Thursday, September 25, 2014

ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች መካከል በተያዘው ዓመት አንዱን በዩኔስኮ ልታስመዘግብ ነው፡፡

    
ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች መካከል በተያዘው ዓመት አንዱን በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባልህ ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት እንደምታስመዘግብ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ። የባለሥልጣኑ የባህላዊ ቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው እንዳስታወቁት አገሪቷ በድርጅቱ በጊዚያዊነት ካስመዘገበቻቸው አራት ቅርሶች መካከል አንዱን በዚህ ዓመት በቋሚነት ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰች ነው። ዩኔስኮ በጊዚያዊነት ከመዘገባቸው መካከል የመልካ ቁንጡሬና የባጭልት የቅሪት አካል አካባቢዎች፣ የጌዲኦ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልከአ ምድር እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻና የድሬ ሼክ ሁሴን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።


ድርጅቱ ከየአገራቱ በየዓመቱ አንዳንድ ቅርሶች እንዲመዘገቡ በሚፈቅደው መሰረት ኢትዮጵያ ከእነዚህ አራት በጊዚያዊነት ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱን በተያዘው ዓመት ታስመዘግባለች ብለዋል። በቅርስነት ይመዘገባሉ ከሚጠበቁት ቅርሶች አንዱ የሆነው በላይኛው የአዋሽ ሸለቆ የሚገኘው የመልካ ቁንጡሬ ከግማኝ ክፍለ ዘመን በላይ የቅሪተ አካል ምርምርና ጥናት የተካሄደበት አካባቢ ነው።


በአካባቢው ከ80 በላይ የቅሪተ አካል ንብርብሮች የተገኙ ሲሆን 30 ያህሉም በቁፋሮ መውጣት የቻሉ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በአካባቢው የሆሞ ኢሬክተስን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ ቁሳቁሶች፣ የሰውና የእንስሳት ቅሪት አካላት በቁፋሮ የተገኙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ከእነዚህ ቅርሶች በተጨማሪ ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ በቅርስነት እንዲሰፈሩ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ደሳለኝ  ለኢዜአ አመልክተዋል። በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ የሚጠበቁት የሐረር ሕዝቦች የአሹራ በዓል አከባበር፣ የሲዳማ የዘመን መለወጫና የጨምበላላ በዓል እንዲሁም የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ይገኙበታል። የቅርሶቹን ምዝገባ አስመልክቶ ድርጅቱ ውሳኔውን በመጪው ኅዳር ወር አጋማሽ ለኢትዮጵያ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።  ባላፈው ዓመትም በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የሚከበረው የመስቀል በዓል በዩኔስኮ በቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment