እንዲፈታ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ውጤት እያስገኘ
መሆኑን መመልከት ይቻላል ብለዋል አቶ ሀይለማርያም።
በአለፈው አንድ አመት ውስጥ አፍሪካውያን መልካም የሚባል ውህደት ፈጥረዋል ፤ የተለያዩ የጋራ አጀንዳዎችም በስኬት ተከናውነዋል ያሉት አቶ ሀይለማርያም ፥ በመካከለኛዋ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲረጋገጥ እና አገሪቱ ቀድሞ ወደነበረችበት መረጋጋት እንድትመለስ አለማቀፉ ማህበረሰብ ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በተጨማሪም
አህጉሪቱ የ2063 አጀንዳን እንድታሳካ ፣ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ
እንድትችልና የበለፀገች አፍሪካን ማየት እንዲቻል ከአፍሪካውያን የበለጠ ስራ እና ጥረት ይጠበቃል ብለዋል። በጉባኤው
አፍሪካ በመልካም አስተዳደር እምርታ አሳይታለች ፤ ስለሆነም አህጉሪቱን መላው የዓለም ህዝብ እና የተባበሩት
መንግስታት ድርጅት አይናቸውን እንደጣሉባት የተናገሩት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ምክትል ጽሀፊ ጃን ኢሊሰን
ናቸው።
በሌላ
በኩል የማዳጋስካርን ወደ ህብረቱ መመለስ ምክንያት በማድረግ ፕሬዝዳንት ሄሪ ራጃኦናሪማምፒያኒና ባደረጉት ንግግር
ሀገራቸው ጠንካራ መንግስት ለመመስረት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን ተናግረዋል። የሊቀመንበርነቱን ቦታም የሞሪታንያው ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብድልአዚዝ ከህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተረክበዋል። ጉባኤው በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል።
ምንጭ ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