Monday, October 12, 2020

የቴአትር ምሁር፣ ደራሲና ተርጓሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ…

የመድረክ ፈርጥ፣ የተውኔት ፀሃፊ እና አዘጋጅ እንዲሁም ምሁር ናቸው፡፡ በሃገር ፍቅር እና በብሄራዊ ትያትር ቤት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩንቭርስቲ ባህል ማዕከል /ቤተ ኪነ ጥበባት ትያትር/ በሰራተኝነት እና በኃላፊነት ስርተዋል፡፡ ለረጅም አመታትም በመምህርነት ሙያ አገልግለዋል፡፡ በጥበቡ አለም 60 አመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን በእነዚህ አመታትም 100 በላይ የጥበብ ስራዎችን ለህዝብ አቅርበዋል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፡፡

 በ1929ዓ.ም በሀረርጌ  የተወለዱት ተሰፋዬ ገሠሠ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን የተማሩ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1951ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወደ አሜሪካ በመሄድ በቴአትር ጥበባት ተምረዋል፡፡ በውጪ ተምረው ከመጡ በኋላ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ /የአሁኑ ብሄራዊ ትያትር/ የመድረክ አስተባባሪ ወይም ስቴጅ ማናጀር ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

የጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን “የእሾህ አክሊል” ትያትርን በአዘጋጅነት እና በመሪ ተዋናይነት ሰርተዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በርከት ያሉ ስራዎች ላይ በተዋናይነት ፣ በደራሲነት እና አዘጋጅነት ተሳትፈዋል፡፡ ለአብነትም ፡-  

-    እዮብ     - ሀምሌት    -  ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት   -  የእሾህ አክሊል

-    ኡመር   - ፍርዱን ለእናንተ  - የገና ገበያ   - የሺ   - ቴዎድሮስ

-    አሉላ አባነጋ  - አጎቴ ቫኒያ  - ሮሚዮና ዡሌት  - ባለካባ እና ባለዳባ

-    ጠልፎ በኪሴ  - ላቀችና ማሰሮ   -  አባት እና ልጆቹ እና ተሀድሶ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጋሽ ተስፋዬ ከተውኔት ፀሀፊነት: አዘጋጅነት እና ተዋናይነት ባሻገር በጋዜጠኝነት ሙያም በኢትዮጵያ ሬዲዮ "በኪነ ጥበባት ጉዞ" እና በኢትዮጵያ ቴሌቭዝን "ህብረት ትርኢት" የተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ ሰርተዋል፡፡

 "ህልም እና እውነት" የተሰኘ የሬዲዮ ድራማ ድርሰታቸው 1988. በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቀረበ ሲሆን እነወጋየሁ ንጋቱተክሉ ምናሴየወንድወሰን ገብረየሱስ እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል፡፡ "አባት እና ልጆቹ" በተሰኘው ድርሰታቸው ደግሞ የፊልም ባለሙያ ሀይሌ ገሪማ(ፕሮፌሰር) ፣ ወንድወሰን ገብረየሱስ(ጋዜጠኛ) ፣  ታደሰ ሙሉነህ(ጋዜጠኛ) ፣ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ፣ አያልነህ ሙላት እና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከል/ቤተ ኪነ ጥበባት ወ ትያትር/ በሚመሰረትበት ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ እነ አባተ መኩሪያ ፣ ወጋየሁ ንጋቱ ፣ ደበበ እሽቱ ሌሎች አንጋፋ እና ወጣት የጥበብ ሰዎችን በሙያ ቀርፀዋል/አፍርተዋል/፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ "የመድረክ ተውኔት ነፍሱ ተዋናይ ነው" የሚል እምነትም አላቸው፡፡ በኪነ ጥበቡ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ባህል ማዕከልም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡


10 በላይ መፅሃፍትን ለአንባቢ አድርሰዋል፤ እነሱም ፡-

1.  ዕቃው (ተውኔት) 1961ዓ.ም

2.  መተከዣ (ግጥም እና አጭር ልቦለድ) 1967ዓ.ም

3.  መልክአ ዑመር (አዛማጅ ትርጉም) በ1986ዓ.ም

4.  የወጣቱ ቨርተር ሰቀቀኖች (ትርጉም) 1997 ዓ.ም

5.  የዑመር ኻያም ታሪካዊ ልቦለድ (አዛማጅ ትርጉም) 1999ዓ.ም

6.  ጥንወት (ልቦለድ) 2000ዓ.ም

7.  ጎህ ሲቀድ (የግጥም መድብል) 2001ዓ.ም

8.  ሽልማቱ (ልቦለድ) 2002ዓ.ም

9.  ይሉኝታ እና ፍቅር (ልቦለድ) 2002ዓ.ም

10.  ረጅም ጉዞ ወደ ነፃነት (ትርጉም) 2009ዓ.ም

11.  የመጨረሽታ መጀመርታ (ልቦለድ) 2010ዓ.ም

12.  አሰብ እና ክበር (አዛማጅ ትርጉም) 2011ዓ.ም

13.  መደበሪያ (ልቦለድ) 2013 ዓ.ም - ይህ መፅሃፍ የ84 አመታቸውን ባከበሩበት ወቅት ለአንባቢያን ያበቁት ነው፡፡ ከእሳቸው ጋር ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍ መፅሃፍ ገልጦ እንደማንበብ ይቆጠራል፡፡  እኔም ይህን እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በነበረችን ጥቂት ደቂቃዎች ብዙ እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ ግለ ታሪካቸው በሌላ ሰው እየተፃፈ እንደሆነ ሹክ ብላኛል፡፡ እሱ ለንባብ ሲበቃ ስለ እሳቸው ብዙ ነገር እናገኛለን ብዬም አስባለሁ፡፡ ከእሳቸው ስራዎች እና የህይወት ልምድ እኔ በጥቂቱ አጋራኋችሁ፤ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት….  

No comments:

Post a Comment