Tuesday, September 30, 2014

ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ 95 ሚሊዮን ብር ያጭበረበረው ግለሰብ ተያዘ


  ከሰባት ዓመት በፊት ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ አጭበርብሮ የተሰወረውን ግለሰብ መያዙን የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ግብረሀይል አስታወቀ፡፡ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ ማጭበርበር ወንጀል ተከሶ የቅጣት ፍርድ የተበየነበት አቶ አስማረ አያሌው ደስታ ከተባበሩት የአረብ ኢምሬትስ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱን ግብረ ኃይሉ አረጋግጧል፡፡ በመስከረም19/2007 ለኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ግለሰብም ከዚህ በፊት እሱ በሌለበት የ25 ዓመት ፅኑ እስራትና የ180 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበት ነበር፡፡
  ተከሳሹ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሀሰተኛ የወርቅ ጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሀሰተኛ የላኪና አስመጪ የንግድ ፍቃድ ካዘጋጀ በኃላ ከባንኩ 95 ሚሊዮን 553 ሺህ 413 ብር ከ89 ሳንቲም አጭበርብሯል፡፡    
   በዚህም ግለሰቡ ከታህሳስ 1998 እስከ መጋቢት 1999 ባሉት ጊዜያት በውስጣቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረታ የያዙ 29 የታሸጉ ሳጥኖች ለብሔራዊ ባንኩ ሰጥቷል፡፡ ግለሰቡ ድርጊቱን መፈፀሙን ሲነቃበትም በኬንያ በኩል ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመሄድ ከተደበቀ በኃላ ፣በቁጥጥር ስር ውሎ በብሔራዊ ኢንተርፖል አማካኝነት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ወንጀለኛውን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
  አቶ አስማረ ከፍተኛ የሆነ የህዝብና የሀገር ሀብት በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ በጥብቅ ለ7 ዓመታት ሲፈለግ እንደነበርም ግብረ ሀይሉ ገልጿል፡፡ በማንኛውም መልኩ በሀገሪቱ ደህንነትና ጥቅም ላይ ጉዳት በመፈፀም ለማምለጥና ለመሰወር ጥረት የሚያደርጉ መሰል ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረባቸው እንደማይቀር አስታውቋል፡፡ የኢፌዲሪ መንግስት ለተባበሩት የአረብ ኢምሬት መንግስትና ህዝብ ላደረጉላት ትብብርና ድጋፍ ምስጋና አስተላልፎል ብሏል ግብረ ሀይሉ፡፡
                                         ምንጭ ፡- ኢ.ብ.ኮ/EBC/

No comments:

Post a Comment