Saturday, September 3, 2022

ስለ መንዝ - አርባ ኃራ መድኃኒዓለም ታሪክ ምን ያህል ያውቃሉ ?


አርባ ኃራ መድኃኒዓለም አስገራሚ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቦታ የሚገኘው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ነው፡፡ ቦታው ከደብረ ብርሃን ከተማ 118 . ርቀት ላይ ይገም ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ የይገም ቀበሌ ከጣርማበር 75 .ሜ፤ ከሞላሌ ከተማ ደግሞ 22ኪሜ ይርቃል፡፡ ታሪካዊው ቦታ ከይገም ከተማ 10 ደቂቃ በእግር ከተጓዙ በኋላ ያገኙታል፡፡ ቦታው ዋሻ ሲሆን በዋሻው ውስጥ ደግሞ እጅግ ብዛት ያላቸው የቅዱሳን አጽሞች ይገኛሉ፡፡ይህ ቤተክርሲቲያንና ቅዱስ ዋሻ የሚገኙበት ቦታ አርባ ሃራ ምስካበ ቅዱሳን መድሃኒ ዓለም ተብሎ ይጠራል ፡፡

አርባ ማለት አርባ /40/ ቁጥርን ያመለክታል አርባ ቁጥር ምንድን ነው ቢሉ ቦታው የነበሩት አርባ ቅዱሳን ለመዘክር የተሰጠ ስም ነው፡፡ ሃራ ማለት ደግሞ ወታደር ማለት ነው የዚህ ስም አጠራር ደግሞ የምድራዊ ወታደርነት ሙያን የሚያመለክት ሲሆን በሃይማኖት ተጋድሎ ለአምላካቸው ታማኝ በመሆን ስለ ሀይማኖታቸው የተሰጡት የቅዱሳን የሰማእታትን ውጊያና ተጋድሎዋቸውን ለማመላከት የተሰጠ ስም ነው፡፡ በተጨማሪም ሃራ የጻድቁን ኣባት የአቡነ ኃራን ማለትም የገዳሙን መስራች ያስታውሳል፡፡ ምስካበ ቅዱሳን ማለት የቅዱሳን መገኛና ማረፊያ ማለት ነው፡፡

በምስካበ ቅዱሳን አርባ ሃራ መድሃኒ ዓለም ገዳም ውስጥ በርካታ አፅመ ቅዱሳን ይገኛሉ፡፡ እነዚህም አጽሞች በሰሌን በቆዳና በሸራ የተገነዙ ሲሆን አገናነዛቸውም የኢትዮጵያን የግንዛት ስርዓት የተከተለ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ምንም እንኳን በአፅም ላይ አፅም ተነባብሮ የሚገኝ ቢሆንም የመዓዛው ሽታ ዕጣን ዕጣን የሚሸት ነው ፡፡ አፅሞቹ ሲታዩ ቀሳውስት የነበሩበት መስቀላቸውን በደረታቸው ላይ አስረው መነኮሳት ፊታቸውን በእጃቸው ሸፍነው ምዕመናኑ እጃቸውን ወደ ጉያቸው ዘርግተዉ ይታያሉ፡፡ 9ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት በነገሰችበት ወቅት አብያተ ክርሰቲያናትን እንዲወድሙ ስታደርግ አቡነ ሃራ የሚባሉ ታላቅ አባት በአክሱምና በታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት የነበሩትን ታሪካዊ ቅርሶችና ቅዱሳት መጽሀፍት ሰብስበው በዚህ ቅዱስ ዋሻው ውስጥ አስቀምጠዋቸው እንደነበር ከተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በተከታታይም ከግብፅ ሀገር ከገዳመ አስቄጥስ አርባ ቅዱሳን በትዛዝ እግዚአብሔር መጥተው አቡነ ሃራ ከተባሉት አባት ጋር ሲኖሩ ከእለታት አንድ ቀን አቡነ ሃራ አርባውን ቅዱሳን ይህን ዋሻ ውስጥ ለውስጥ የምንፈለፍልበት መሳሪያ ፈልጉና አምጡ አሏቸው አርባውም ቅዱሳን ወደ ሃገራቸው ግብፅ ተመልሰው በመሄድ የዋሻ መፈልፈያ መሳሪያ አምጥተው ውስጥ ለውስጥ አራት ሰዓት የሚያስኬድ ዋሻ ፈልፍለው ልዩ ልዩ ክፍሎች ሰርተውለታል፡፡ ዋሻው ሁለት በሮች ሲኖሩት በውስጥ ደግሞ አምስት ክፍሎች ያሉት እንደነበር ነገር ግን አሁን እነዚህ ክፍሎች በእድሜ መግፋት ምክንያት በመደፈናቸው ማየት አይቻልም ፡፡


አቡነ ሃራም በዚህ ዋሻ በፆም በፀሎት ሲኖሩ ብዙ ተአምራትን በአምላካቸው ፈቃድ ፈጽመዋል፡፡ ከእነዚህ አስደናቂ ተአምራት መካከል ከእለታት አንድ ቀን ሁለት ሙሽሮች ከበቅሎ ተንከባለሉና በዋሻው በር ላይ ወድቀው ሞቱ በዚህ ግዜ የሙሽሮቹ አጃቢዎች ከፍተኛ ሃዘን ደረሰባችው ጻድቁ አቡነ ሃራ ይህን ተመልክተው ጸልየው በእሳቸው ፀሎትና በእግዚአብሄር ሃይል ሙሽሮቹን አስነስተው ለሰርገኞቹ አስረከቧቸው ሰርገኞቹም ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኖ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ምእመናንም ይህንን ተአምር አይተው በወቅቱ ለነበረው ገዢ በግዛትህ ውስጥ የሚገኙት አቡነ ሃራ የልጅህን አስከሬን ብትወስድለት ከሙታን ለይተው ያስነሱልሃል ብለው ነገሩት እርሱም የልጁን አስከሬን አሸክሞ ወደ ጻድቁ አባት ወደ አቡነ ሃራ ዘንድ አመጡ ከዚያም ንጉሱ አባቴ ሆይ በተሰጠዎት ሃብተ ጸጋ ልጄን ያድኑልኝ ብሎ በግንባሩ ወድቆ ለመናቸው የሞተውን ልጅ አስነሱለት በዚህም የጻድቁ ዝና እስከ ሩቅ ሃገር ተሰማ፡፡ 

ጻድቁ አቡነ ሃራም ወደ ፈጣሪያቸዉ አቤቱ ጌታዬ እየሱሰስ ክርስቶስ ሆይ ይህችን ቦታ አስቀድመህ እንደሰጠኽኝ ከእኔ በኋላም ለሚተኩ ወንድሞቼ እና ልጆቼ የተቀደሰችና የተባረከች ፀጋ የሚገኝባት አጋንንት የሚደክሙበት ቅዱሳን የሚማፀኑበት እና በመጨረሻም የቅዱሳን ዐጽሞች የሚያርፉበት ይሆንልኝ ዘንድ እለምንሀለሁ ብለዉ በጸልዩት ጊዜ አምላክ ጽኑል ልመናቸዉን ሰምቶ ለቦታዉ የጠየቁትን ቃል ኪዳን በአካል ተገለፆ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ከግብጽ መጥተዉ እርሳቸዉን ሲያገለግሉ / ሲያስተምሩ ብዙ ትሩፋት ሲሰሩ የኖሩት አርባዉ ቅዱሳን በዚሁ ቦታ አጽሞቻቸዉ ተቀምጠዋል፡፡


በመጨረሻም አቡነ ኃራ 11ኛው ክፍለ ዘመን በተወለዱ 220 አመታቸዉ ጥቅምት 27 ቀን አርፈዉ አባፍሬ ሰናይ የሚባሉ መነኩሴ ገንዘዉ በክብርና በይባቤ በደከሙበት አርባ ኃራ መድኃኒአለም ዋሻ አሳርፈዋቸዋል፡፡ በአርባሃራ ምስካበ ቅዱሳን መድኃኒአለም ገዳም በከበረዉ አፅም ጻድቁም ወደ እግዚአብሄር ፀልየው መግነዝ ከሚፈጸሙት ተአምራት መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህንን የቅዱሳን አጽም ግነዝና የተቀደሰዉን አፈር እየዳሰሱ በሽተኞች ለህመማቸዉ ፈዉስን ልጅ ያልወለዱ መካን የነበሩ እናቶችም የልጅ በረከት አግኝተዋል፡፡ በለምፅ የተመቱ ከለምፃቸዉ ድነዋል ፡፡ በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ወገኖች እህል ሲዘሩ የተቀደሰዉን አፈር በአንድነት በእርሻዉ ላይ ከበተኑት አይጦች ፣ወፎቸ ዝንጀሮዋችና ጃርቶች እንዲሁም ሌሎችም የእህል ጠላቶች አይደርሱበትም በእብድ ዉሻ የተነከሱ ሰዎች የተቀደሰዉን አፈር በዉሀ በጥብጠዉ ጠጥተዉና አሻሽተዉ ፍጹም ፈዉስ ያገኛሉ፡፡

አዘጋጅ - የመ///////ቤት

No comments:

Post a Comment