በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ 63 ተከሳሾች ክስ፣ በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ በመደረጉ ከእስር ተፈቱ፡፡ተከሳሾቹ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረገው ተፈጽሟል በተባለው የወንጀል ድርጊት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ክሱ እንዲቋረጥ ከተደረገላቸው መካከል ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለው የተከሰሱ ግለሰቦች፣ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ነገር ግን የአመራርነት ሚና ያልነበራቸው ግለሰቦች ክሳቸው መቋረጡና እንዲፈቱ መወሰኑን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
ከኤምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር መሥራች የነበሩት፣ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋም ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የሚታወቁት የዓለም ገነት ቆርቆሮ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም፣ ሪቬራ ሆቴልን ለሜቴክ ከመሸጣቸው ጋር በተያያዘ የተከሰሱበት ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡
ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ተከሳሾች መካከል የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደም ይገኙበታል፡፡ኮሎኔሉ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል በመከላከያነት ከቆጠሯቸው መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ብዛት ምክንያት ሳይቀርቡ በመቅረታቸው የክስ መዝገባቸው በተደጋጋሚ ሲቀጠር የነበረ ቢሆንም፣ አሁነ መንግሥት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ክሳቸው ተቋርጦ ሊፈቱ ችለዋል፡፡
በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በጅግጅጋና ሌሎች የክልሉ ከተሞች በተፈጸመ ዘርን መሠረት ያደረገ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠልና ንብረት ዘረፋ ጋር በተያያዘ በቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) የክስ መዝገብ የተካተቱት የክልሉ ሕፃናትና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ራህማ መሐመድ፣ እንዲሁም ወ/ሮ ዘምዘም ሐሰንና የሌሎች ክስ ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል፡፡
ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሽን (ሜቴክ) ተከሳሾችም፣ ኮሎኔል ዙፋን በርሄ፣ ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔና ሌሎችም ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ከደቡብ ክልልም ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የኤጄቶ አባላት የነበሩት አቶ አማኑኤል በላይነህ፣ ተሰማ ኤልያስ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ አቶ አዲሱ ቀሚሶና ሌሎችም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎችም በአጠቃላይ 63 ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡
የክስ ማቋረጥ ሒደቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመሩት የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃላፊዎች በተገኙበት፣ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሉባቸውን ውስንነቶች መናገራቸውን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ ገልጸዋል፡፡ ወንጀል በብዙ መንገድ ሊፈጸም እንደሚችል ጠቁመው፣ የመጀመርያው የመንግሥት አካል የተጣለበትን ኃላፊነት አለመወጣት መሆኑን አክለዋል፡፡
