Thursday, October 16, 2014

የፖስታ አገልግሎት አጀማመር በኢትዮጵያ



    በአገራችን የፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ1886 ዓ.ም በአዋጅ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ በዚሁ ዓመተ ምህረት በነሀሴ ወር የመጀመሪያዎቹ ቴምብሮች በፈረንሳይ አገር ታትመው ሐረር ከተማ ደረሱ፡፡ የታተሙት ቴምብሮች ብዛት ሰባት ዓይነት ሲሆን ዋጋቸውም ሩብ፣ ግማሽ፣ አንድ፣ ሁለት፣ አራት፣ ስምንት እና አስራ ስድስት ግርሽ ነበር፡፡ 

  ከነዚህ መካካል የመጀመሪያዎቹ አራቱ ዳግማዊ ምኒሊክ የዙፋን ልብሳቸውን እንደተጎናፀፉ የሚያሳዩ ሲሆን የቀሩት ሶስቱ ደግሞ የይሁዳ አንበሳን ምስል የያዙ ነበሩ፡፡የኢትዮጵያ ፖስታ ቴምብሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሽያጭ ላይ የዋሉት በጥር ወር 1887ዓ.ም በእንጦጦ ፣ በሐረር እና በድሬድዋ ከተሞች መሸጥ ጀመሩ፡፡

 ከአንድ አመት በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ቴምብሮች በፓሪስ ከተማ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የቴምብር ኤግዚቢሽን እንዲታዩ ተደርጎ በተመልካች ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ወቅትም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ቴምብሮች እንደተሸጡ ይነገራል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የመታሰቢያ ቴምብሮች በእውቁ ፈረንሳዊ ሰዓሊ ሙሴ የጂን ሙስ የተሳሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎት ከ1899 - 1945 ዓ.ም ድረስ በፖስታ ቴሌፎንና ቴሌግራፍ/ፓቴቴ/ ስር ቆይቶ ቀስ በቀስ እራሱን እያስተዳደረ በ1958ዓ.ም እንደገና በአዋጅ ተቋቋመ ፡፡

  በ1901ዓ.ም (አንዳንድ መረጃዎች በ1900ዓ.ም ይላሉ) ኢትዮጵያ የአለም የፖስታ ህብረት አባል ለመሆን በመቻሏ የኢትዮጵያ ፖስታ ቴምብሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱን ወሰን አልፈው በመላው አለም በሚገኙ አባል ሀገራት መሰራጨት ጀመሩ፡፡ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ የመጀመሪያዎቹ መደበኛ ቴምብሮች እንደገና ልዩ ምልክት እየታተመባቸው በመታሰቢያነት ወጡ፡፡ ስለሆነም እነዚህ ቴምብሮች በአገራችን የመጀመሪያዎቹ የመታሰቢያ ቴምበሮች ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡

   በ1902 ዓ.ም ለአገር ውስጥ እና ለውጪ አገር አገልግሎት የሚውሉ ሰባት ዓይነት አዲስ መደበኛ ቴምብሮች ታተሙ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ የመንግስትን አርማ የሚሳዩ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ያገር ባህል ልብሳቸውን ለብሰው በቀኝ እጃቸው በትረ -መንግስት እንደያዙ ሲያሳዩ፤ በቀሩት ሁለቱ ላይ ዳግማዊ ምኒሊክ ልብሰ መንግሰታቸውን ተጎናፅፈው እና ዘውድ ጭነው ይታያሉ፡፡

    ቀጥሎም በ1911ዓ.ም ለሶስተኛ ጊዜ በመደበኛነት የሚያገለግሉ 15 ዓይነት ቴምብሮች ታትመው ገበያ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም ቴምብሮች ቀደም ሲል ከተዘጋጁት ለየት ያሉ ነበሩ፡፡ የቴምብሮቹ ስዕል ጉማሬ፣ ጎሽ፣ አነር፣ ቀጭኔ፣ ዝሆን፣ አንበሳ እና ሰጎን ይታዩባቸው ነበር፡፡ ስዕሎቹም የመጀመሪያዎቹ የአገር ውስጥ ሰዓሊያን የስዕል ስራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ አገሪቱን እስከወረረበት ጊዜ ድረስ የጠቅላይ ፖስታ ቤት የተከፈተበትን፣ የመጀመሪያው አውሮፕላን አዲስ አበባ ያረፈበትንና የቀይ መስቀል አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ የመታሰቢያ ቴምብሮች ታትመዋል፡፡


   በግንቦት ወር 1927ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባ ገብቶ ወረራውን በመቀጠሉ ቀደም ሲል የታተሙት ቴምብሮች በብዛት ከመቃጠላቸውና ከመዘረፋቸውም በላይ እስከ 1933ዓ.ም የታተሙ አዳዲስ ቴምብሮች አልነበሩም፡፡ ጣሊያን ድል ተደርጎ ወደ አገሩ ሲመለስ በዚሁ ዓመት በመጋቢት ወር ሶስት ዓይነት መደበኛ ቴምብሮች ታትመው ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡
   

   
   በአጠቃላይ በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ አልፎ ቴምብር ማሳተም የተቋረጠባቸው ጥቂት ጊዜያቶች ቢኖሩም ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት የአገሪቱን ባህል፣ ምጣኔ ሀብት፣ ፖለቲካ፣ ቅርሳ ቅርሶች፣ አዕዋፍ፣ እፀዋት እና እንሰሳት እንዲሁም በአገር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፉ እና ታሪክ ያወቃቸው ታላላቅ ሰዎችና ቦታዎችን ወ.ዘ.ተ የሚያወሱ ቴምብሮች ታትመው በአገር ውስጥም ሆን በውጪ አገር ተሸጠዋል፡፡ ለወደፊቱም እነዚህን በመሳሰሉና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መደበኛ እና የመታሰቢያ ቴምብሮች እየታተሙ አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment