Monday, November 2, 2015

ልክ በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም ነበር የአፄ ምኒልክ ሐውልት የተመረቀው፡፡

  
   አዲስ አበባ ከተቆረቆረች ወዲህ በውስጧ ከቆሙት ሐውልቶች በቅድሚያ ከሚጠቀሱት አንዱ የአፄ ምኒልክ ሐውልት ነው፡፡ ሐውልቱን ያሠሩት ንግሥት ዘውዲቱ ሲሆኑ የቆመው የአባታቸው የአፄ ምኒልክ ማስታወሻ እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ የሐውልቱን ንድፍ ያወጣው ጀርመናዊ አርክቴክት ሀርቴል ስፔንግለር ነበር፡፡ ሐውልቱም የተቀረፀው ጀርመን ሀገር ሲሆን የተሰራውም ከነሐስ ነው፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሀገር በማቅናቱና በፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግላቸው የታወቁ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ሐውልቱም ይህን ታሪካዊ ውሎአቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ የተቀረፀ ነው፡፡ በሐውልቱ ላይ አፄ ምኒልክ ካባ እንደለበሱ አንባር አጥልቀው በእጃቸው ጣምራ ጦር ይዘው በፈረሳቸውበአባ ዳኘውላይ ተቀምጠው በግርማ ሞገስ ይታያሉ፡፡ የሐውልቱ ቁመት ከተፈጥሮ አካላዊ መጠን በላይ ሲሆንአባ ዳኘውፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ በኋላ እግሮቹ ቆሞ፣ የፊት እግሮቹን ወደላይ አንስቶ ይታያል፡፡


  ሐውልቱ ከጀርመን ሃገር ተሠርቶ ከመጣ ወዲህ የሚቆምበት ቦታ በዝግጅት ላይ እያለ ንግሥት ዘውደቱ በድንገት መጋቢት 22 ቀን 1922 . አረፉ፡፡ ነገር ግን የተጀመረውን ሥራ የንግሥቲቱን አልጋ የወረሱት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲጠናቀቅ በማድረግ በንግሥናቸው በዓል ዋዜማ ጥቅምት 22 ቀን 1923 . በታላቅ ክብር በንጉሠ ነገሥቱ ተገለጠ፡፡ ስድስት ቀን የፈጀው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንግሥና በዓል የተጀመረው በአፄ ምኒልክ ሐውልት ምረቃ ሲሆን፣ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት፣ እንግዶች አንዱ የነበረው ኢቨሊን ዋህግ ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ በአንድ  መጽሐፉ ውስጥ እንደሚከተለው ገልፆታል፡፡የሃገር ተወላጅ የሙዚቃ ባንድም ሙዚቃ ያሰማ ጀመር፡፡ በአውቶሞቢል ንጉሡ መጡ፡፡ ... ንግግርም ካደረጉ በኋላ ገመዱን ስበው ሐውልቱ የተሸፈነበትን አረንጓዴውን ሐር ገለጡ፡፡ ከሐውልቱም ግርጌ ዘመን የማይሽረው ጥቅስ የተቀረፀ ሲሆን እንዲህም ይነበባል፡-

 ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው፡፡


  1928 . ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ አዲስ አበባን ከያዘ በኋላ ቤኔቶ ሙሶሊኒ በፋሽስት ፖሊሲው መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያን ነፃነት የሚያንፀባርቅ ማስታወሻ ለማስወገድ በተንቀሳቀሰበት ጊዜ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት የአድዋ ጦርነት ማስታወሻና የጣሊያኖች ሽንፈት ምልክት ስለነበር በዚሁ የፋሽስቶች ዘመቻ ዒላማ ውስጥ ገባ፡፡ ማርሻል ባዶልዮ አዲስ አበባ እንደገባ ሙሶሊኒ ከሮም ባስተላለፈለት መልዕክት የአፄ ምኒልክን ሐውልት እንዲያፈርስ አሳስቦት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባዶሊዮ ትዕዛዙን ከማስፈፀሙ በፊት በግራዚያኒ ስለተተካ የማፍረሱ ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ዘገየ፡፡ ሙሶሎኒ ጊዜ ሳያጠፋ በቅኝ ግዛት ሚኒስትር በነበረው በሌሶና በኩል ለግራዚያኒ የሚከተለውን ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡

  የምኒልክና የይሁዳ አንበሳ ሐውልቶች በሃያ አራት ሰዓት እንዲፈርሱግራዚያኒም ምንም እንኳን ሐውልቶች ከግዙፍነታቸው የተነሣ ለማፍረስ የቴክኒካል ችግር ቢኖርም በትዕዛዙ መሠረት እንደሚፈፀም ያረጋግጣል፡፡ ነገር ግን የማፍረሱ ሥራ የጣሊያኑ የቅኝ ግዛት ሚኒስትር ሌሶና እና የሥራ ሚኒስትሩ ችቦሊ ጊገሊ ባሉበት እንዲፈፀም ስለተወሰነ ለብዙ ወራት ዘግይቶ ባለሥልጣኖቹ በተገኙበት የማፍረሱ ሥራ ማታ ጥቅምት 16 ተጀምሮ ንጋቱ ላይ 17/1936 .. ተጠናቀቀ፡፡ ብርሃኑ ድንቄየአምስቱ የመከራ ዓመታት አጭር ታሪክበሚለው መጽሐፋቸው ጣሊያኖች የአፄ ምኒልክን ሐውልት እንዴት እንዳፈረሱት እንደሚከተለው ገልፀውታል፡፡

  በቅድሚያ ሐውልቱ ያለበትን አካባቢ ረጅም እንጨት እየማገሩ በቆርቆሮ ሲያጥሩ ሰነበቱ፡፡ ይህንን ያየው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሊያፈርሱት ነው ብሎ እርስ በእርሱ በሐዘን መነጋገሩን ቢሰሙልናድስነው ብለው አስወሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ካመቻቹ በኋላ ግን በየበሩ ጥበቃውን አጠናክረው ... ወደ ማታ የአራዳን አካባቢ በታንክ አጥረው በባውዛ ሌሊቱን ከተማውን እየተቆጣጠሩ በሌላ ኃይል ደግሞ ሐውልቱን ሲያፈርሱ አድረው ሲነጋጋ ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው ቀበሩት፡፡ ሕዝቡ እድሜና ፆታ ሳያግደው ሐዘኑን ይገልጽ እንደነበር አዛውንቶች ይመሰክራሉ፡፡ በጊዜው የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበረው የሃንጋሪው ዶክተር ላዲ ስላስ ላቫ እንደፃፈው ሐውልቱ ከፈረሰበት ቦታ ቆመው ያለቅሱ የነበሩትን ሰዎች የጣሊያን ወታደሮች በኃይል ይበትኑ እንደነበር ገልፆአል፡፡ በሌላ ዘገባ ደግሞ አንድ ሕፃን ልጅ ሲያለቅስ ጣሊያኖች ደርሰው ለምን እንደሚያለቅስ ቢጠይቁትየንጉሱን ምልክት ስላወረዳችሁ ነውብሎ እንደመለሰላቸውና ጣሊያኖችም ከሙሶሊኒ ሌላ ንጉሥ እንደሌለው በመንገር ልጁን ገርፈው እንዳባረሩት ተገልጿል፡፡


   ጣሊያኖች የኢትዮጵያ ነፃነት ምልክት የሆኑትን ሐውልቶች በማፈራረስ ግማሾቹንም ወደ ጣሊያን አግዞ በመውሰድ የኢትዮጵያዊያንን የነፃነት መንፈስ ለመስበርና የጣሊያንን የበላይነት በሕዝቡ መሀል ለማስረፅ ይታገሉለት የነበረው ዓላማ ሳይሳካ ቀረ፡፡ በመጨረሻም በአርበኞች ትግልና በእንግሊዞች እርዳታ ተሸንፈው ሀገር ለቀው ወጡ፡፡ ከነፃነት በኋላም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ እንደገና ታድሶና ተጠግኖ ቀድሞ በነበረበት ቦታ ሚያዝያ 27 ቀን 1934 . እንዲቆም ተደረገ፡፡ 1988 . የአድዋ ድል መቶኛ ዓመት ሲከበር ሐውልቱ ጥገና የተደረገለት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment