Sunday, December 21, 2014

ጥቂት ስለ አርቲስት ሙሉ ገበየሁ ....

  
አርቲስት ሙሉ ገበየሁ ሙዚቃን የጀመረው ገና በህፃንነቱ ማይጨው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነበር፡፡ በት/ቤቱ ባሉ ክበባት ውስጥም ይሳተፍ ነበር፡፡ በተለይ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜን በጉት ነበር የሚጠባበቃት፡፡ 8ኛ ክፍልን አጠናቆ ሚኒስትሪ ከወሰደ በኋላ አስተማሪው ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት እንዲገባ እድሉን አመቻቹለትና ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እየተማረ እሱ ደግሞ ብርሃን ህይወት (የድሮው አሜሪካን ሚሽን የልጃገረዶች ት/ቤት) ሙዚቃን ያስተምር ነበር፡፡ በሳምንት እስከ 14ብር ድረስ ይከፈለው ነበርና በወቅቱ ጥሩ ገቢ ያለው (ሀብታም ተማሪ) ነበር፡፡
    በ1972ዓ.ም ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ሜጀሩን “ቫዮሊን” ማይነሩን ደግሞ “ፒያኖ” አድርጎ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ሙያና እውቀቱን ለማሻሻልም በ2000ዓ.ም በዚሁ ት/ቤት በባህላዊ ሙዚቃ ሜጀሩን እና ማይነሩን “ማሲንቆ እና ክራር” አድርጎ ድግሪውን አግኝቷል፡፡ በ1972ዓ.ም በወጣትነቱ በራስ ትያትር ቤት ተቀጥሮ በባለሙያነት እና በኃላፊነት የሙዚቃ ክፍሉን በማደራጀት እና በማጠናከር የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ በጊዜውም በርከት ያሉ አርቲስቶች ራስ ትያትር ገብተው ብዙም ሳይቆዩ ወደ ውጪ ስለሚሄዱ ለአርቲስት ሙሉ ገበየሁ “ባለሙያ አስመጪ እና ላኪ” የሚል ቅፅል ስም ወጥቶለት ነበር፡፡ ከግጥም ይልቅ ዜማን ያስቀድማል፡፡ በራስ ትያትር ቆይታውም በርካታ ግጥምና ዜማዎችን ደርሷል፡፡

አርቲስት ሙሉ ገበየሁ
  ግጥምና ዜማን /ሁለቱንም/ ከሰራላቸው ድምፃውያን መካከል፡-
  1.  ሰለሞን ተካልኝ እና አስቴር ከበደ - ከተራራው ወዲያ (በድጋሚ ኤፍሬም ታምሩ ተጫውቶታል)
   2.  ታደለ በቀለ - ሆዴ መላ
   3.  ነፃነት መለሰ - ልቤን ውሰደው እና መውደዴን
   4.  ይመኑ መንግሰቴ እና ኤልሳቤት - ጎፈሬ
   5.  ጁዲ ተፈራ - 3 ስራዎችን “ይሸመታል” ከሶስቱ ስራ አንዱ ነው
   6.  ትህትና ቢሰጥ - አትማል - 1998ዓ.ም የኢትጵያን አይዶል ተወዳዳሪ ነበረች፤ ለእነዚህ እና ለሌሎችም ግጥም እና ዜማ ደርሶ ሰጥቷል፡፡

 ዜማ ከሰራላቸው መካከል የተወሰኑትን እንጥቀስ፡-
   1.  ኤፍሬም ታምሩ - ከጓጓዘኝ (ግጥም - ይልማ ገብአብ)
   2.  አስቴር ከበደ - ፍቅር እንዳሰቡት  (ግጥም - ደበሽ ተመስገን)
   3.  ህፃናት በህብረት - ብሄር ብሄረሰቦች ( ግጥም - ቢኒያም ኃይለስላሴ)
   4.  ፋሲል ደሞዝ - 1 ስራ  የሺመቤት  - 2 ስራዎች - “ዘመዘመው” አንዱ ነው፡፡ ከእነዚህም ባሻገር   ፀሀዬ ዮሀንስ ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ፣ መሰረት በለጠ ፣ ኤልያስ ተባባል ፣ ሻምበል በላይነህ ፣ ትንሹ ድምፃዊ ፋሲል ሽመልስ  እና ዮዲት ዘለቀ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

     በብሄር ብሄረሰቦች መዝሙሩም ከህፃን እስከ አዋቂ በመላው ህብረተሰብ ዘንድ አድናቆትን እና ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ በዚህ ስራቸውም ከአዲሰ አበባ መስተዳድር አምስት አምስት ሺ እና ከኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ ሃያ አምስት ሃያ አምስት ሺ ብር ተሸልመዋል (የግጥም ደራሲው ቢኒያም ኃይለስላሴ እና የዜማ ደራሲው ሙሉ ገበየሁ)፡፡ በተጨማሪም ከ50 በላይ ለሚሆኑ ማስታወቂያዎች ዜማን ደርሷል፡፡ ከሚታወቁት መካከል እንኳን “ኪዊ የጫማ ቀለም” ፣ “ደስታ ከረሜላ” እና “ቸራሊያ ብስኩት” ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

   አርቲስት ሙሉ ገበየሁ በራስ ትያትር ቤት ቆይታው ልዩ ልዩ ሙዚቃዊ ድራማዎችን በመስራትም ተሳትፏል፡፡ “ጥንታዊት ኢትዮጵያ” ፣ “ከተማ” እና “ዘመን” የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በራስ ትያትር በጥናታዊ መንገድ ለተዘጋጀው “ላጤ” ትያትር ማጀቢያ የሚሆን የድምፅ ግብአት/Sound Effect/ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን አዘጋጅቷል፡፡
 
   ከ1972 -1986ዓ.ም ለ14 ዓመታት ያህል በራስ ትያትር ቤት ከቆየ በኋላ ወደ ህፃናት እና ወጣቶች ትያትር ቤት በፍቃዱ ተዛወረ፡፡ በዚህም ከምንም በመነሳት የሙዚቃ ክፍሉን በማጠናከረ እና በማደራጀት በርካታ ወጣት ባለሙያዎችንም አፍርቷል፡፡ በዚህም የሙያ አባት ለመባል ችሏል፡፡ በህፃናት እና ወጣቶች ትያትር ቆይታውም “የወላጆች ጌጥ” የሚል የህፃናት ካሴት ለመጀመሪያ ጊዜ አስተባብሮ አውጥቷል፡፡

  የኢትዮጵያ አይዶል ዳኛ በመሆንም ለሁለት አመታት ያህል ሰርቷል፡፡ በአዲስ አበባ መስተዳድር ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊም ነበር፡፡ አሁን በጡረታ ወጥቶ የግሉን ፕሮሞሽን ድርጅት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለግጥም እና ዜም ደራሲ ሙሉ ገበየሁ እድሜ እና ጤና በመመኘት እኔ በዚሁ አበቃሁ፡፡ በተረፈ እናንተ ጨምሩበት……

No comments:

Post a Comment