የሲ/ር አሰለፈች ቀብር ከሃዘን ይልቅ ፍርሃት ነግሶበት አለፈ። እድርተኞች አልመጡም፤ ቤተዘመድ አልሸኛቸውም፤ ከሚወዷቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው ግብዓተ መሬታቸው ሲፈጸም አንድም ሰው ዝር አላለም። ጸሎተ ፍትሐት የሚያደርግ ልዑክ ጠፍቶ መምህረ ንስሃቸውን አንድ ዲያቆን ከርቀት በለሆሳስ ነው ያደረሱት። የሚያጽናና የለም። እዝን ያመጣም አልነበረም። ከሞታቸው በላይ የእናታቸው ቀብር የልጆቻቸውን ልብ ሰብሯል።
የታመመ ጠያቂ፣ የተጣላ አስታራቂ ነበሩ። ለቅሶ ቢሆን ሰርግ ወይዘሮ አሰለፈች ከሌሉ ጨው እንደሌለው ወጥ ነው። በአንዴ ከደጋሹ በላይ አዛዥ ናዛዥ ሆነው ይገኛሉ። በሰፈሩ በቤት ውስጥ ተወልዶ ሲ/ር አሰለፈች እትብቱን ያልቀበሩለት ማግኘት ይከብዳል። ለዚህም ይመስላል የሰፈሩ ጎረምሳ እሳቸውን እንደ እናት ከመቁጠር በላይ በስማቸው ሊምል የሚዳዳው። ታዲያ የእኚህ ደርባባ፣ አመለሸጋ የመንደሩ ሁሉ እናት ቀብር ለምን የአልፎ ሂያጅ ቀብር መሰለ?
ሦስት ልጆቻቸውን ያለአባት አስተምረው ለዩኒቨርሲቲ ያደረሱት በአንድ የመንግስት ሆስፒታል በነርስነት እየሰሩ በሚያገኙት ደሞዝ ነበር።
ሦስት ልጆቻቸውን ያለአባት አስተምረው ለዩኒቨርሲቲ ያደረሱት በአንድ የመንግስት ሆስፒታል በነርስነት እየሰሩ በሚያገኙት ደሞዝ ነበር።
በባልደረቦቻቸው እንደተወደዱ፣ በታካሚዎች እንደተመሰገኑ 20 ዓመታት አገልግለዋል። ታዲያ በአንድ ሰንካላ ቀን በሥራ ላይ እያሉ ሁለት ጸጉረ ልውጥ ሰዎች ከሜትረኗ ጋር አስጠርተዋቸው 'እዚህ ዋርድ ተኝቶ የነበረው ታካሚ 'ፖዘቲቭ' ስለሆነ መመርመር አለብሽ' አሏቸው። ደነገጡ። ምርመራ አድርገው ውጤት እስኪደርስ ለጤና ባለሞያዎች ወደተለየ ቦታ ተወሰዱ። ድፍን ሁለት ቀን ፍርሃት፣ ሃዘን፣ ጭንቀት፣ . . . መጥፎ ስሜቶች ሁሉ በከፍተኛ አቅማቸው በረቱባቸው። እንቅልፍ አይታሰብም፤ የመጀመሪያውን ቀን ስለልጆቻቸው ሲብሰከሰኩ ቁጭ ብለው ለደቂቃ በአይናቸው ሳይዞር ነበር የነጋው። . . . የፈሩቱ አልቀረም ኮሮና እንዳለባቸው ስለታወቀ ወደ ህክምና ማእከል ተወሰዱ። ካለባቸው የአስም ሕመም ጋር ተዳብሎ በሽታው ስለጸናባቸው ወደ ጽኑ ሕክምና ክፍል በገቡ በ3ተኛው ቀን የልጆቻቸውን ወግ ማእረግ ሳያዩ እንዲሁ እንደተንከራተቱ አረፉ።
የሲ/ር አሰለፈች ታሪክ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብን? ሃዘን፣ ፍርሃት፣ ድንጋጤ፣ መሸበር፣ ጭንቀት . . .?
ስሜቶቹስ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው? የምናውቃቸው እናት፣ ጎረቤት፣ ባልደረባ ወይስ ማንን አስታወሱን? ከእነዛ ሁሉ ቁጥሮች በተለየ እንድንጠነቀቅ፣ ወላጆቻችንን እንድናስብ፣ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አነሳሱን?
እያንዳንዱ ብዙኃን መገናኛ ቢያንስ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች (ማንነታቸው ሳይገለጽና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ) ታሪክ በመተረክ ሕዝቡ ነፍስና ስጋ መንፈስም ያላቸው ወገኖቹ ምን እየደረሰባቸው እንዳለ እንዲገነዘብ ማድረግ ይቻላል። እንዲያ ሲሆን ሰዎች ራሳቸውን በሞቱት ወገኖች ጫማ እንዲያስቀምጡ ያስችላቸዋል። ይህ መንገድ ሊፈጥር የሚችለውን የፍርሃት መጠን እያዩ ሚዛኑን መጠበቅ ይቻላል።
ተፃፈ… በዶ/ር እንግዳ ግርማ
(የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር)
No comments:
Post a Comment