ህፃን ወርቅንህም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ “ፑንጃብ” በሚባል የህንድ ት/ቤት ሲገቡ ኢትዮጵያዊ ስማቸው ተለውጦ አሳዳጊያቸው ባወጡላቸው ስም “ቻርለስ ማርቲን” ተብለው ተመዘገቡ፡፡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ እዚያው ሀገር ውስጥ “ላሆሬ የህክምና ኮሌጅ /Lahore Medical College/” በ1879ዓ.ም የህክምና እና የቀዶ ጥገና ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም ህንድ አገር በሚገኘው “ጉርዳስፑር/Gurdaspur/” ከተማ ረዳት የቀዶ ጥገና ሀኪም ተብለው በባታል ሆስፒታል ሲሰሩ ቆዩ፡፡ በ1881ዓ.ም ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄደው በኤደንብራው እና ግላስኮ ዩኒቨርስቲዎች የህክምና ድህረ ምረቃ እና የመድሃኒት ቅመማ ተምረው ባገኙት የላቀ ውጤት ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ችሎታ ማስረጃ እና በርካታ ዲፕሎማዎችን ተቀብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእንግሊዝ ኤምባሲ ሰራተኞቹን የሚያክምለት ባለሙያ ይፈልግ ስለነበረ ሀኪም ወርቅነህ ተመርጠው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደገና በመምጣት ስራቸውን በ1900ዓ.ም ጀመሩ፡፡ የኤምባሲው ሀኪም ሆነው በመስራት በነሀሴ ወር 1901ዓ.ም ወደ ቤተ መንግስት ገቡ፡፡ በዚህ ስራ ላይ ለሶስት አመት አፄ ምኒሊክን ሲያክሙ ቆይተው በ1905ዓ.ም በሰኔ ወር ወደ በርማ ሄደው የህክምና ስራቸውን ቀጠሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በመመላለስ በልዩ ልዩ ሙያዎች አገልግለዋል፡፡
በብላቴን ጌታ ህሩይ እና በአቶ
ተክለሀይማኖት ድጋፍም የአማርኛ እና የጂኦግራፊ መፅሃፍ ፅፈው አሳትመዋል፡፡ በተጨማሪም በግላቸው ገንዘብ የአቃቂን ድልድይ እና
በውሃ ግፊት የሚንቀሳቀስ የእህል ወፍጮ በወንዙ ዳር ተክለው ለአካባቢው ህዝብ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ የአሰሩትን ድልድይ
የአካባቢው ማህበረሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “የሀኪም ወርቅነህ ድልድይ” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይወሳል፡፡ የቀድሞው ተፈሪ
መኮንን ት/ቤት የአሁኑ እንጠጦጦ አጠቃላይ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ሚያዚያ 17 ቀን 1917ዓ.ም ሲከፈት ሀኪም ወርቅነህ የመጀመሪያው
ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ በዚያን ዘመን የመምህር እጥረት ስለነበረም 21 ያህል ህንዳውያን መምህራንን በማስመጣት እንዲያስተምሩ
አድርገዋል፡፡ እንግሊዝ አገር የተማረው ልጃቸው ቴዎድሮስ ወርቅነህም በዚሁ ት/ቤት የእንግሊዘኛ መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡
ሀኪም ወርቅነህ በተፈሪ መኮንን
ት/ቤት አስተዳዳሪ ሆነው እየሰሩ ሳለ ሰኔ 24ቀን 1920ዓ.ም ልዩ ፍርድ ቤት ተመሰረተ፡፡ ይህ የነፃ ባሮችን እና የውጭ አገር
ዜጎችን ጉዳይ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ሲቋቋም ሀኪም ወርቅነህ “አዛዥ” የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸው የዚህ ፍርድ ቤት ሹም ሆኑ፡፡
ይህን ስራ ከተፈሪ መኮንን ት/ቤት አስተዳዳሪነታቸው ጋር ለአራት አመት ደርበው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በመቀጠልም ጥቅምት 23 ቀን
1923ዓ.ም ተፈሪ መኮንን “ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ” ተብለው ዘውድ ደፉ፡፡ ንጉሰ ነገስቱ በጥር 1923ዓ.ም
ላይ አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን የጨርጨር ገዥ ብለው በመሾም ወደ አሰበ ተፈሪ /የአሁኑ ጭሮ/ ላኳቸው፡፡ አዛዥ ሀኪም ወርቅነህ
በዚያ በነበራቸው ቆይታም ት/ቤት አሰርተው ንጉሱ በተገኙበት አስመርቀዋል፡፡
አዛዥ ሀኪም ወርቅነህም ጣሊያን ከሀገራችን ከተባረረች በኋላ ቀሪ ጊዜያቸውን በሀገራቸው
ለማሳለፍ ወሰኑ፡፡ በዚህ መሰረትም በሚያዚያ ወር1934ዓ.ም አዲስ አበባ ፒያሳ እሳት አደጋ አካባቢ ባለው ቤታቸው እየኖሩ ጥቅምት
20 ቀን 1945ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የአስተማሪ፣ በጎ አድራጊ ፣ ደራሲ እና ዲፕሎማት ሀኪም አዛዥ ወርቅንህ እሸቴ
ስራና የህይወት ታሪክ እነዲህ በአጭሩ የሚያልቅ አይደልም፡፡ ለትውስታ እኔ ይህንን አወራኋችሁ ቀሪውን ደግሞ እናንተ ጨምሩበት ……..
!!
ምንጭ ፡- ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት
No comments:
Post a Comment