Sunday, May 12, 2013

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች ቤት የንብረትና የሰነድ ማስረጃዎች ተገኙ

n     ግንቦት 4/9/2005 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተገኘ።
  ከገንዘብ በተጨማሪ በርካታ የቤት ካርታዎች፣የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችና ሌሎችም ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ  የፍርድ ቤት ማዘዣ በማውጣት ታዛቢዎችና ተጠርጣሪዎቹ ራሳቸው በተገኙበት ነው በትናንትናው እለት በግለሰቦቹ ቤትና መስሪያ ቤት ብርበራ ያካሄደው።
    ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ በሆኑት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት በተደረገው ብርበራ 8 ላፕቶፖችን ጨምሮ 200 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ፣26 ሺህ 300 የአሜሪካን ዶላር፣19 ሺህ 435 ዩሮ ፣560 ፓውንድና 210 የታይላንድ ገንዘብ  ተገኝቷል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ በለገዳዲና ለገጣፎ የሚገኙ የቦታ ካርታና ፕላን እንዲሁም የተለያዩ ሰነዶች መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል፤


        የፌዴራል ፖሊስ እንዳለው የቃሊቲ ጉምሩክ ኃላፊ በነበሩት ሌላኛው ተጠርጣሪ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም ቤትም እንዲሁ ወደ 2 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ  በጥሬው ተገኝቷል። አቶ አስመላሽ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ውስጥ የጉምሩክ ስነ ስርዓት አፈጻጸም የስራ ሂደት፣የኤርፖርት የኤርጉምሩክ የድህረ ክሊራንስ ኦዲት የስራ ሂደትና የኤርፖርት ጉምሩክ ስነ ስርዓት ቡድን መሪ በመሆን ጭምር ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። 

      ተጠርጣሪዎቹን ለህግ ለማቅረብ ከፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመሆን የተካሄደው ጥምር ዘመቻ በእቅድ የተመራ፣ህጋዊ ስርዓትን መሰረት ያደረገና የተሳካ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ገልጿል። በሂደቱም ከወንጀሉ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው ማስረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ነው በፌዴራል ፖሊስ የፋይናንስ ነክ ወንጀሎች ቡድን መሪ ኢንስፔክተር በለጠ ባለሚ የተናገሩት። በቀጣይም ፖሊስ በምርመራ ሂደቱ የደረሰበትን መረጃ ለህዝብ እንደሚያሳውቅና ህብረተሰቡም ህግን ለማስከበርና ሙስናን ለመዋጋት መንግስት በሚያደርገው ጥረት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment