Sunday, December 21, 2014

አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ 287 ዶክተሮችን አስመረቀ

  
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ቤት ለ47ኛ ጊዜ በመጀመሪያ ህክምና ዲግሪ ያስለጥናቸውን 287 ዶክተሮች አስመርቋል፡፡ ኮሌጁ እያከበረ የሚገኘውን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግም ልዩ ተመራቂዎችንም አስመርቋል፡፡
  የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኮሌጁ ሀገራችን በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበችው ላለው ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዛሬ ተመራቂዎችንም በሀገራችን የጤና ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ለመክፍት መትጋት ይጠበቅባችኋል በማለት አሳስበዋል፡፡ 
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ በውጭ ሀገር ህክምና ለማግኘት የሚንከራተቱ ዜጎችን በሀገር ውስጥ እንዲታከሙ ለማስቻል ኮሌጁ ከዚህ በላይ ሊሰራ ይገባል ብልዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጀይሉ ኡመር ዩንቨርስቲው በአፍሪካ ግንባ ቀደምና የምርመር ተቋም ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በህክምናውም የጤና ሳይንስ ጥራትንና ተገቢነትን ለማሻሻል ኮሌጁ በለውጥ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
   የህክምና ትምህርት ቤቱ ዲን ዶክተር ማህሌት ይገረሙ በበኩላችው ኮሌጃችን በኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመራቂ ማስመረቁ ሀገራችን በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበችው ላለው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ኮሌጁ በድህረ ምረቃ ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን 5 ሙህራንንም አስመርቋል፡፡ አራቱ በከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና አንድ ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ በሆነው ፊዞሎጅ አስመርቋል፡፡
    ኮሌጁ በ1967፣ በ1968 እና በ1969 ዓ.ም በህክምና ትምህርት ቤቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይመረቁ ወደ ስራ የተሰማሩ ዶክተሮችን በልዩ የምረቃ ፕሮግራሙ አስመርቋል፡፡ በኮሌጁ ከሰላሳ ዓመት እስከ አርባ ዓመት ድረስ ያገለገሉ ከፍተኛ ሙሁራንን እና ኮሌጁን በዲንነት የመሩ የአመራር አካላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ኮሌጁ ካስመረቃቸው 287 የህክምና ባለሙያዎች መካከል 81 ሴቶች ናቸው፡፡
   የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ቤት ከተመሰረተበት 1957 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ2ሺህ በላይ የህክምና ምሁራንን አፍርቷል፡፡

No comments:

Post a Comment