Wednesday, September 7, 2022

ኑ ጳጉሜ 3 ታላቁን እና ታሪካዊውን ምሳለ ማሪያም ሩፋኤል በዓል በድምቀት እናክብር...


መሥህለ ማርያም ሩፋኤል 713 ዓመት በላይ ወርቃማ ታሪክ ባለቤት ነው። በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ከመሃል ሜዳ ከተማ 13 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ያገኙታል፡፡ ለዚህ ታሪካዊና ሐይማኖታዊ ስፍራ ሥም ያወጡለት አፄ አምደ ፅዮን እንደሆኑ ይነገራል፡፡ መሥህለ ማርያም ማለት ‹‹ማርያምን›› የምለምንበት ማለት ነው፡፡

መሥህለ ለማርያም በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ከአክሱም ፅዮን ማርያም ተባርካ የመጣች መንዝ ላይ የመጀመሪያዋ ታቦት ናት፡፡ አጼ አምደ ፅዮን ከድል በኋላ ሲመለሱ ወደ መስሓለ ማርያም የቤተመንግስት ዝውውር ሲያደርግ በደብር ማእረግ ደብሩን ከተከሉ በኋላ መስሓለ ማርያም /ማርያምን የምንመለከትበት ቦታ/ ብለው እንደሰየሙት የአካባቢው አባቶች ያስረዳሉ፡፡

በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት አባቶች ታቦቷን በዋሻና በተለያዩ አካባቢዎች ከወረራው ለማትረፍ ተደብቃ እነዋሪ /ብርሃን አንኮበር የመሳሰሉ ቦታዎች ላይ ከተቀመጠች በኃላ አዲስ ዓለም ማርያም ገዳም እንድትቀመጥ ተደርጎ እስካሁን ድረስ በዚያው ትገኛለች፡፡ አሁን ደብሩ ሩፋኤል ይባል እንጂ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የመጀመሪያዋ ታቦት የማሪያም ነበረች ሲሉ አባቶች ይናገራሉ፡፡ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ምኒልክ ንግስና ዘመን ህዝቡ እስከመቼ ታቦት ሳይኖረን የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ በማንሳቱ አሁን ያለው የቅዱስ ሩፋኤል ታቦት እንዲተከል ተደርጓል፡፡ የሩፋኤል ታቦት ከዚሁ ወረዳ በአናዝ ጥድ ቀበሌ ከሚገኘው ገሜ ጊዮርጊስ ከሚባል ስፍራ የመጣ ነው ብለው ታሪካዊ ዳራውን ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን ታሪካዊቷና ጥንታዊቷ ታቦተ ማርያም በስፍራው ባትኖርም ስፍራው እስካሁን ድረስ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመጀመሪያዋ ታቦት ምስሓለ ማርያም/ ማሪያምን የምንለምንበት ስፍራ/ በሚል መጠሪያ ይጠራል፡፡


አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዚህ ቦታ ላይ ሆነውመፅሐፈ ምስጢር” የተባለውን ድርሰታቸውን እንደደረሱም ይወሳል፡፡ ዘመኑም አፄ ይስሐቅ የነገሱበት ነው፡፡ አፄ ዘርዐ ያዕቆብም ወደ አዳል ለውጊያ ሲሄድ መሥህለ ማርያምን ተስለው ሄዱ፡፡ ድል አድርገው ቢመለሱም ቤተ ክርስቲያኗን ሳያሰሯት ሞቱ፡፡ ይህንን የሰማው ልጃቸው በእደ ማርያም ቤተ ክርስቲያኗን አሰርቷል፡፡ በዮዲት ጉዲት ዘመን መርሐቤቴ ነጭገደል የተሰውትን ሰማዕታት አምጥቶ እዚህ ቦታ እንዲያርፉም አድርጓል፡፡ንግስናውን በዚያው የፈፀመ ሲሆን ርስት እና ጉልትም ለቤተክርስቲያኗ ሰጥቷል፡፡


ይህ ስፍራ 713 አመታት በፊት የታላቁ የአጼ ዘርአያእቆብ ልጅ ንጉስ በእደ ማርያም የንግስና መቀመጫ ስፍራ የነበረ የቤተ መንግስቱም ፍርስራሽ በአርኪዮሎጂስቶች ተቆፍሮ የተገኘበት እጅግ ባማሩና እድሜ ጠገብ በሆኑ አገር በቀል ዛፎች የተከበበ ቦታ ነው ከዚህ በተጨማሪም ጳጉሜ 3 በአመት አንድ ጊዜ የሩፋኤል ታቦት ወጥቶ የሚከበርበትና በዚህም ዕለት በዚሁ ቦታ በአመት አንድ ጊዜ የሚውል ገበያ የሚካሄድበት ነው፡፡ በዚህ ገበያ የረከሰ ማንኛውም እቃ /ሸቀጣ ሸቀጥ አመቱን ሙሉ ይረክሳል የተወደደም አመቱን ሙሉ ተወዶ ይቀጥላል ተብሎ በአካባቢው ማሕበረሰብ ዘንድ ይታመናል። ይህ ሁኔታ ዕለቱን ታሪካዊና ተወዳጅ እንዲሁም ልዩ ሆኖ አንዲቆይ አድርጎታል፡፡

                        “ይጎብኙ፣ ታሪክ ይወቁ ፣መንፈስዎን ያደሱ!!!

ምንጭ - የመ/////

No comments:

Post a Comment