Monday, June 22, 2015

እነሆ ስጦታ……… ከሸዋንዳኝ ሀይሉ !!!



      በእነ ለንደን ቢት ቦብ ማርሌ እና አርኬሊ ሙዚቃን አሀዱ ያለው አርቲስት ሸዋንዳኝ የአማርኛ ሙዚቃ ዳዴው የእነ ግርማ በየነ ጌታቸው ካሳ እና ዳዊት መለሰ ስራዎች ነበሩ፡፡ ከዚያም በሳቂልኝ እና ስጦታሽ አልበሞቹ ከወዳጅ እና አድናቂዎቹ ጋር ተገኛኝቷል፡፡ .. 2004 በኮራ የሙዚቃ ሽልማት በወንዶች ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ወክሎ 3ኝነት ደረጃን አግኝቷል፡፡

   ሙዚቃን ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ በሴንት ጆሴፍ ት/ቤት ነበር የጀመረው፡፡ በዚህ ት/ቤትም የተለያዩ የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን በመጫወት ለሁለት አመታት ያህል ሰርቷል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሙዚቃን ይጫወት የነበረው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ከአባቱ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞት እስከ መኳረፍ ደርሶ ነበር፡፡ በዚህም ከቴዲ አፍሮ ጋር ቤት ተከራይተው ለሶስት አመት ያህል አብረው ኖረዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ሸዋንዳኝ “ስቅ አለኝ” እና “ስጦታሽ” የተሰኙትን አልበሞቹን ሲያወጣ ቴዲ አፍሮ በርከት ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን ሰጥቶታል፡፡
  

  “ስቅ አለኝ” አልበሙ ከአባቱ ጋር ያስታረቀው ሲሆን እሳቸውም ደውለው አበረታተውታል፡፡ ከዚህ አልበም በኋላም ግብፅ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ዱባይ ፣ አቡዳቢ ፣ ባህሬን ፣ እስራኤል ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ ቡፌ ድላጋር ፣ የቀድሞው ላየን ክለብ ፣ ኮፊ ሀውስ ፣ ሂልተን ፣ ሽራተን ፣ ኢሉዥን እና ሚሞ ክለቦች ሰርቷል፡፡ በኋላ ላይም እሱ እና ቴዲ አፍሮ ላየን ክለብ ይዘው በጋራ ይሰሩበት ነበር፡፡ በተጨማሪም በ1999ዓ.ም “ፋራናይት” የተሰኘ ክለብ ከጓደኞቹ ጋር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህም እዮብ መኮንን ፣ ፀደኒያ ገ/ማርቆስ ፣ ጆኒ ራጋ እና ሌሎችም ስራቸውን ያቀርቡበት ነበር ምንም እንኳን አሁን አገልግሎት ላይ ባይሆንም፡፡
  

  በሀገራችን ታዋቂ ከሆኑት አይቤክስ ፣ ኢትዮ ስታር ፣ ኤክስፕረስ ፣ መዲና ፣ አዲሰ ፣ ሌቫንስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ጋርም ሰርቷል፡፡ “አፍሮ ሳውንድ” ቴዲ አፍሮ ፣ ግሩም መዝሙር እና ሸዋንዳኝ ሀይሉ በጋራ የመሰረቱት ባንድ ነው፡፡ ስያሜውን ያወጣው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ሲሆን ባንዱ ለ10 ዓመት ያህል በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በጊዜውም እነ ኤልያስ መልካ ፣ ዳግማዊ አሊ ፣ ዳንኤል ክንደያ ፣ አሸናፊ አሊ እና ሁንአንተን የመሳሰሉ ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ 


  አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ “ስቅ አለኝ” የተሰኘ አልበሙን ከሰራ ከ8 ዓመት በኋላ “ስጦታሽ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ለአድናቂዎቹ  ጀባ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስራ ገና ሳይጀመር ቅድመ ክፍያ (ቀብድ) የኤሌክትራ ባለቤት አቶ ተሾመ በራሳቸው ፍላጎት ሰጥተውት የተሰራ አልበም ነው፡፡ አልበሙም 6 ዓመታትን ወስዷል፡፡


   እዚሁ አዲስ አበባ መስቀል ፍላወር የተወለደው አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ምስክያዞና ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሴንት ጆሴፍ እንዲሁም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሏል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታ የመጀመሪያ አመት ኬሚስትሪን ቢመርጥም ከአንድ አመት በኋላ ወደ ማኔጅመት በመቀየር ለሶስት አመት ተምሮ ሳይጨርስ “ዊዝድሮዋል” አድርጓል፡፡ አሁን ሙሉ ጊዜውን ለሙዚቃ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከሙዚቃው ውጪም ፊልም እና ግራውንድ ቴንስ ይወዳል፡፡ እግር ኳስ ከሀገር ውስጥ የቅድስ ጊዮርጊስ ፤ ከውጪ ደግሞ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ደጋፊ ነው፡፡ እኔ ይህን አልኩ እናንተ ደግሞ ቀሪውን ጨምሩበት…….

No comments:

Post a Comment