Monday, March 2, 2020

አቶ ውብሸት ወርቃለማው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡


  በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ፈር ቀዳጅ የነበሩት አቶ ውብሸት አንበሳ የተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት በመክፈት ለሙያው ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ውብሸት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል በመሆን አገራቸውን በመወከል የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነትን በማሻሻሉ  እና በአገር ሽማግሌነት ለሕዝብና ለአገር ፋይዳ ያላቸው በርካታ ሥራዎችን በብቃት ሲሰሩ ቆይተዋል። ለዛ ባለውና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ይታወቃሉ። ለወጣት የማስታወቂያ ባለሙያዎች አርአያ በመሆናቸው ብዙዎች ያከብሯቸዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎችን ሰርተዋል።
 አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ የተወለዱት መንዝ በቀድሞው ይፋት አውራጃ ማፉድ ገበያ አንቃውሃ በተባለ አካባቢ ነው። የትውልድ ዘመኑን የሚያስታውሱት ከታሪክ ግጥጥሞሽ ጋር በማያያዝ እንጂ በስንት ዓመተ ምህረት እንደሆነ በውል አያስታውሱትም። እናም በወርሃ መስከረም ጃንሆይ ድል አድርገው ከገቡ በኋላ እንደተወለዱ ከእናታቸው መስማታቸውን ይናገራሉ። የግለታሪክ መፅሃፋቸው ደግሞ 1934 . እንደተወለዱ ይናገራል። አቶ ወብሸት ወርቃለማው ለቤተሰቦቻቸው የመጨረሻ/ሰባተኛ/ ልጅ ሲሆኑ በቤት ውስጥ የቤተክህነት ትምህርት አስተማሪ ተቀጥሮላቸው ቅስና፣ ዳዊት መደገም እና ዜማን ተምረዋል። የትምህርት አቀባበላቸው ጥሩ ነበርና እድሜያቸው አስር ሳይደርስ ማፉድ ደብረኃይል ቅዱስ ሚካኤል ደብር በዲቁና አገልግለዋል፡፡ ዲያቆን እያሉ ግን አንድ ቀን በተወለዱበት አካባቢ ማፉድ ገበያ ያለው ክንውን ቀልባቸውን ይስበዋል። የገበያው ትርምስ፣ የሸማች እና ሻጭ አለመገናኘት በአጠቃላይ የቀያቸው ንግድ ቀልባቸውን ቢስበው አንድ መላ ይዘይዳሉ።
 ረጅም ሰው በረዳትነት በማቆም ገዢና ሻጩን እያገናኙ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማሰብ ስራውን ጀመሩት። አብሯቸው የሚሰራው ደግሞ ሁለት ሜትር ከአስር ሳንቲሜትር ርዝመት ያለው ቁመተ መለሎ ሰው ነበር። በማፉድ ገበያ አንድ ጠዋት ረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ ወጥተው «ይህን ያህል ሰንጋ፣ ይህን ያህል ጤፍ፣ ሁሉም በየአይነቱ ገብቷል» በማለት የመጀመሪያውን ማስታወቂያ በአየር ላይ አዋሉ። በማስታወቂያው የተሳበው ሸማች የትነው ያለው እያለ ከሻጭ ጋር እየተገናኘ ግብይቱ ሲጧጧፍ ዋለ። መጠነኛ ገቢም ከሻጮች በመቀበል የዕለት የማስተዋወቅ ውሏቸውን አጠናከሩት።
 በድቁና ስራቸው በዓመት አምስት ማርትሬዛ የሚያገኙት አቶ ውብሸት፤ በማፉድ ገበያ የሆሳዕና ዕለት በሰሩት የማስታወቂያ ስራ ብቻ ከአጋራቸው ጋር አስር ማርትሬዛ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ሲሸከሟቸው ለሚውሉት ቁመተ መለሎ የተወሰነውን ማርትሬዛ በመስጠታቸውና እርሳቸውም እኩል መካፈል አለብኝ በማለታቸው ትብብራቸው መፍረሱን ያስታውሳሉ።ይህ ደግሞ ሰው ትክሻ ላይ ወጥተው ማስታወቂያ ከመስራት ይልቅ ወደ ጽሁፍ ማስታወቂያ እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል። አጤፋሪስ እና የከሰል ድቃቂ አቀላቅለው ለሶስት ቀን በማቡካት ያገኙትን ቀለም የፍየል ቆዳ አስወጥረው መፃፍ ጀመሩ። በገበያው በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ ቆዳውን በአጋም እሾህ ይወጥሩትና የገባውን እህል እና ሰንጋ ብዛት እየጻፉ ማስተዋወቁንም ተያያዙት። ቆዳው በየሳምቱ ቅዳሜ ዕለት ይታጠብና ሌላ ማስታወቂያ ይጻፍበታል። እንዲህ እንዲህ እያሉ የማስታወቂያ ስራ ታዋቂነታቸውን በመንዝና ይፋት አካባቢዎች አሰፉት። ከዚያም በሀገር አቀፍ ደረጃ የብሄራዊ ሎተሪ ፣ፊሊፕስ ማስታወቂያዎችን ሰሩ፡፡ በግላቸውም አንበሳ የማስታወቂያ ድርጅትን አቋቁመው የአቢሲኒያ እና መድህን ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ማስታወቂያዎችን ሰርተዋል፡፡  
 ከትውልድ አካባቢያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተስፋ ኮከብ የተባለ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት አቶ ውብሸት፤ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ሙዚቃ እና ቴአትር መማር ጀመሩ። በወቅቱ ፈረንሳይ አገር ተምረው የመጡት የቴአትር ባለሙያው አቶ ማቴዎስ በቀለ ነበሩ የሚያስተምሯቸው። እናም አንድ ተውኔት ተዘጋጅቶ የሀብታም ልጅ ገፀ ባህሪን ተላብሰው እንዲጫወቱ ተመረጡ። በወቅቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሃረርጌ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስላቋቋመ አቶ ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ድሬዳዋ እንዲሄዱ ተደረገ።
 በሁለት ዓመት የሃረርጌ ሀገር ፍቅር ቆይታቸውም ጭሮ፣ ገለምሶ፣ ኦጋዴን እና ቀብሪደሃር የመሳሰሉ አካባቢዎችን በመዘዋወር በርካታ ቴአትሮች ላይ ሰሩ። ከቴአትር ስራቸው በተጓዳኝ መድረክ መሪም ነበሩ። በመድረክ ላይ ቀልድ እና እያዋዙ በሚያቀርቡት መልዕክት ታዳሚዎቹን ያስደምሙ ነበር። በዚህም ብዙዎች መድረክ በመምራት ሙያ እንዲገፉበት ያበረታቷቸዋል። የሃረርጌው ሀገር ፍቅር ከሁለት ዓመት በኋላ ሲፈርስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ዳግም ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተቀላቀሉ።
በዚህ ቴአትር ቤት በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ከወጋየሁ ንጋቱ እና አንጋፋ ተዋናዮች ጋር የመስራት እድልን አግኝተዋል። በቴአትር ክፍሉም በተዋናይነት፣ በደራሲነት እና በመድረክ አስተዋዋቂነት ሰርተዋል።በሀገር ፍቅር መድረኮች የአፄ ኃይለስላሴን ገጸባህሪ ወክለው በመተወን ከንጉሱ ጭምር አድናቆትን ያተረፉት አቶ ውብሸት፤ ቴአትሩን በሚሰሩበት ወቅት መልካቸውም ሆነ ሁለመናቸው ንጉሱን ስለሚመስል ታዳሚዎች ልክ እንደ ንጉሱ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት እና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች በሁለት ቡድኖች ሆኖ ቻይና እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሲሄዱ እርሳቸውም ተጓዥ ነበሩ። በዚህም ለሁለት ወራት ያክል በየመድረኮቹ በመምራት ብቃታቸውን አስመስክረዋል። ከስራቸው በኋላ ማታ ማታ መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ውብሸት፤ በስራ ቦታቸው ላይ ደረጃቸውን እያሳደጉ በቴአትር ቤቱ እስከ ምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰው እንደነበር ይናገራሉ። ቴአትር ቤቱን ለቀው ሲወጡም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የማስታወቂያ ባለሙያነት ተቀጠሩ። ከቴአትር ሙያቸው ጋር በተያያዘ «እኔና ሰባት ገረዶቼ፣ ማን መክቶት፣ 3 1 የጥንቆላው መዘዝ፣ ውለታ በጥፊ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ እና ባሻህ ዘመኑ» የተባሉ ድርሰቶችን አዘጋጅተዋል። ሰባት የቴሌቪዥንና ሁለት የመድረክ ስራዎችንም አቅርበዋል። «የክትነሽ» የሚል ፊልም ደግሞ በአሜሪካን ስቱዲዮ አቀናብረው ለእይታ አብቅተዋል።
አቶ ውብሸት የበጎ አድራጎት ተግባርን የጀመሩት በወጣትነት እድሜያቸው ነው። 1977 . በድርቁ ወቅት «ስጋውን ብሉ ቆዳውን አምጡ» በማለት በእርድ ወቅት ቆዳዎችን ለእርዳታ ለማዋል ያሰባስቡ ነበር። ለገና በዓል ከፊታውራሪ አመዴ ለማ እና ከተለያዩ ወጣቶች ጋር በመሆን በአንድ ቀን ከቆዳ ገቢ የሰበሰቡትን 77 ብር ለድርቅ ተጎጂዎች መለገሳቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም ሳያበቁ ሰዎች ለድርቅ ድጋፍ እንዲለግሱ የገንዘብ ሳጥን አዘጋጅተው በየመንገዱ በመዞር ገቢ አሰባስበዋል።
በወቅቱ የአንገታቸውን ወርቅ እና የያዙትን ሁሉ የሰጧቸው ሩህሩህ ሰዎች መኖራቸውንም አይዘነጉትም። የእርሳቸውን ፈለግ የሚከተሉ ተማሪዎችን ከተኩ በኋላ የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባሩን ለሌሎች ወጣቶች አስተላልፈዋል። ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ደግሞ አባያ ሐይቅ ሞልቶ አካባቢውን በጎርፍ ሲያጥለቀልቅ አቶ ውብሸት ለወገን ደራሽ ነበሩ። የአራት ነገስታትን ፎቶ አሰርተው ፎቶዎቹን ለቴሌቶን ጨረታ በማቅረብ ከመቶ ብር በላይ በመሸጥ ለተፈናቃዮች አበርክተዋል።
 ከ11 ዓመታት በፊት በድሬዳዋ አሰቃቂ የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥምም በሙያቸው ተጎጂዎችን አገልግለዋል። የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በሸራተን ሆቴል ቴሌቶን ሲያዘጋጅ መድረኩን በመምራት በአንድ ቀን 125 ሚሊዮን ብር ቃል እንዲገባ አድርገዋል። ቃል የተገባው ገንዘብ እንዲሰጥ ሌት ተቀን በመስራት አንድ መቶ ሚሊዮን ብሩ እንዲገኝ ጥረዋል። ድሬዳዋ ድረስ ሄደውም ለተጎጂዎች የተሰሩትን ቤቶች እና ዳግም ጎርፍ እንዳይመጣ የሚከላከለውን ግድብ በመጎብኘት ቃል የተገባው ገንዘብ የዋለበትን ስራም ገምግመዋል። በቅርቡ ደግሞ የብሔራዊ ደም ባንክ የክብር አምባሳደር በመሆን ዜጎች በደም እጦት ምክንያት እንዳይሞቱ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። በየጊዜው ደም በመለገስ ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ። «ደም በመለገሴ የሰው ህይወት ተርፏል» የሚለውን ማስታወቂያ በእራሳቸው ወጪ ከነዜማው አዘጋጅተዋል። የደም ባንክን ብቻ ሳይሆን ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ በጎ ምግባሮች የሚውሉ ማስታወቂያዎችን ያለክፍያ ማዘጋጀታቸውን የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።
በርካታ የሙያ ልጆችን በማፍራት ሳይሰለቹ ሰርተዋል። እነ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሙሉአለም ታደሰ፣ ጥላሁን ጉግሳ እና ሌሎችም አርቲስቶችን በሙያቸው ቀርፀው ለአገር አበርክተዋል። እነርሱም «የማስታወቂያ ስራ አባታችን» እያሉ በተደጋጋሚ ይጠሯቸዋል። ከማስታወቂያው ጎን ለጎን ደግሞ በንግድ ምክር ቤቶች ተሳትፎ አድርገዋል። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኮሚቴ አባል ሆነው ሰርተዋል። በዓመቱ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት ሆነው ያለደመወዝ አገራቸውን አገልግለዋል። በወቅቱ ከቤልጂየም፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከጅቡቲ እና ከዱባይ ጋር ሰባት የተለያዩ ስምምነቶችን በመፈራረም የንግድ ግንኙነት እንዲካሄድ መንገድ ያበጁ ናቸው። በዚህም የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በስራቸው ተደስቶ መኪና ሸልሟቸዋል።
  ከበርካታ ሽልማቶቻቸው መካከል ጥቂቶቹ፡-
1.  በቴአትር ጥበባቸው ጃንሆይን መስለው ሲሰሩ አፄ ኃይለስላሴ ካባ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።
2.  በንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነታቸው ደግሞ የሳዑዲ መንግስት የንጉሳቸውን ምስል የያዘ ነጭ ወርቅ ሸልሟቸዋል።
3.  አውሮፓ ልዑክ መርተው ሲሄዱም እንዲሁ የወርቅ ማንኪያ ተበርክቶላቸዋል።
4.  በማስታወቂያ ስራቸው ጣሊያን ጎልድ ሜርኩሪ ኢንተርናሽናል የክብር ሽልማት ሰጥቷቸዋል።
5.  .. 1981 ቬንዙዌላ ካራካስ በተዘጋጀ ሽልማት ከአፍሪካ «The first African in Advertisement & public relation» በሚል ዘርፍ ተሸላሚም ናቸው።
6.  የመካከለኛው ምስራቅ የማስታወቂያ ማህበር «የአገሩን ምርቶች የሚያኮራ ባለሙያ» በሚል በወቅቱ ብርቅ የነበረውን የምስል እና ድምጽ ማጫወቻ መሳሪያ ሸልሟቸዋል።
7.  የአሜሪካ ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት ደግሞ ..1989 18 ዓይነት የማስታወቂያ ማስተላለፊያ መንገዶች የሚሰራ ሰው ብሎ ልዩ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
8.  እስራኤል እና ጀርመን ላይ በስራቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። የጉማ ሽልማት 2010 . የህይወት ዘመን ተሸላሚ ናቸው።
9.  ስለስራቸው ድካም እና ጥረት እውቀና ለመስጠት «ለመድረስ» የተሰኘ ፊልም ማስተዋሻነቱ ለእርሳቸው ተደርጓል።
10.  6ኛው ጉማ የፊልም ሽልማት ላይም የህይወት ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
 ሁልጊዜም ወደውጭ አገራት ሲጓዙ አዋዜ እና የአገር ባህል ልብስ እንዲሁም ካባ አይለየኝም የሚሉት አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ፤ 45 አገራትን የማየት እድል አጋጥሟቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ የሚመቻቸውና የሚናፍቁት አገር ግን እንደሌለ ስሜት በተቀላቀለበት ንግግራቸው ያስረዳሉ። በአጠቃላይ ጋሽ ውብሸት ወርቃለማው በባህል አምባሳደርነት እና በሀገር ሽማግሌነት ለሀገራቸው እና ለህዝባቸው የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ባደረባቸው ህመም በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ21/6/2012ዓ.ም ምሽት ላይ ህይወታቸው አልፏል፡፡
አቶ ውብሸት ወርቃለማው የሁለት ወንድ ልጆች አባትም ነበሩ፡፡ ለእሳቸው ዕረፍተ ነፍስን፤ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና አድናቂዎቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
                                             ምንጭ ፡- አዲስ ዘመን

No comments:

Post a Comment