Thursday, December 25, 2014

ከሊስትሮንት እና ሎተሪ አዟሪነት እስከ አንጋፋ ተዋናይነት ---- አርቲስት ሱራፌል ተካ !!!

 
   ተዋናይ ሱራፌል ተካ ትውልድ እና እድገቱ ጎንደር ፒያሳ አካባቢ ነው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈው ሱራፌል በወጣትነቱ በሊስትሮነት ፣ ሎተሪ አዟሪነት ረዘም ላሉ አመታት ሰርቷል፡፡ ከዚያም በ1982ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ በጎንደር ሲኒማ ቤት የሻይ ክበብ ባሪስታ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ በዚህ ወቅት በጎንደር ከተማ የሚገኙ አማተር ከያኒያን “አፄ ቴዎድሮስ - የአንድ እናት ልጆች” የተሰኘ ትያትር ለህዝብ ለማቅረብ ዝግጅት ሲያደርጉ እሱ ሹልክ እያል እየገባ ይመለከት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ እየተደበቀ ትያትሩን እየተመለከተ ተውኔቱን ያጠናል፡፡ ከያንያኖቹ ተለማምደው ሲጨርሱ እሱ መድረክ ላይ እየወጣ አንዴ ቴዎድሮስን ሌላ ጊዜ ድግሞ ገብርዬን ሆኖ ይጫወታል፡፡ ባጋጣሚ የተውኔቱ ፀሀፊ /ደራሲ/ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ እቃ እረስተው ሲመለሱ እሱ ሲተውን ይመለከቱታል፤ በጣም ተገርመውም ያደንቁታል፡፡ ሀሳብ ተለዋውጠው ይለያያሉ፡፡

   ሱራፌል ከሻይ ክበቡ ስራውን እየተወ የከያንያኑን ልምምድ ይመለከታል፡፡ ስራውን ትቶ እየጠፋ ሲያስቸግራቸው የክበቡ ኃላፊ ይከታተሉታል፡፡ እናም በሲኒማ ቤት በተደጋጋሚ ሲያገኙት ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ መጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡ ከዚያም ትያትር መመልከቱን ትቶ የባሪስታነት ስራውን እየሰራ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ይኸውም “አፄ ቴዎድሮስ - የአንድ እናት ልጆች” የተባለው ትያትር በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በየጦር ካምፖቹ እንዲቀርብ ሲደረግ “ገብርዬን” ሆኖ የሚጫወተው ወጣት ይጠፋል፡፡ 

      ይኸን ጊዜ የተውኔቱ ደራሲ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ባንድ ወቅት መድረክ ላይ የገብርዬን ገፀ ባህሪ ሲጫወት የነበረው ሱራፌል ትዝ ይላቸዋል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን አስተካክሎ እንዲተውን ይመረጣል፡፡ይህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ ሱራፌልን ወደ ተውኔቱ ያመራው፡፡ በወቅቱም የገብርዬን ገፀ ባህሪ ማለትም ታማኝነቱን ፣ ገርነቱን እና የዋህነቱን ስለሚወደው በግሩም ሁኔታ ተጫውቶ ያልተጠበቀ ነገር አሳየ፡፡ በዚህም አድነቆት ከየአቅጥጫው ጎረፈለት፡፡ ተዋናይ ሱራፌል ተካ ከሚሰራበት የሻይ ክበብ ሳያስፈቅድ በመሄዱ ሌላ ሰው ተቀጥሮ ይጠብቀዋል፤ እሱም የትወና ሙያውን በአጫጭር ስልጠናዎች በማጠናከር ይቀጥላል፡፡ 


