Tuesday, November 19, 2013

ስቴፈን ዊሊያም ሆውኪንግ

ዊሊያም ሼክስፒር  አይዛክ ኒውተን ቻርለስ ዳርዊን፣ አልበርት አንስታይን፣ እና መሰል ምሁራኖች በእያንዳንዱ የአለም ማህበረሰብ ህይወት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻሉ የእውቀት አበቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምድራችንን ከተሰናበቷት ዘመናትን ቢያስቆጥሩም ለአለም ህዝብ አበርክተው ያልፉት ስራቸው ግን ስማቸውን ለዘላለም እንድናስታውሳቸው ያደርግናል፡፡ 
    ስቴፈን ሆውኪንግ ደግሞ አንስታይን ካለፈ በኋላ የተገኘ ምጡቅ አእምሮ ያለው የአለማችን ቁንጮ ሳይንቲስት እየተባለ ይወደሳል፡፡ .. ጥር 8, 1642 ጋሊሊዮ ጋሊሊ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ታህሳስ ወር 1642 እውቁ የፊዚክስ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተን ተወለደ፡፡ 300 አመታት በኋላ ደግሞ ብሪታኒያው ስቴፈን ሆውኪንግ እውቁ የእንግሊዝ ዩንቨርሰቲ በሚገኝበት ከተማ ኦክስፎርድ .. ጥር 8, 1942 ተወለደ፡፡


 
 ሆውኪንግ እጅግ ምጡቅ አእምሮውን በመጠቀም አብረውት የሚማሩትን ተማሪዎች ከመብለጥም አልፎ የፊዚክስ ትምህርትን ለበርካታ አመታት ላስተማሩ መምህራንም ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ .. 1962 ከኦክስፎርድ ዩንቨርሰቲ የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያ ድግሪውን አገኝቷል፡፡ ከተወሰኑ አመታት በኋላም 1966 ከካምብሪጅ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ድግሪውን ተቀብሏል፡፡
   ስቴፈን ዊሊያም ሆውኪንግ በሲንጉላሪቲ / ነጥብነት/ ቢግ ባንግ / ታላቁ ፍንዳታ/ ብላክ ሆልስ / ፅልመታዊ ጉድጓዶች/ የሆውኪንግ ራዴሽን / ጨረራ/ የሚሉ ንድፈ - ሀሳቦች ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ “A Brief History of Time, The Grand Design” እነዚህን እና ሌሎች መፅሀፍትን አሳትሟል፡፡ በተለይ “A Brief History of Time” የተሰኘ መፅሀፉ በብዙ ሚሊዮን ቅጅዎች የተሸጠ ሲሆን በተለያዩ ቋንቋዎችም ተተርጉሟል፡፡ 1979 በሂሳብ የሉካዥያን ፕሮፌሰርነትን አግኝቷል፡፡ በርካታ ሽልማቶችንም በተለያዩ ጊዜያት ተጎናፅፏል፡፡


  
   የአስትሮ - ፊዚክሱን ሊቅ ገና በወጣትነቱ ያጋጠመው የሞተር ኒውሮን በሽታ ለሞት ባይዳርገውም የእድሜ ልክ አካል ጉዳተኛ እና የተሸከርካሪ ወንበር ቁራኛ አድርጎታል፡፡በሽታው ልዩ ልዩ የነርብ ህዋሳትን የሚያቀጭጭና የሚያዳክም በመሆኑ ሆውኪንግንም መናገር እንዳይችል አድርጎታል፡፡ 

  
  ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና በሰው ሰራሽ ንግግር ማቅረቢያ መሳሪያ /speech generating device / በመጠቀም መግባባት ይችላል፡፡ በጉንጮቹ አካባቢ የተገጠሙት እነዚህ ሴንሰሮች ሀሳቡን በመረዳት ወደ ፅሁፍ እና ድምፅ ይቀይሯቸዋል፡፡
                                          
  እንደዚህ አይነት ተሞክሮዎች መነሳሳትን ይፈጥራሉ እና ለዛሬ ስለ ስቴፈን ሆውኪንግ በጥቂቱ ተጨዋወትን ፡፡ ደግደጉን ተመኘሁላችሁ ሰላም ጤና እና ፍቅር ከእናንተ ይሁን !!!

1 comment: