Monday, June 15, 2015

ወይ ሰኞ ገበያ………. !!!


   የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በአማራ ክልላዊ ምንግስት ከተቋቋሙት ልዩ የብሄረሰብ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በ1986ዓ.ም አጋማሽ የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም ሁለት የከተማ መስተዳድሮች እና አምስት የገጠር ወረዳዎችን አቅፏል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ከሚሴም ከአዲስ አበባ በደሴ መስመር በ325 ኪ፣ሜ ከባህር ዳር ደግሞ በወልዲያ መስመር 555 ኪ.ሜርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አብዛኛው ህዝብ ኦሮሞ ሲሆን የአማራ ፣ የአርጎባ እና የአፋር ብሄረሰቦችም በዞኑ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የዞኑ የስራ ቋንቋም ኦሮምኛ ነው፡፡

 
  በኦሮሞ ዞን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ገበያዎች ቢኖሩም የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የባቲ እና የሰንበቴ ገበያዎች ናቸው፡፡ከኮምቦልቻ ጅቡቲ በሚወስደው መንገድ 41 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የባቲ ከተማን እናገኛለን፡፡ ባቲ በተለያዩ የዘፈን ቅኝቶች ብዙ የተባለላት ታሪካዊ እና ዕድሜ ጠገብ ከተማ ነች፡፡ በተለይ ባቲ ከምትታወቅባቸው መካከል አንዱ ገበያዋ ሲሆን ከመርካቶ ቀጥሎ የሚገኝ ትልቅ ገበያም እንደሆነ ይነገርላታል፡፡


   ዘወትር ሰኞ ሰኞ የሚውለው የባቲ ገበያ የአርጎባ ፣ የአማራ ፣ የኦሮሞ እና የአፋር ብሄረሰቦችን ያገናኛል፡፡ ብሄረሰቦቹ ከእነ አለባበሳቸው እና አጋጌጣቸው በስፋት በገበያው ላይ መገኘታቸው ለጎብኚዎች ትልቅ እርካታን ይፈጥራል፡፡ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተሰራው የሰው መስቀያ ብረትም በገበያው መሀል ቆሞ ይገኛል፡፡ ይሄም የዘመኑን ታሪካዊ ገፅታ የሚያሳይ ቅርስ ነው፡፡


   ዘወትር እሁድ እሁድ የሚውለው የሰንበቴ ገበያም የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ያገናኛል፡፡ ይህም የባህል ትስስር እና ልውውጥን ከመፍጠሩም ባሻገር የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል፡፡

No comments:

Post a Comment