Friday, December 12, 2014

ኢትዮጵያዊው ዶ.ር ቻርለስ ማርቲን ማን ናቸው………?

 

ከአባታቸው ከነጋድራስ እሸቴ ወልደማርያም እና ከእናታቸው ከወ/ ደስታ ጥቅምት 11 ቀን 1858. ጎንደር ከተማ ተወለዱ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ጦርነት ራሳቸውን ሲያጠፉ ከጄኔራል ናፒዬር ጦር ግማሹ ልዑል አለማየሁን ጨምሮ ወደ እንግሊዝ አገር ሲሄዱ እነ ኮለኔል ቻርለስ ቻምበርሌን ህንዳዊያን ወታደሮቻቸውንና ህፃን ወርቅነህን በአደራ ልጅነት ይዘው ወደ ህንድ ሀገር ተመለሱ፡፡ ህንድ እንደደረሱም የህፃን ወርቅነህ አሳዳጊ ቻምበርሌን ይሞታሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የቻምበርሌን ወዳጅ የነበረው ኮለኔል ማርቲን ህፃን ወርቅነህን እንዲያሳድግ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡

  
ህፃን ወርቅንህም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ “ፑንጃብ” በሚባል የህንድ ት/ቤት ሲገቡ ኢትዮጵያዊ ስማቸው ተለውጦ አሳዳጊያቸው ባወጡላቸው ስም “ቻርለስ ማርቲን” ተብለው ተመዘገቡ፡፡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ እዚያው ሀገር ውስጥ “ላሆሬ የህክምና ኮሌጅ /Lahore Medical College/” በ1879ዓ.ም የህክምና እና የቀዶ ጥገና ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም ህንድ አገር በሚገኘው “ጉርዳስፑር/Gurdaspur/” ከተማ ረዳት የቀዶ ጥገና ሀኪም ተብለው በባታል ሆስፒታል ሲሰሩ ቆዩ፡፡ በ1881ዓ.ም ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄደው በኤደንብራው እና ግላስኮ ዩኒቨርስቲዎች የህክምና ድህረ ምረቃ እና የመድሃኒት ቅመማ ተምረው ባገኙት የላቀ ውጤት ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ችሎታ ማስረጃ እና በርካታ ዲፕሎማዎችን ተቀብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእንግሊዝ ኤምባሲ ሰራተኞቹን የሚያክምለት ባለሙያ ይፈልግ ስለነበረ ሀኪም ወርቅነህ ተመርጠው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደገና በመምጣት ስራቸውን በ1900ዓ.ም ጀመሩ፡፡ የኤምባሲው ሀኪም ሆነው በመስራት በነሀሴ ወር 1901ዓ.ም ወደ ቤተ መንግስት ገቡ፡፡ በዚህ ስራ ላይ ለሶስት አመት አፄ ምኒሊክን ሲያክሙ ቆይተው በ1905ዓ.ም በሰኔ ወር ወደ በርማ ሄደው የህክምና ስራቸውን ቀጠሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በመመላለስ በልዩ ልዩ ሙያዎች አገልግለዋል፡፡

  በብላቴን ጌታ ህሩይ እና በአቶ ተክለሀይማኖት ድጋፍም የአማርኛ እና የጂኦግራፊ መፅሃፍ ፅፈው አሳትመዋል፡፡ በተጨማሪም በግላቸው ገንዘብ የአቃቂን ድልድይ እና በውሃ ግፊት የሚንቀሳቀስ የእህል ወፍጮ በወንዙ ዳር ተክለው ለአካባቢው ህዝብ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ የአሰሩትን ድልድይ የአካባቢው ማህበረሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “የሀኪም ወርቅነህ ድልድይ” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይወሳል፡፡ የቀድሞው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የአሁኑ እንጠጦጦ አጠቃላይ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ሚያዚያ 17 ቀን 1917ዓ.ም ሲከፈት ሀኪም ወርቅነህ የመጀመሪያው ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ በዚያን ዘመን የመምህር እጥረት ስለነበረም 21 ያህል ህንዳውያን መምህራንን በማስመጣት እንዲያስተምሩ አድርገዋል፡፡ እንግሊዝ አገር የተማረው ልጃቸው ቴዎድሮስ ወርቅነህም በዚሁ ት/ቤት የእንግሊዘኛ መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡
   
   ሀኪም ወርቅነህ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት አስተዳዳሪ ሆነው እየሰሩ ሳለ ሰኔ 24ቀን 1920ዓ.ም ልዩ ፍርድ ቤት ተመሰረተ፡፡ ይህ የነፃ ባሮችን እና የውጭ አገር ዜጎችን ጉዳይ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ሲቋቋም ሀኪም ወርቅነህ “አዛዥ” የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸው የዚህ ፍርድ ቤት ሹም ሆኑ፡፡ ይህን ስራ ከተፈሪ መኮንን ት/ቤት አስተዳዳሪነታቸው ጋር ለአራት አመት ደርበው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በመቀጠልም ጥቅምት 23 ቀን 1923ዓ.ም ተፈሪ መኮንን “ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ” ተብለው ዘውድ ደፉ፡፡ ንጉሰ ነገስቱ በጥር 1923ዓ.ም ላይ አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን የጨርጨር ገዥ ብለው በመሾም ወደ አሰበ ተፈሪ /የአሁኑ ጭሮ/ ላኳቸው፡፡ አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ በዚያ በነበራቸው ቆይታም ት/ቤት አሰርተው ንጉሱ በተገኙበት አስመርቀዋል፡፡

    ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ በእንግሊዝ ሀገር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ባለ ሙሉ ስልጣን መልዕክተኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በወቅቱም ጣሊያኖች በሀገራችን ላይ የፈፀሙትን ግፍና ጭቆና ለአለም ህዝብ ለማሳወቅ በማሰብ፣ በአካል በመገኘት እንዲሁም በሬዲዮ ንግግር በማድረግ እና በጋዜጣም በመፃፍ ከፍተኛ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ ሀኪም ወርቅነህ ከአፄ ምኒሊክ ጋር በነበራቸው ቅርበት በንግስት ዘውዲቱ በኩል ካገኟቸው ባለቤታቸው / ቀፀላወርቅ ቱሉ 13 ልጆችን ወልደዋል፡፡



    ሁለቱ ልጆቻቸው ማለትም ቢኒያም በመካኒካል፤ ዮሴፍ ደግሞ በሲቪል ምህንድስና በውጭ ሀገር ከተመረቁ በኋላ ወደ ሀገራቸው በመምጣት በጣሊያን ጦርነት ተሳትፈዋል፡፡ በጊዜውም ቢኒያም በአውሮፕላን ነጂነት፣ ዮሴፍ ደግሞ የሰራዊት አባል በመሆን ተመድበው አገልግለዋል፡፡ የካቲት 12ቀን 1929. አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አሰግዶም ግራዚያኒን ለመግደል ባደረጉት ሙከራ እናንተም ተሳትፋችኋል ደግሞም ከአባታችሁ ጋር ደብዳቤ ትላላኩ ነበር በማለት በግፍ ተገድለዋል፡፡

  አዛዥ ሀኪም ወርቅነህም ጣሊያን ከሀገራችን ከተባረረች በኋላ ቀሪ ጊዜያቸውን በሀገራቸው ለማሳለፍ ወሰኑ፡፡ በዚህ መሰረትም በሚያዚያ ወር1934ዓ.ም አዲስ አበባ ፒያሳ እሳት አደጋ አካባቢ ባለው ቤታቸው እየኖሩ ጥቅምት 20 ቀን 1945ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የአስተማሪ፣ በጎ አድራጊ ፣ ደራሲ እና ዲፕሎማት ሀኪም አዛዥ ወርቅንህ እሸቴ ስራና የህይወት ታሪክ እነዲህ በአጭሩ የሚያልቅ አይደልም፡፡ ለትውስታ እኔ ይህንን አወራኋችሁ ቀሪውን ደግሞ እናንተ ጨምሩበት …….. !!  

                        ምንጭ ፡- ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት


No comments:

Post a Comment