ሌላው ደግሞ ወንጀል ፈጻሚ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ተጠያቂ እንደሚሆን ጠቁመው፣ ሕግ የማስከበር ሥራ መጀመርያ መፈጸም ያለበት በመንግሥት መሆኑ በተደረገ ውይይት መተማመን ላይ በመደረሱ፣ ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ፣ ዕቅድ በማውጣት መሥራት መጀመሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እነ ማን ወንጀል እንደሠሩ፣ እነ ማን እንደተያዙና እነ ማን እንዳልተያዙ፣ ላለመያዛቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግምገማ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ክልል ተወያይቶና በተለይም ወንጀል ሠርተው ስላልተያዙ ተጠርጣሪዎች ላለመያዛቸው መንስዔ የሆነው ማን እንደሆነ ማለትም የፖለቲካ አመራሩ፣ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይስ ሌላ የሚለውን እየመረመሩ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በተቀመጠው አቅጣጫም መሠረት ዕርምጃ ለመውሰድ መርሐ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሥራውን መሥራት ያልቻለ አመራር ያልቻበት ምክንያት ተገምግሞ አሳማኝ ካልሆነ በራሱ ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድበትም ጠቁመዋል፡፡
ክስ ማቋረጥ ማለት ግን የመጨረሻ ውሳኔ አለመሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ክስ የተቋረጠላቸው ተከሳሾ ተመልሰው ወደ ለመዱት ድርጊት የሚገቡ ከሆነ ግን ዓቃቤ ሕግ ያቋረጠውን ክስ ማንቀሳቀስ የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተከሳሾች አንዳንዶች የጤንነት ችግር ያለባቸው፣ ከሕፃናት ጋር ታስረው የሚገኙ፣ የወንጀል ተሳትፏቸው አነስ ያሉ ተከሳሾች መሆናቸውንም አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሳቸዉ እንድቋረጥ የተደረጉ ግለሰቦች ስም ዝርዝር
ReplyDeleteየካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም
1. ሌ/ኮ/ ቢኒያም ተወልደ
2. ሌ/ኮ/ል ሰላይ ይሁን
3. ሌ/ኮ/ል ጸጋዬ አንሙት
4. ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ
5. ኮ/ል ግርማ ማንዘርጊያ
6. ኮ/ል ዙፋን በርሄ
7. ኮ/ል አሰመረት ኪዳኔ
8. ሻ/ል ይኩኖአምላክ ተሰፋዬ
9. አቶ አለም ፍጹም
10. አቶ ሰለሞን አብርሃ
11. አቶ ሰመረ ኃይለ
12. አቶ ክፍላይ ንጉሴ
13. ሌ/ኮ/ል መንግስቱ ከበደ
14. ሌ/ኮ/ል እሥራኤል አሰፋው
15. ሌ/ኮ/ል ከተማ ከበደ
16. ሌ/ኮ/ል ለተብርሃን ደሞዝ
17. አቶ ኡስማን ከበደ
18. ሌ/ኮ/ል ዋቅቶላ አዲሱ
19. ሌ/ኮ/ል ታቦር ኢዶሳ
20. ሻ/ል ዩሐንስ ትኬሳ
21. ወ/ሮ ወላንሳ ገ/ኢየሱስ
22. ሻ/ቃ ረመዳን ለጋስ
23. አቶ ሙሉጌታ ሰይድ
24. አቶ ዋሴዕ ሳድቅ
25. አቶ ሲሳይ ደበሌ
26. አቶ አክሊሉ ግርማይ
27. ወ/ሮ ራህማ መሀመድ
28. ወ/ሮ ዘምዘም ሀሰን
29. ኮ/ር ፋሩቅ በድሪ
30. አቶ አሳጥረው ከበደ
31. አቶ ሲሳይ አልታሰብ
32. አቶ አበበ ፋንታ
33. አቶ አሰቻለዉ ወርቁ
34. አቶ ተሾመ መለሰ
35. አቶ አለምነህ ሙሉ
36. አቶ ከድር ሰይድ
37. አቶ አዲስ አማረ
38. አቶ አማረ ብሌ
39. አቶ ክርስቲያን ታደለ
40. አቶ በለጠ ካሳ
41. አቶ ሚፍታህ ሸምሱ
42. ዶ/ር ማቴ ማንገሻ
43. አቶ ታሪኩ ለማ
44. አቶ ጌታሁን ዳጉይ
45. አቶ በላይ በልጉዳ
46. ሪ/ፓ/ር አመሉ ጣሚሶ
47. አቶ ተፈራ ቄንፈቶ
48. ረዳት ፕሮፈሰር ተሰማ ኤልያስ
49. አቶ አማኑኤል በላይነህ
50. አቶ አዲሱ ቃሚሶ
51. ሱ/ኢ/ አሰገል ወ/ጊዩርጊስ
52. ሱ/ኢ/ አሰፋ ኪዳኔ
53. ሱ/ኢ/ ገ/እግዚአብኤር ገ/ሃዋርያት
54. አቶ ግርማ አቡ
55. አቶ አብዱልሙኒየር አብዱልጀሊስ
56. አቶ ቶፊቅ አብዱልቃድር
57. አቶ ከማል መሃመድ
58. ኮ/ር ኡስማን አህመድ
59. ኮ/ር ኤዶሳ ጎሽ
60. አቶ ባበከር ከሊፋ
61. ዋ/ሳ/ እቴነሽ አርፋይኔ
62. አቶ ኤርሚያስ አመልጋ
63. አቶ ሙሉጌታ ሰይድ