Tuesday, September 30, 2014

ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ 95 ሚሊዮን ብር ያጭበረበረው ግለሰብ ተያዘ


  ከሰባት ዓመት በፊት ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ አጭበርብሮ የተሰወረውን ግለሰብ መያዙን የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ግብረሀይል አስታወቀ፡፡ከብሔራዊ ባንክ በሀሰተኛ ወርቅ ማጭበርበር ወንጀል ተከሶ የቅጣት ፍርድ የተበየነበት አቶ አስማረ አያሌው ደስታ ከተባበሩት የአረብ ኢምሬትስ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱን ግብረ ኃይሉ አረጋግጧል፡፡ በመስከረም19/2007 ለኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ግለሰብም ከዚህ በፊት እሱ በሌለበት የ25 ዓመት ፅኑ እስራትና የ180 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበት ነበር፡፡
  ተከሳሹ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሀሰተኛ የወርቅ ጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሀሰተኛ የላኪና አስመጪ የንግድ ፍቃድ ካዘጋጀ በኃላ ከባንኩ 95 ሚሊዮን 553 ሺህ 413 ብር ከ89 ሳንቲም አጭበርብሯል፡፡    
   በዚህም ግለሰቡ ከታህሳስ 1998 እስከ መጋቢት 1999 ባሉት ጊዜያት በውስጣቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረታ የያዙ 29 የታሸጉ ሳጥኖች ለብሔራዊ ባንኩ ሰጥቷል፡፡ ግለሰቡ ድርጊቱን መፈፀሙን ሲነቃበትም በኬንያ በኩል ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመሄድ ከተደበቀ በኃላ ፣በቁጥጥር ስር ውሎ በብሔራዊ ኢንተርፖል አማካኝነት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ወንጀለኛውን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
  አቶ አስማረ ከፍተኛ የሆነ የህዝብና የሀገር ሀብት በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ በጥብቅ ለ7 ዓመታት ሲፈለግ እንደነበርም ግብረ ሀይሉ ገልጿል፡፡ በማንኛውም መልኩ በሀገሪቱ ደህንነትና ጥቅም ላይ ጉዳት በመፈፀም ለማምለጥና ለመሰወር ጥረት የሚያደርጉ መሰል ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረባቸው እንደማይቀር አስታውቋል፡፡ የኢፌዲሪ መንግስት ለተባበሩት የአረብ ኢምሬት መንግስትና ህዝብ ላደረጉላት ትብብርና ድጋፍ ምስጋና አስተላልፎል ብሏል ግብረ ሀይሉ፡፡
                                         ምንጭ ፡- ኢ.ብ.ኮ/EBC/

Thursday, September 25, 2014

ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች መካከል በተያዘው ዓመት አንዱን በዩኔስኮ ልታስመዘግብ ነው፡፡

    
ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች መካከል በተያዘው ዓመት አንዱን በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባልህ ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት እንደምታስመዘግብ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ። የባለሥልጣኑ የባህላዊ ቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው እንዳስታወቁት አገሪቷ በድርጅቱ በጊዚያዊነት ካስመዘገበቻቸው አራት ቅርሶች መካከል አንዱን በዚህ ዓመት በቋሚነት ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰች ነው። ዩኔስኮ በጊዚያዊነት ከመዘገባቸው መካከል የመልካ ቁንጡሬና የባጭልት የቅሪት አካል አካባቢዎች፣ የጌዲኦ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልከአ ምድር እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻና የድሬ ሼክ ሁሴን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።


ድርጅቱ ከየአገራቱ በየዓመቱ አንዳንድ ቅርሶች እንዲመዘገቡ በሚፈቅደው መሰረት ኢትዮጵያ ከእነዚህ አራት በጊዚያዊነት ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱን በተያዘው ዓመት ታስመዘግባለች ብለዋል። በቅርስነት ይመዘገባሉ ከሚጠበቁት ቅርሶች አንዱ የሆነው በላይኛው የአዋሽ ሸለቆ የሚገኘው የመልካ ቁንጡሬ ከግማኝ ክፍለ ዘመን በላይ የቅሪተ አካል ምርምርና ጥናት የተካሄደበት አካባቢ ነው።


በአካባቢው ከ80 በላይ የቅሪተ አካል ንብርብሮች የተገኙ ሲሆን 30 ያህሉም በቁፋሮ መውጣት የቻሉ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በአካባቢው የሆሞ ኢሬክተስን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ ቁሳቁሶች፣ የሰውና የእንስሳት ቅሪት አካላት በቁፋሮ የተገኙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ከእነዚህ ቅርሶች በተጨማሪ ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ በቅርስነት እንዲሰፈሩ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ደሳለኝ  ለኢዜአ አመልክተዋል። በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ የሚጠበቁት የሐረር ሕዝቦች የአሹራ በዓል አከባበር፣ የሲዳማ የዘመን መለወጫና የጨምበላላ በዓል እንዲሁም የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ይገኙበታል። የቅርሶቹን ምዝገባ አስመልክቶ ድርጅቱ ውሳኔውን በመጪው ኅዳር ወር አጋማሽ ለኢትዮጵያ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።  ባላፈው ዓመትም በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የሚከበረው የመስቀል በዓል በዩኔስኮ በቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ 95 ባህርተኞችን አስመረቀ

 የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመካኒካል እና ኤሌክትሪክ ኢንጅነሪግ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በባሕር ምህንድስና አሰልጥኖ አስመርቋል።
  የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ጆርዳን በክር በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተመራቂዎች ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ የመርከብ ምህንድስና ንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠናዎችን ለስድስት ወራት ተከታትለዋል። የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ በዚህ ዙር 50 የኤሌክትሪካል መሀንድሶችንና 45 መካኒካል መሀንድሶችን በድምሩ 95 ባህርተኞችን ነው ያስመረቀው። ተመራቂዎችም ለበርካታ አመታት በዘርፉ ላይ የካበተ ልምድ ባላቸው መምህራን የወሰዱት እውቀት በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ብዙ ግብራም ዘርፉ የስራ እድል ከመፍጠሩም ባለፈ ለሃገሪቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ አስገኝቷል። ተቋሙ አሁን ያስመረቃቸው ባህርተኞች በመካኒካል ምህንድስና ለ8ኛ ጊዜ፣ እንዲሁም በኤሌክትሪካል ምህንድስና ዘርፍ ደግሞ ለ3ተኛ ጊዜ ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ እስከአሁን ድረስ ከ8 መቶ በላይ የባሕር ምህንድስና እጩ መኮንንኖችን አሰልጥኖ አስመርቋል።
                                                                     
                                                                            ምንጭ ፡- ...

የዓለም አቀፉ አማራጭ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ - ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር

  
   / ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2002 ዓመት - ዓለም አቀፉን አማራጭ የኖቤል ሽልማት (Alternative Nobel Prize) በስቶኮሆልም ስዊዲን ተሸልመዋል፡፡
  
  / ተወልደብርሃን በፈረንጆቹ 2006 ዓመትም የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሸልመውን የምድራችን ጀግና - Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ይህን ሽልማት ያገኙት ሰባት ብቻ ናቸው፡፡ የዚህ ሽልማት ተቋዳሽ ከሆኑት መካከል የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ሚኻኤል ጎርቫቾቭ አንዱ ነበሩ፡፡
 
  / ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሄር የታዋቂው ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ታናሽ ወንድም ናቸው፡፡ አፍሪካውያን / ተወልደብርሃንን - የአፍሪካ ድምጽ - The Voice of Africa እያሉ ይጠራቸዋል ያንቆለጳጵሳቸዋል፡፡


Tuesday, September 23, 2014

አንጋፋው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ፡፡

 
   በ68 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ በዛሬው ዕለት መስከረም 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቤተሰቦች፣ የጥበብ ወዳጆች፣ አድናቂዎቹ በተገኙበት የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
  በ1939 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደው አርቲስት ኃይማኖት ዓለሙ ዘመናዊ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት አጠናቆ የከፍተኛ ትምህርቱን በአሜሪካ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪውን በመከታተል በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቋል። ሁለተኛ ዲግሪውንም በክብር እዚያው ይዟል። በጎርጎሮሳውያኑ 1988 በተካሄደ የሼክስፒር ድርሰቶች አተዋወን ላይ በመወዳደር “የኢራ አልድሪጅ” ሽልማትን አግኝቷል። በ1989 በሎስ አንጀለስ የአል ካሚኖ ዩኒቨርሲቲ የፋኩልቲ አባል በመሆን የሼክስፒርን ተውኔቶች አስተምሯል፣ አዘጋጅቷልም።
   በሀገር ወስጥ ደግሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን /በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን/ “ፊት ለፊት” የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን ሲያልግል በውጭ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች አገልግሏል። የ3 ልጆች አባት የነበረው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ፣ ባደረበት ሕመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ68 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር፡፡
                                          ምንጭ ፡- ኢብኮ/EBC/

Monday, September 22, 2014

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 20 ቦይንግ 737 ሞዴል አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው፡፡


   አየር መንገዱ ከ40 ቢሊዮን ብር በላ በሆነ ወጪ ግዢውን ለመፈፀም ከአምራቹ ቦይንግ ኩባንያ ጋር ተስማምቷል ተብሏል፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የአውሮፕላኖቹ ግዢ እ.ኤ.አ 2025 መጨረሻ 18 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት ለማጓጓዝ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል፡፡አየር መንገዱ የቦይንግ ምርት የሆነውን 737 ሞዴል በአንድ ጊዜ በብዛት ለመግዛት ሲያዝ የመጀመሪያ ያደርገዋል ሲል ብሎምበርግ ዘግቧል፡፡

ፈንድሻ እና ድፎ ዳቦ - በመምህር ቃለአብ ካሳዬ


  ፈንዲሻ እና ድፎ ዳቦ በዓመት በዓል የእራት እና የቡና ዝግጅት ላይ በአንድ ላይ ቀርበው ተገናኙና እንዲህ ተጨዋወቱ፡፡ ሰዎቹ ደመራን ለማብራት አንድ አንድ እየለኮሱ ከቤት ወደ ግቢ ሲወጡ ጠብቆ ድፎ ዳቦ እንዲህ አለ፡- “አንቺ ፈንዲሻ! አቤት እንዴት ፍካት ያምርብሻል? በዚህ ላይ በስኳር ጣፍጠሽ! እታለሜ አንቺስ እድለኛ ነሽ”፡፡ ፈንዲሻም መለሰች “አይ ድፎ የእኔ ፍካት ያለ እሳት አይወጣም፡፡ ያለ እሳት እኔ ጥሬ ነኝ! በእሳት ስመታ ቢያቃትለኝም ደስ ይለኛል፤እፈካበታለሁ! ለነገሩ ሰዎች ነቅተውብኛል! “ማሽላ እያረረ ይፈካል/ይስቃል/” ይሉኝ የለ? ፅጌረዳ ትፈነዳለች፣ ትፈካለች፤ እኔም እፈነዳለሁ፣ እፈካለሁ፤ ፅጌረዳ በፀሀይ፣ በአየር፣ በውሀ ትፈነዳለች፣ ትፈካለች፡፡ እኔ ደግሞ በእሳት! አይገርምህም ድፎ? ለነገሩ ፈክቼ በክብር ለሰዎች ስዞር ደስ ይለኛል፡፡  

  እኔ የምለው ድፎ፡- እነዚህ ሰዎች ግን አይማሩብኝም! ሰው ሁሉ በእሳት /በመከራ/ የቀመማል ተብሎ ተፅፏል እያሉ ሲያወሩ ሰምቻለሁ፤ ነገር ግን በመከራ ሲጎሳቆሉ እንጂ ሲፈኩ፣ ሲቀምሙ እነጂ ሲቀመሙ እምብዛም አላይም፡፡ ከእኔ ከማሽላዋ በታች ይኖራሉ! እኛ በድስት ውስጥ በእሳት ስንፈካ ከመካከላችን እሳቱ የበዛበት ተፈናጥሮ ይወጣና ወደ ውጪ ይወድቃል፤ ያ አባላችን ታዲያ በክብር ከእኛ ጋር ለቡና ቁርስ አይቀርብም፡፡ ወይ ይረገጣል፣ ወይ ይጠረጋል፣ ወይ የአቧራ ጌጥ ይሆናል፣ ወይ ዶሮ ይለቅመዋል፡፡ ሆ ሆይ! ዝም ብሎ በእሳት መፍካት ነው፡፡

  ደግሞም እንደተናገርከው ስንታገስ ስኳር ይጨምሩልናል፡፡ ከዚያ በሰው ጥርስ ተነክሰን፣ በሰው አፍ ውስጥ ሞተን በሰው ሆድ ውስጥ እንቀበራለን! ከሞቱስ አይቀር እንደኛ ፈክቶ፣ እንደኛ ጣፍጦ መሞት ነው፡፡ ፍፃሜዬን ያሳምርልኝ ይላሉ የእኛን መጨረሻ ያዩ! አይ ሰው! ግና ከእኛ አይማርም! ያፈካል እንጂ አይፈካብንም፣ ያጣፍጠናል እንጂ አይጣፍጥብንም፡፡ እኛ ምን ገዶን! ከኛ አይጉደል አለች ፈንድሻ በመቅረቢዋ/እርቦ/ እንደተከመረች በረጅሙ ተንፍሳ!

   እኔ የምለው ግን ድፎ፣ ምነው ገላህ ከላይ መሀሉ ላይ ጠቆረ? ድፎም መለሰ እረ ተይኝ እቴ! “ያልተገላበጠ ያራል” ይሉ ነበር ለተረቱ፣ ነገር ግን ሳያገላብጡ አሳረሩኝ፡፡ እኔ እጅ እግር የለኝ፣ በምን ጎኔ ልገላበጠው ብለሽነው! ይኸው ውስጤ እሳት በዝቶ ገላዬ ሳይቀር አረረልሽ!፡፡ ፈንድሻም መለሰች “ምነው በውሀ ቢደፉህ፣ ነጭ ህብስት ሆነህ አቤት ስታምር!” ተይኝ እባክሽ የእኔ ሞገስ በኮባ ተሸፍኜ በእሳት ስገረፍ ነው፡፡ ደስ ይለኛል፣ አበሻነት ይሰማኛል! እሳቱ ሲበዛ ግን አርራለሁ፣ እጠቁራሉ፡፡ እሳቱን በልክ ሲያደርጉልኝ እና ሲያገላብጡ ነው መልካም፡፡


  አይ ፈንድሻ ካንቺ ብቻ መሰለሽ? ሰዎቹ ከእኔም አይማሩም፡፡ ከልክ በላይ እሳት ይጎርሳሉ፡፡ ከልክ በላይ ፖለቲካ፣ ከልክ በላይ አክራሪነት፣ ከልክ በላይ ምኞት፣ ከልክ በላይ ኑሮ፣….. ከውስጥ ጨጓራቸውን ተልጦ ከውጪ ፊታቸው በማዲያት ጠቆረ፡፡ እነሱ አረረ ብለው እኔን በቢላዋ ይፈቀፍቃሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ አረርን ብለው በእንባ ይንፈቀፈቃሉ፤ አይ የሰው ልጆች፣ እሳቱን በልክ ማድረግ እንዲህ ያቅታቸዋል!!

   አንዳንዴ የተበላሸ ስንዴ /በቆልት/፣ የቆየ እርሾ እየቀየጡብኝ ስሜን ያጠፋሉ፣ ቦካ ይሉኛል፡፡ ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ፣ የደፋውን እንደሚቆርስ ማን ባስታወሰልኝ! ደግሞም የሰውን ልጅ ስም በማጥፋት ማን ያህለዋል? ወንድሜን ጤፍንም ህዝቡን እንዲህ ቀጥ አድርጎ ይዞ ስሙን አጥፍተውት የለ? ሰውን ለሚንቅ ሰው መጠሪያ አደረጉት “ሰው ጤፉ” እያሉ፡፡ ጨውና በርበሬም ተስማምተው እንዳልጣፈጡ እነሱን ለማጋጨት “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” ይላሉ፡፡ አይ የሰው ልጆች! 

  ታሪካችንን አጎደፉት፣ ስማችንን አጠፉት እኮ አለ ድፎ ዳቦ! ፈንዲሻም መለሰች ቃሪያስ መች ተረፈች? “አድሮ ቃሪያ” እየተባለች የሰነፍ ታፔላ ሆናለች፡፡ የወንድም የእህቶቻችን የአተር፣ የዳጉሳ፣ የቦለቄ፣ የሽንብራ፣ የሱፍ፣ የጥቁር አዝሙድ…… ስም በየዘመናቱ ጠፍቷል፡፡ ስለዚህ ዛሬ እኛ በኩኪስ፣ በፈረንጅ ጎመን፣ በፓስታ፣ በመኮረኒ፣ በፒዛ፣ በላዛኛ እና በወዘተርፈ ተተክተናል፡፡

 
   
ድሮ በየቤቱ እንዳልነገስን ዛሬ እንደበሽተኛ ተገልለን በባህል ምግብ ቤቶች እና አዳራሾች ብቻ እየተሰየምን ነው፡፡ ይህ ህዝብ አበሻ ነኝ ብሎ ይኮራል እንጂ ራሱን ለፈረንጅ አልሸጠምን? በእኔ ላይ እንኳን ፍሩኖ መጥታለች! ፈንድሻም መለሰች አይ ድፎዬ ይህንንም ባልጣልሽ፣ ያንንም ባላነሳሽ ሲባል አልሰማህም? እኛ ባልተረሳን የውጪውንም ባልተዉት ባልከፋ ነበር፡፡


  
  ፀሀፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል እንጂ ኢትዮጵያ እሱ ውስጥ አትኖርም ብሎ የፃፈውን ሳስታውስ ያለ እሳትም በእሳትም ፍክፍክ ብዬ እስቃለሁ፡፡ አይ ጉድ…… ብሎ ወሬውን ሊቀጥል ሲል ፈንድሻ በል በል! ደመራቸውን ደምረው እየገቡልህ ነው፣ ዝምበል ድፎ!!! አሁን እኛ ልንጠቅማቸው፣ እነርሱ ላይጠቀሙ፤ ልናስተምር፣ ላማሩ ደረሱ፡፡ በልጆቻችን ካልተገናኘን በቀር እኔና አንተ እዚሁ እንሰነባበት፡፡ ደህና ሙት ድፎ! አሜን ደህና ሙቺ ፈንድሻ፡፡ የሰው ልጅ መማር ቢፈልግ በአንድም በሌላም ይማር ነበር፡፡ ግና ግናማ………..!!!

Sunday, September 21, 2014

ጥቂት ስለ “ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ /አቢሲኒያ ባንክ/ ”

  
  ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ የተቋቋመው በ1897ዓ.ም ሲሆን “ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ” ይባል ነበር፡፡ ባንኩንም በበላይነት ይቆጣጠርና ይመራው የነበረው በወቅቱ የእንግሊዛውያን ንብረት የነበረው የግብፅ ብሄራዊ ባንክ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ የራስ መኮንን ይዞታ በነበረው የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ /6ኪሎ ካምፓስ/ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ባንኩም በወቅቱ ከነበሩት የሳር ክዳን ቤቶች ውስጥ በአንዱ ተቋቋመ፡፡


  በእንግሊዞች የበላይ ገዥነትና ንብረትነት የተቋቋመው ይህ ባንክ እስከ 1923ዓ.ም ድረስ በዚሁ ስም አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ሚያዚያ 23 ቀን 1924ዓ.ም አፄ ኃይለስላሴ ባንኩን ከእንግሊዝ ማህበር ላይ በስምምነት ገዝተው፣ ይህንንም በህግ አሳወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ ተብሎ እንዲሰየም አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ባንኩ በአፍሪካውያን ንብረትነት በአፍሪካ ውስጥ የተመሰረተ የመጀመሪያው ባንክ (African Indigenous Bank) ለመሆን በቅቷል፡፡ በታህሳስ ወር 1956ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ በሚል መጠሪያ ይታወቅ የነበረው ይህ ባንክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመባል ለሁለት ተከፈለ፡፡

  አሁን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ባንክ የተቋቋመው ግንቦት 23ቀን 1901ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ባንክ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የስያሜ ለውጦች አድርጓል፡፡ እነሱም፡-
         ከ1901 – 1928ዓ.ም የእርሻ እና የንግድ ማስፋፊያ የኢትዮጵያ ማህበር
         ከ1937 – 1942ዓ.ም የኢትዮጵያ የእርሻ ባንክ
         ከ1942 – 1943ዓ.ም የኢትዮጵያ የእርሻ እና ንግድ ባንክ
         ከ1943 – 1962ዓ.ም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ
         ከ1962 – 1971ዓ.ም የእርሻ እና ኢንዱስትሪ ልማት ባንክ አክሲዮን ማህበር
         ከ1971 – 1987ዓ.ም የእርሻ እና ኢንዱስትሪ ልማት ባንክ
         ከ1987ዓ.ም ወዲህ የኢትጵያ ልማት ባንክ በመባል ይታወቃል፡፡
                                                        
                                              ምንጭ ፡- ህብር ኢትጵያ

Friday, September 19, 2014

ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ከዚህ አለም በሞት ተለየ::


   ተዋናይ፣የፊልም ዳይሬክተር፣መምህር፣ የዳንስ ጥበብ ባለሙያ ፣የማስታወቂያ ባለሙያና አማካሪ ነበር ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ፡፡ በተለያዩ የመድረክ ስራዎች በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ሀገር መድረኮች ላይ በብቃት በመጫወት ይታወቃል፡፡ በተለይም በተማሪነት ዘመኑ የዊሊያም ሼክስፒርን ስራዎች ይጫወት ነበር፡፡

   
  የቴአትር ስራዎችን ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው በብቃት መጫወት የጀመረው፤ ከአማርኛ ተውኔቶች በተጨማሪም በወቅቱ በእንግሊዘኛ በሚዘጋጁ የተውኔት ስራዎች ውስጥም በብቃት ተውኗል፡፡ በአሜሪካ እና በተለያዩ ሀገራትም በትወና ችሎታው የተለያዩ ልማቶችን አግኝቷል፡፡

   በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ እጅግ በርካታ ቴአትሮችን ሠርቷል ከእነዚህም መካከልምጴጥሮስ ያቺን ሰዓትኦቴሎእናት አለም ጠኑእናቴዎድሮስይጠቀሳሉ። የሲሳይ ንጉሱን ልቦለድ /ግርዶሽ/ ወደ ፊልም በመቀየር አዘጋጅቷል፤ ተውኗል፡፡ የሸክስፒርን ስራዎች በተለይም በጫንያለው ወልደጊዮርጊስና ቴዎድሮስ ተሰማ የተተረጎመውን ተጫወቷል፡፡ 

   በፀጋዬ ገብረ መድህን ስራዎች በዘመኑ እጅግ ድንቅ ብቃት ያሳየባቸውንየእናት ዓለም ጠኑእናሀሁ በስድስት ወርቴአትሮች ላይ የተለያዩ ገፀባህሪያትን ወክሎ በብሔራዊ ቴአትር ተውኗል፡፡ ሀምሌትን አዘጋጀቷል፡፡ ከፍቃዱ ተክለማሪያም በፊትቴዎድሮስንሆኖ ተወኗል፡፡

   በቀድሞው ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩንቨርስቲ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን በትወና /አክቲንግ/ በአሜሪካን አገር /ሚኒሶታ/ Minnesota University ሁለተኛ ዲግሪውን ተምሯል፡፡ትምህርቱንም በከፍተኛ ማእረግ ነበር ያጠናቀቀው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙ በቀድሞው ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን/ የአሁን ኢቢሲ/ “ፊት ለፊትበተሰኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ይታወቃል፡፡


   አዲስ አበባ የተወለደውና ሆለታ ያደገው ሀይማኖት እስከቅርብ ቀን ድረስ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ(በተጋባዥመምህርነት) እንዲሁም በራክማኖቭ /ቤት ሲያስተምር ነበር።ሙዚቃ ይወዳል ይላሉ የቅርብ ጓደኞቹ፡፡ጊታርም በድንቅ ብቃት ይጫወት እንደነበር ይመሰክሩለታል፡፡

 
   በሲዲ ያልተለቀቁ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች እንዳሉትም ተጠቁሟል፡፡ ከምንም በላይ ግጥም በማራኪ አቀራረብ በማንበብ ይወደድ የነበረው አነጋፋው አርቲስት ሀይማኖት ዓለሙ በመድረክ መምራትም ተወዳጅ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማስታወቂያው ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራም ነበር፡፡በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን አዳዲስ ድራማዎችን በባለሙያዎች በተዋቀረ ካውንስል ለማስገምገም ከተመረጡ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ 

   ለሁለገብ ባለሙያው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች እና አድናቂዎች መፅናናትን ተመኘሁ፡፡