  በጎንደር ቆይታውም “ዞብል” የሚባል አማተር የትያትር እና የስነ ፅሁፍ ክበብን በመመስረት ሊቀመንበር ሆኖም አገልግሏል፡፡ ከዚያም የቀድሞው የብአዲን ኪነት ፣ የዘመናዊ እና የባህላዊ ቡድንን ተቀላቀለ፡፡ ባህር ዳር ሙሉዓለም አዳራሽ ከተሰራ በኋላ የአማራ ክልል የባህል፣ የዘመናዊ እና የትያትር ቡድን ተባለ፡፡ ትንሽ ከቆየ በኋላ በአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ተጠቃለለ፡፡ በዚህም በቋሚ ሰራተኝነት ለረጅም አመታት አገልግሏል፡፡ ተዋናይ ሱራፌል ተካ በአማራ ክልል ቆይታው በርካታ ትያትሮችን ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ “ መጢቃ ፣ ቅርሻት ፣ አማጭ ፣ ጉድና ጅራት ፣ ሙት ይዞ ይሞታል ፣ አንድ ጡት ፣ ማሪኝ ፣ ሽፍንፍን ፣ የዘመን ምጥ እና እርጉም ሀዋሪያ ይጠቀሳሉ፡፡ የቴዎድሮስ ራዕይም እዚያ ተሰርቶ አዲስ አበባ ብሄራዊ ትያትር ነው የተመረቀው፡፡ ከ15 በላይ ትያትሮችን የተጫወተ ሲሆን ከ10 በላይ ባሉት መሪ ተዋናይ ፣ በ3 ያህሉ በዋና አዘጋጅነት እና በተቀሩት ደግሞ በረዳት አዘጋጅነት ተሳትፏል፡፡


  “አማጭ ፣ ጉድና ጅራት  እና ሙት ይዞ ይሞታል” - የመምህር ጎይቶም ሀይሌ ሲሆኑ “የዘመን ምጥ” ደግሞ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ድርሰት ነው፡፡ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ቆይታውም “የኢንስፔክተርነት” ማዕረግ አግኝቷል፡፡ ከባህር ዳር ወደ አዲሰ አበባ ከመጣ በኋላም በተለያዩ ትያትሮች እና ፊልሞች ላይ ልዩ ልዩ ገፀ ባህሪያትን ተላብሶ ተጫውቷል፡፡ ቴያትሮችን ስናስቀድም ፡- የጠለቀች ጀምበር ፣ ደጋግ ሰይጣኖች ፣ ጓደኛሞቹ ፣ ግዳይ ፣ የቴዎድሮስ ራዕይ ፣ ቶፓዝ ፣ ሶስተኛው ችሎት ፣ ቅጥልጥል ኮኮቦች ላይ ተውኗል፡፡ በተወሰኑት ላይ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የሚታዩ ስራዎችም አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ “የፍቅር ማዕበል” የተሰኘው ትርጉም ትያትር ይጠቀሳል፡፡


   የፊልም ስራን የጀመረው “ዘቢግ ባታለየን” / ግዙፉ የሻለቃ ጦር እንደማለት ነው/ አለም አቀፍ እውቅና ካላቸው እንግሊዛውያን እና አንጋፋ ኢትዮጵያን ተዋናዮች ጋር ነው፡፡ ፊልሙ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ሲሆን የታየው በጊዜው ከፍተኛ የሆነ ብር አግኝቶበታል፡፡ 8,000 ብር ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ላሎምቤ ፣ ባለስልጣኑ ፣ አባይ ወይስ ቬጋስ ፣ ኤማንዳ ፣ ፀረ ሚሊዮን ፣ ህይወት በደረጃ ፣ የባል ጋብቻ ፣ ጀግኖቹ እና አልበም ጥቂቶቹ ናቸው፡ 

   በተጨማሪም በሰው ለሰው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ “ኩራን” ሆኖ በመጫወት ከፍተኛ ተወዳጅነትን አግኝተዋል፡፡ ከባለቤቱ አርቲስት ገበያነሽ ኃይለማሪያም ጋር የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የባህል ፣ የዘመናዊና የትያትር ቡድን ክፍል ሳሉ ተዋውቀው አሁን ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አርቲስት ገበያነሽ የተለያዩ የሬድዮ ጭውውቶችን እና ድራማዎችን የምትፅፍ እና የምትጫወት ሲሆን በሰው ለሰው ድራማ ላይም የይጥና ባለቤት ሆና ተውናለች፡፡

No comments:

Post a Comment